ፈልግ

ብፁዕ ካርዲናል አቡነ ብርሃነየሱስ ሱራፌል የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሊቀ ጳጳሳት ብፁዕ ካርዲናል አቡነ ብርሃነየሱስ ሱራፌል የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሊቀ ጳጳሳት  

ብፁዕ ካርዲናል አቡነ ብርሃነየሱስ ሱራፌል ለ2016 ዓ.ም የገና በዓል ያስተላለፉት መልእክት

ብፁዕ ካርዲናል አቡነ ብርሃነየሱስ ሱራፌል የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሊቀ ጳጳሳት የ2016 ዓ/ም የጌታችን የመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል በማስመልከት ለመላው ምዕመናን ያስተላለፉት መልዕክት

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን፡፡

‹‹ሕፃን ተወልዶልናል ወንድ ልጅም ተሰጥቶናል አለቅነትም በጫንቃው ላይ ይሆናል›› (ኢሳያስ 9፤5)

-   በክርስቶስ የተወደዳችሁ ብፁዓን ጳጳሳት

-   ክቡራን ካህናት

-   ገዳማውያንና/ውያት

መላው ምዕመናን የእግዚአብሔር ሕዝብ፤ ከአገራችሁ ውጭ የምትኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን እንኳን ለ2016 ዓ/ም የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ብርሃነ ልደቱ በሰላም አደረሳችሁ፡፡

የእግዚአብሔር ሕዝብ በጭንቀትና በውጥረት ውስጥ በነበረ ጊዜ እግዚአብሔር ታላቅ የመፅናኛ ቃልን እየሰጠ ቀጥሏል፡፡ ፍትህ ሲጎድል ይገስፅና ያስተምር እንደነበረ ሁሉ ሕዝብ በኃዘንና በተስፋ መቁረጥ ላይ ሲወድቅም ያበረታታ ነበር፡፡ ከሕዝቡም ጋር መሆኑን ይገልፅ ነበር፡፡ ከእነኚህ የመፅናኛ ቃሎች መካከልም ስለ አማኑኤል መወለድ የተጻፈው ትልቅ ቦታ አለው፡፡ (ኢሳ 7)

አማኑኤል የሚለው ስም በመጀመሪያ ትርጉሙ በጥንት ከክርስቶስ መወለድ በፊት የነበረውን ህዝብ ሲያጽናና ዛሬ ደግሞ በይሁዳና በአሕዛብ የተቋቋምነውን የዓለም ሕዝቦች በሙሉ ያጽናናል፡፡ የተወለደው ሕጻን የዓለም ብርሃን ነው፡፡ ማለትም ዓለም እንደ ብርሃን አለኝ ብላ የምታስበው ነገር እንኳን ሳይቀር ብርሃን ያስፈልገዋል፡፡ ምጡቅ ብርሃን እንደሚያስፈልገው የማይገነዘብ ዓለም ሳያስበው በጨለማ ሊመላለስ ይችላልና  ከዚህም የተነሳ ነቢዩ ኢሳያስ ‹‹በጨለማ የሚኖር ሕዝብ ታላቅ ብርሃን አየ›› (ኢሳ፤9) ይላል፡፡ ይህ ማለትም ከእግዚአብሔር ርቆ የነበረው ሕዝብ ወደ እግዚአብሔር ቀረበ ማለት ነው፡፡ ይልቁንም በእግዚአብሔር ተጎበኘ ማለት ነው፡፡ የፍትህ መጓደል የፍቅር እጦት  በጨለማ መኖር ማለት ነው፡፡ በሞት ጥላ መመላለስ ማለት ነው፡፡ በእግዚአብሔር ምሕረት ለፍትህ የሚቆምበት ፍቅርን የሚያነግሱበት ዘመን ይመጣል፡፡ ‹‹ሕዝብን አበዛህ ደስታቸውንም ጨምረህ ሰዎች ምርትን ሲሰበስቡ፤ ምርኮን ሲከፋፈሉ ደስ እንደሚላቸው ሁሉ እነርሱም በፊትህ ደስ ይላቸዋል›› የሚለው ቃል ይፈጸማል፡፡ ምክንያቱም እውነተኛ ደስታ ከእግዚአብሔር የሚገኘው ደስታ ነው፡፡ እውነተኛው ምርት የፈጣሪ በረከት ያለበት ምርት ነው፡፡ ይህ ደግሞ በፍትሕና በአምላክ ፍቅር ብቻ የሚቆም ነው፡፡

