ፈልግ

አባ ኢብራሂም ፋልታስ አባ ኢብራሂም ፋልታስ  

አባ ፋልታስ በመካከለኛው ምስራቅ በተከሰተው ግጭት ከአሥር ሺህ በላይ ህጻናት ተገድለዋል አሉ

በኢየሩሳሌም የሚገኙት የቅድስት አገር ተንከባካቢ ካህን የሆኑት አባ ኢብራሂም ፋልታስ ከቫቲካን ዜና ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ የእስራኤልና የሐማስ ጦርነት ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ከ10,000 በላይ ሕፃናት መገደላቸውን ገልጸው፥ ‘ለሁለቱ ህዝቦች ሲባል ሁለቱም ሃገራት የጋራ መፍትሄ እንዲፈልጉ አሳስበዋል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

አባ ፋልታስ በቃለ ምልልሱ ጦርነቱን አስመልክተው እንደተናገሩት “እስከ አሁን ድረስ ወደ 30,000 የሚጠጉ ሰዎች እንደሞቱ እና ከ60,000 በላይ ሰዎች እንደቆሰሉ፣ 40,000 ህፃናት ወላጅ አልባ እንደሆኑ፣ እንዲሁም ከ10,000 በላይ ህጻናት እንደተገደሉ መረጃ ደርሶናል” ብለዋል።

በኢየሩሳሌም የሚገኙት የቅድስት አገር ተንከባካቢ ካህን የሆኑት አባ ኢብራሂም ፋልታስ የእስራኤል እና የሐማስ ጦርነት ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ የተከሰቱትን እነዚህን አሰቃቂ ሁነቶች የቫቲካን የዜና ወኪል ከሆነው ፌዴሪኮ ፒያና ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ በዝርዝር ገልጸዋል።

ፍራንቺስካዊያኑ ካህን ጦርነቱ ከተጀመረ 100 ቀናትን እንዳለፈው ካስታወሱ በኋላ፥ በተጨማሪም በዌስት ባንክ በህዝቡ ላይ እየደረሰ ያለውን ስቃይ ሲናገሩ “በዌስት ባንክ እስካሁን ድረስ ከ400 ሰዎች በላይ እንደሞቱ፥ ከ10,000 በላይ ሰዎች እንደቆሰሉ፥ ብሎም በሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች ለእስራት እንደተዳረጉ” በአጽንኦት ገልፀዋል።

በአከባቢው የሚገኘው የአጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ስጋት

አባ ፋልታስ በአከባቢው የምትገኘው የካቶሊክ አጥቢያ ቤተክርስቲያን ስጋት አስመልክተው እንደተናገሩት አሁን እያየን ባለው በቅድስቲቱ ምድር እየተከሰቱ ካሉ አሰቃቂ ክስተቶች አንፃር “የሦስተኛውን የዓለም ጦርነትን” ሊያስነሳ እንደሚችል ጠቁመዋል።

የጋዛ ጦርነት ወደ አከባቢው ሃገራት በመዛመት እየተከስተ ያለውን ነገር ሲገልፁም፥ ደቡባዊ ሊባኖስ በቦንብ መመታቷን፣ በየመን የሁቲ አማፂያን በውጭ የንግድ መርከቦች ላይ የበቀል እርምጃ መውሰዳቸውን በመጥቀስ፥ “እየሆነ ያለውን ነገር በትኩረት ማየት አለብን” ሲሉ በጥብቅ አሳስበዋል።

ካህኑ እየሆኑ ባሉት ነገሮች በጣም መገረማቸውን፥ ብሎም የዓለም መሪዎች ባሳዩት ቸልተኝነት እና የአብዛኛዎቹ ሃገራት መሪዎች ይህን ሁሉ ነገር እያዩ ዝም ማለታቸው በጣም እንዳበሳጫቸው ምንም ሳይሸሽጉ ተናግረዋል።

የዓለም መንግስታት ዝምታን አስመልክተው እንደተናገሩት “እስካሁን ድረስ ስለዚህ ጦርነት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስን ያህል የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረግ ማንኛቸውም ድምፃቸውን ሲያሰሙ አልሰማንም” ብለዋል አባ ፋልታስ።

"እነዚህ ሰዎች ምንም የላቸውም"

ካህኑ አክለውም እንደተናገሩት በጋዛ መላው የክርስቲያን ማህበረሰብ በሁለት አብያተ ክርስቲያናት ውስጥ ተጠልለው እንደሚገኙ በመግለጽ፥ 600 የሚሆኑ ምዕመናን በላቲኑ የካቶሊክ ሆሊ ፋሚሊ ቤተ-ክርስቲያን እና 200 የሚሆኑት ደግሞ በግሪክ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ውስጥ ተጠልለው እንደሚገኙ አብራርተዋል።

አባ ፋልታስ ጋዛ ውስጥ ስላለው አንገብጋቢ ችግር ሲገልፁ፥ “ውሃ የለም፣ ምግብ የለም፣ የመገናኛ ዘዴዎች ዬሉም፣ በአጠቃላይ ምንም ዬለም ማለት ይቻላል” ብለዋል።

ቤተክርስቲያኒቷ “መሰረታዊ ፍላጎቶችን ለማሟላት የምትችለውን ሁሉ እያደረገች ነው” ሲሉ ያረጋገጡት ካህኑ፥ በጋዛ የቆሰሉ ህፃናት ወደ ጣሊያን ተወስደው ህክምና ሊያገኙ የሚችሉባቸው መንገዶች እንዲመቻቹ ያላቸውን ‘ህልም’ አጋርተዋል።

ሁለት ህዝቦች ፣ ሁለት ግዛቶች

ብዙ ሕጻናት “አሁንም በፍርስራሹ ሥር ናቸው፤ ሁሉም ሰው ይህን አሳዛኝ ሁኔታ ያያል፤ እየተከሰተ ያለው በዓይኖቻቸው ፊት ነው፥ የዓለም ሁሉ ኅሊና የት ገባ? የዓለም ኃያላን የት አሉ?” በማለት በምሬት አውግዘዋል።

አባ ፋልታስ ዓለም አቀፍ ፖለቲከኞች “የሁለት ህዝቦች፣ የሁለት ሃገራት መፍትሄዎች” ብለው ያቀረቡትን ሀሳብ በማጤን፥ "ይህ ሃሳብ በእስራኤል ውስጥ የተወሰነ ተቀባይነት አግኝቷል” ብለዋል።

ይህንን መነሻ ግምት ውስጥ በማስገባት “ጊዜው ወደ ተግባር መግባት የሚያስፈልግበት ወቅት ነው” ካሉ በኋላ፥ “ይህ ካልሆነ በቅድስት አገር ውስጥ እስራኤላውያንም ሆኑ ፍልስጤማውያን ማንም በሰላም መኖር አይችልም” በማለት ሃሳባቸውን አጠቃለዋል።
 

23 January 2024, 13:59