ፈልግ

ለንደን ከተማ ለንደን ከተማ  (AFP or licensors)

በእንግሊዝ እና በዌልስ የምትገኘው የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን የዘር ፍትህ ቀን ማክበሯ ተነገረ

በእንግሊዝ እና በዌልስ የምትገኘው ካቶሊካዊት ቤተክርስትያን የዘር ፍትህ እሁድን ጥር 19 ቀን 2016 ዓ.ም. ያከበረች ሲሆን፥ ቤተክርስቲያን ዘረኝነትን በመቃወም እና የዘረኝነት ፍትህን በአዲስ ጉልበት ለማስከበር ትኩረት ያደረገችበት ቀን ነው ተብሏል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

የዘንድሮው የዘር ፍትህ እሑድ መሪ ሃሳብ “በቤተክርስትያን ህይወት እርስ በርስ መተያየት” የሚል ሲሆን፥ ዘራችን እና አስተዳደጋችን ምንም ይሁን ምን ሁላችንም የእግዚአብሔር ልጆች መሆናችንን የማወቅን አስፈላጊነት ያጎላል ተብሏል። 

ቤተክርስቲያኒቷ እንደገለጸችው የዚህ ዓመት መሪ ሃሳብ በዚህ ጉዳይ ላይ ማሰላሰልን፣ መወያየትን እና ወደ ተግባር መግባትን በማበረታታት፥ እንዲሁም እነዚህን ጉዳዮች ከዘር ፍትህ እሑድ በኋላ ባሉት ሳምንታት እና ወራት ውስጥ እንድናከናውን ለማበረታታት ያግዛል ብላለች።

በትናንትናው እሁድ በመላው እንግሊዝ እና ዌልስ ባሉ አቢያተ ክርስቲያናት በተደረጉት ቅዳሴዎች ላይ፥ ደብሮች እና ግለሰቦች በዘረኝነት ምክንያት የሚደርሰው ስቃይ እንዲያበቃ ጸሎት እንዲያደርጉ ጥሪ ቀርቦላቸዋል ተብሏል።

ቤተክርስቲያኒቷ ከተለያዩ ሀገራት እና ባህሎች የተውጣጡ የእመቤታችን ቅድስት ማሪያምን እና የሕፃኑ ኢየሱስን ምስል የሚያሳዩ፥ ግለሰቦች ወይም አጥቢያዎች ከኮምፒዩተሮች ላይ ሊያወርዷቸው የሚችሉ ተከታታይ የፒዲኤፍ ፖስተሮችን እንዳዘጋጀችም ተነግሯል። በተጨማሪም ፖስተሮቹ ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ኢንሳይክሊካል ፍራቴሊ ቱቲ የተወሰደ ጸሎትንም እንደሚያካትት ተገልጿል።

በዚህ ዓመት ክብረ በዓል፣ ቤተክርስቲያኗ ቅዱስ እና አርአያነት ያለው ህይወትን በመምራት ላይ ባሉ ሰዎች ብዝሃነት ላይ ትኩረት ያደረገች ሲሆን፥ የካቶሊክ ቅዱሳን እንደ እኛው በዚህ ዓለም የተመላለሱ እና ወደ እግዚአብሔር ጸሎታችንን እንድናቀርብ የሚማልዱ ጀግኖች ወንዶች እና ሴቶች እንደነበሩ ተነግሯል።

ሊቀ ጳጳስ ፖል ማክሌናን በእንግሊዝ እና በዌልስ የዘር ፍትህን የሚመሩ ጳጳስ ሲሆኑ፥ የዘንድሮውን የዘር ፍትህ እሁድ ጭብጥን ለማብራራት መልእክት እንደፃፉ እና በዚህም መልዕክታቸው ሁሉም ካቶሊኮች ቀኑን እንዲያከብሩ ጥሪ አስተላልፈዋል።

ጳጳሱ ባስተላለፉት መልእክት በቤተክርስቲያኒቱ ታሪክ ውስጥ፥ የሚኖሩበትን ማህበረሰብ ተመልክተው በማህበረሰቡ ውስጥ ላዩት ነገሮች ምላሽ የሚሰጡ ሰዎች እንደነበሩ አስታውሰዋል። እነዚህ ሰዎች ለክርስቶስ ትእዛዛት ንቁ እና ጠንቃቃ ስለነበሩ፥ አንድ ሰው በዘሩ ወይም በቀለሙ ምክንያት ፍትህ ተነፍጎ ሲያዩ በፍጥነት እርምጃ እንዲወሰድ ያደርጉ እንደነበርም ገልፀዋል።

ሊቀ ጳጳስ ማክሌናን እንዳሉት እነዚህ ወንዶች እና ሴቶች ሕይወታቸውን በሙሉ የዘር ፍትህ እንዲሰፍን የሰሩ ሲሆን፥ ምንም እንኳን አንዳንድ ጊዜ በስራዎቻቸው ላይ የጠላትነት ስሜት እና ተቃውሞ ቢያጋጥሟቸውም በፅናት እንደቆዩ እና ከእነዚህም ውስጥ አንዳንዶቹ የቤተክርስቲያን ቅዱሳን እንደሆኑ ይታወቃል ብለዋል።

በመጨረሻም እነዚህ ታላላቅ ሰዎች የዘር ፍትህን አስፈላጊነት እና ለምን በዚህ ጉዳይ ላይ መስራት እንዳለብን እንድንገነዘብ ያበረታቱናል፣ ያስተምሩናል ብሎም ንቁ እንድንሆን ያደርጉናል ብለዋል።
 

29 January 2024, 12:10