    ‹‹ሕጻን ተወልዶልናል ወንድ ልጅም ተሰጥቶናል አለቅነትም በጫንቃው ላይ ይሆናል››፡፡ ሕፃን ከማንም በላይ ረዳት ያስፈልገዋል፤ ሕፃንን ማቀፍ መመገብ መጠበቅ ማስተማር ያስፈልጋል፡፡ ከልደት ሚስጥር ስለፍቅር ስለ እንክብካቤ ስለ ሕይወት ብዙ እንማራለን፡፡

    እንግዲህ በዚህ የልደት በዓል እግዚአብሔር ምን ያህል የሰው ልጆችንና ፍጥረታቱን እንደወደደ  እንመልከት፡፡ እግዚአብሔር የሰውን ልጅ በመልኩና በአምሳሉ እንደፈጠረ ሁሉ ምን ጊዜም የበረከቱ ተካፋይ ይሆን ዘንድ ቃል ሥጋ ሆነ፣ የሰው ልጅ በሃጢአት የተነፈገውን ፀጋ  መልሶ ይለብስ ዘንድ ቃል ሥጋ ሆነ፣ አምላክ ከሰው ልጆች ጋር ያለውን ግንኙነት ለማደስ ሰማይንና ምድርን ለማስታረቅ ቃል ሥጋ ሆነ፡፡  የሰው ልጅ በቴክኖሎጂ፣ በማሕበራዊና በተፈጥሮ ሳይንስ በማደጉ በራሱ የሚድን ሊመስለው ይችላል፡፡ ነገር ግን ከላይ በተዘረዘሩት ነገሮች ቢያድግም እራሱን ከጦርነት፣ከጥላቻ፣ከቅናት፣ከግፍና ከሐሰት ማዳን አልቻለም፡፡ የሰው ልጅ እራሱን እንዳልፈጠረ ሁሉ እራሱን ለማወቅ በዙረያው ያለውን ማጥናት አይበቃውም፡፡  ይልቁንም እራሱን ሊመረምር ይገባዋል፡፡ ሳያዳላ ውስንነቱን መረዳት ያሻዋል፡፡ ከሚገኝበት አሳዛኝ ሁኔታ ከገባበት ገደል ከተዘፈቀበት ማጥ ይወጣ ዘንድ ቃል ሥጋ ሆነ፡፡

     የሰው ልጅ ለማኅበራዊ ችግሮቹ መፍትሔ ይፈልጋል፣ ሊፈልግም ይገባዋል፡፡ ነገር ግን ቆም ብሎ ከእርሱ የማሰብ ችሎታና አድማስ ባሻገር መመልከት ሲችል ብቻ ነው መፍትሔን የሚያገኘው በትህትና ወደ ምጡቁ አምላክ ሲመለከት ነው፡፡ ለፍትህ፣ ለእውነትና ለመልካም ነጻነት መሥራት የማንነቱ መሠረት መሆኑን የሚረዳው የልደት በዓልም ለፍትህ፣ ለእውነትና ለመልካም ነፃነት ሰውን የሚጠራ በዓል ነው፡፡ ሰብአዊ ጥበብ የማይደረስበትን አንዳንዴም ጭራሽ የማያስታውሰውን ሀቅ የእግዚአብሔር ቃል ይገልጽልናል፡፡  ይህ ቃል ደግሞ እነሆ ሥጋን ለብሶ በመካከላችንም አደረ! ከእናንተ ጋር ነኝና አትፍሩ ይለናል፡፡

    እውነተኛ ጥበብ ለትሕትናና ለመገረም ቦታን ትሰጣለች፡፡ የሰው ልጅ በትሕትና መንፈስ በዙሪያው ያለውን ሲመለከትና ሲደነቅ ለጥላቻ፣ ለግጭት፣ለሐሰት ቦታ አይኖረውም፡፡ ይልቁንም ለአብሮነትና ለእርቅ ያስባል እንጂ፡፡ አምላክ ስለፍጥረታት ግድ ስለሚለው ለአዕምሮ ልንረዳው የማንችለው ነገር ተከሠተ፡፡ የተአምራት ተአምር ተፈፀመ፡፡ አምላክ የሰውን ልጅ ከማፍቀሩ የተነሣ ደስታውንና ሐዘኑን መካፈል ፈቀደ፡፡ እግዚአብሔር ሰውን በመልኩና በአምሳሉ ፈጥሮ ልዩ ማዕረግ ሰጠው፡፡

    በመጽሐፍ ቅዱሳችን እንደምናየው  በተለያዩ ነቢያት አማካኝነት ፈቃዱን ይገልጽ የነበረው አምላክ ወደ ሰላምና ፍትሕ የሚጠራ ጌታ  ሕዝቡን የሚያፅናና እንዲሁም ወደ ንሰሓ የሚጠራ አምላክ በእኛ መካከል አደረ፡፡ እኛንም ለንሰሐና ለለውጥ ይጠራናል፡፡ ንሰሐ የመለወጥና የማደግ መሠረት ነው፡፡ በሕይወት ያለ ሁሉ ጤናማ እድገት አገኘ የሚባለው ወደ ጤናማ ለውጥም  ቀረበ የሚባለው ለንሰሐ ቦታ ሲኖረው ነው፡፡ ንሰሐ ‹‹እኔ ሙሉ ነኝ ለውጥ አያስፈልገኝም›› ከሚል ስሕተት ያድነናል፡፡ ንሰሐ የተስፋም መሠረት ነው፡፡ ጌታ ወደ ተሻለ ሁኔታ እንደሚያመጣን መረዳት ነው፡፡ ንሰሓ መልካም ሐሳብን መልካም ንግግርን እንዲሁም መልካም ተግባርን ለመላበስ መዘጋጀት ነው፡፡ የልደት በዓልም ተከበረ የሚባለው ሐሳባችንን ንግግራችንን እና ተግባራችንን ሲቀደስልን ነው፡፡

    ሁላችንም እነሆ እንደ ታላቁ ነቢይ ኢሳያስ እኛም ‹‹ሕጻን ተወልዶልናል›› እንበል የስሙንም ድንቅነት እንመስክር፡፡ ኃያል አምላክ መሆኑን በአንደበታችንና በተግባራችን እንመስክር፡፡ የትንሣኤው የምስራች የተወለደው ኃያል አምላክ የዘለዓለም አባት መሆኑን ያሳየናል፡፡ የምድር ነገስታት በጊዜና በቦታ የተወሰኑ ናቸው፡፡የእግዚአብሔር መንግስት ግን የጊዜና የቦታ ገደብ የለውም፤ ትውልዶች ያልፋሉ ጌታ ግን ለዘለዓለም ጸንቶ ይኖራል፡፡ ያለ እግዚአብሔር ሰዎች ፍትሕና ጽድቅን አያመጡም፡፡ ምክንያቱም እግዚአብሔር እራሱ ፍትሕና ጽድቅ ነውና፡፡ ሰዎች ፍትሕና ጽድቅ የሚመስል ነገር ሊያመጡ ይችላሉ ነገር ግን መምሰልና መሆን የተለያዩ ነገሮች ናቸው፡፡

    የተወደዳችሁ ምዕመናን

የክርስቶስን መወለድ በአግባቡ ለማክበር ለሰው ልጆች ሕይወት፣ ለእግዚአብሔር ቤተክርስቲያንና ለእርሱ ቅዱስ ስፍራዎች ክብርን እንስጥ፡፡ ከራስ ወዳድነት መንፈስ እንውጣ በመላው አገራችን ሞት ይብቃ፣ ሰላም ይስፋፋ፡፡ የተራቡ፣ የተጠሙ፣ የታረዙ፣ የተበደሉ፣ የታመሙና የተፈናቀሉ ወገኖቻችንን እናስታውስ፡፡ ከጎናቸው እንሁን እንርዳቸው እናጽናናቸው፡፡ ለኛ ምን ይደረግልን ብቻ ሳይሆን ለሌሎችም ምን እናድርግ እንበል፤ መጠጊያ ለሌላቸው መሸሸጊያ እንሁንላቸው፡፡ የሚገለሉ ባይተዋርነት እንዳይሰማቸው እናድርግ፡፡  ዘመዳቸው እንሁን፡፡ ምክንያቱም የልደት በዓል ክርስቶስ ዘመዳችን እንደሆነ የሚያበሥረን በዓል ነውና፡፡ በልደት ምስጢር ማንም እንግዳ ሊሆን አይገባውም፡፡ እግዚአብሔር ከጥንት ጀምሮ ጠንካራ ትዕዛዝ አስተላልፏል፡፡ በግብጽ ባርነት ሳላችሁ በመገለል፣ በመማረር ኖራችኋል፡፡ ስለሆነም እንግዳ እንዳታማርሩ ይላል፡፡ ይህ ትልቅ የፈጣሪ ትዕዛዝ ነው፡፡ ሁላችንም ልናቀርበው የሚገባው ጥያቄ የሚከተለው ነው፡፡ ‹‹እንግዳ አባርሬ ይሆን››? እንግዳን ከሚያዋርድ ሐሳብ፣ ትምህርት፣ መልዕክት ጋር ተባብሬ ይሆን? የእኔ ባሕል ሙሉ ስለሆነ ሌላውን መጫን፣ ማግለል አለብኝ ብዬ ይሆን? ይህ ዓይነት ሐሳብ ከእግዚአብሔር ቃል እንደሚርቅ ተረድቼ ይሆን? ከእንደዚህ ዓይነት ሐሳብ ለመውጣትስ ምን ማድረግ ይገባኛል ልበል፡፡  ከዚህ ሐሳብና ይህ ዓይነት ሐሳብ ከሚገለጥባቸው ተግባራት ነፃ መውጣት የምንችለው ወደ ገና በዓልና ወደ ትንሣኤ ምስጢር ስንቀርብ ነው፡፡ በዚያን ጊዜ ሰማይና ምድር ከእኛ ጋር አብረው ለታላቁ ጌታ ታላቅ የምስጋና መዝሙር ይዘምራሉ፡፡

    በመጨረሻም በዚህ ታላቅ በዓል ለታመሙት ምሕረትን፤ በታራሚ ቤቶች ላሉት መጽናናትንና መፈታትን፣ በጭንቀትና በመከራ ላይ ለሚገኙት ሁሉ  እግዚአብሔር ሰላሙንና ፍቅሩን እንዲሰጣቸው ሁላችንም የሰላሙ ንጉስ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለአገራችን ሰላሙን እንዲያወርድልን በፀሎት እንትጋ፡፡ ለሁላችንም ንሰሐንና እርቅን የሚፈልግ ልብ ይስጠን፡፡ ሁላችንንም በጥበቡ፣ በምህረቱ፣ በሰላምና በፍቅር ያጽናናን፡፡

    የሰላሙን ንጉስ በማህጸኗ የተሸከመችና የወለደችልን እናታችን እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ፀሎታችንን  ሰምታ ሰላሙን ታሰጠን፡፡

    እግዚአብሔር የልደት በዓላችንን ይባርክልን !

 

+ ብፁዕ ካርዲናል አቡነ ብርሃነኢየሱስ

ሊቀጳጳሳት ዘካቶሊካውያን

06 January 2024, 15:38