ፈልግ

በኢስታንቡል የሚገኝ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን በኢስታንቡል የሚገኝ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን  

ፓትርያርክ በርተሎሜዎስ በቱርክ ጥቃት ከተፈጸመ በኋላ ከምዕመናኑ ጋር ያላቸውን አጋርነት ገለጹ

የቁንስጥንጥንያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ በርተለሜዎስ እሑድ ጥር 19/2016 ዓ. ም. ጠዋት በኢስታንቡል ከተማ ዳርቻ በሚገኝ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ላይ በተፈጸመው ጥቃት ከተጎዱት ምዕመናን ጋር ያላቸውን አጋርነት ገልጸዋል። ቅዱስነታቸው ይህን የገለጹት በኢስታንቡል የሚገኝ ሐዋርያዊ ጽሕፈት ቤት ተወካይ እና የቁንስጥንጥንያ ሐዋርያዊ አስተዳዳሪ ከሆኑት ከብጹዕ አቡነ ማሲሚሊያኖ ፓሊኑሮ ጋር ባደረጉት የስልክ መልዕክት እንደ ነበር ታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በኢስታንቡል በሚገኘው የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቤተ ክርስቲያን በተፈጸመው ጥቃት 52 ዓመት ዕድሜ ያለው ሰው ተገድሎ በርካታ ምዕመና መቁሰላቸውን በማስታወስ የቁንስጥንጥንያው ፓትርያርክ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ በርተሎሜዎስ በቱርክ ለሚገኘው የካቶሊክ ማኅበረሰብ ያላቸውን ድጋፍ ገልጸዋል። ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ በርተለሜዎስ የአደጋው ዜናው እንደደረሳቸው በኢስታንቡል የሐዋርያዊ ጽሕፈት ቤት ተወካይ ለሆኑት ለብጹዕ አቡነ ማሲሚላኖ ፓሊኑሮን በስልክ በማነጋገር ለተጎጂው ቤተሰብ በራሳቸው እና በመንበረ ፓትርያርኩ ስም የተሰማውን ሐዘን ገልጸዋል።

የእስላማዊ መንግሥት ታጣቂ ቡድን ለጥቃቱ ሃላፊነቱን ወስደ

በኢስታንቡል የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቤተ ክርስቲያን ውስጥ እሁድ ጥር 19/2016 ዓ. ም. ጠዋት ሁለት ጭንብል የለበሱ ታጣቂዎች ከፈጸሙት ጥቃት ጋር በተያያዘ ቢያንስ 47 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸው ታውቋል። ከታሰሩት ተጠርጣሪዎች መካከል ሁለቱ ራሱን ከእስላማዊ መንግሥት ከሚለው ቡድን ጋር ግንኙነት አላቸው ተብሎ ይታመናል። እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በታህሳስ 31/2017 ዓ. ም. በኢስታንቡል አዲስ ዓመት መጀመሪያ ላይ ታጣቂ ቡድኑ በአንድ የምሽት ክበብ በፈጸመው ጥቃት 39 ሰዎች ሕይወታቸውን ያጡበት አደጋ ቡድኑ በሀገሪቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የካሄደው የሽብር ጥቃት እንደነበር ይታወሳል።

የቱርኩ ፕሬዝዳንት አቶ ሬሲፕ ጣይብ ኤርዶጋን በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው በኩል ባስተላለፉት የቪዲዮ መልዕክት፥ የአገሪቱ የጸጥታ ሃይሎች በሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች እንዲገቡ መደረጉን አስታውቀዋል።ብጹዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ በርተሎሜዎስ ከሐዋርያዊ ጽሕፈት ቤት ተወካይ ከብጹዕ አቡነ ማሲሚላኖ ፓሊኑሮን ጋር ባደረጉት የመልዕክት ልውውጥ ጉዳዩን በጥልቀት ለመመርመር ባለሥልጣናቱ ያላቸውን ቁርጠኝነት ገልጸው፥ ፍርሃትን እና ወከባን በማስወገድ የሃይማኖት ማኅበረሰቦች በሰላም አብሮ መኖርን ማስከበር አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ እሑድ ጥር 19/2016 ዓ. ም. በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ከተሰበሰቡት ምዕመናን ጋር የመልዓከ እግዚአብሔር ጸሎት ባቀረቡበት ወቅት ባሰሙት ንግግር፥ በኢስታንቡል ከተማ በሚገኝ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ላይ ታጣቂዎች የፈጸሙትን ጥቃት ጠቅሰው፥ በመስዋዕተ ቅዳሴው ጸሎት መካከል ታጣቂዎች የአንድ ሰው ሕይወት አጥፍተው በርካቶች ላይ የመቁሰል አደጋ ማድረሳቸውን ገልጸው ለምዕመናኑ ያላቸውን ቅርበት ገልጸዋል።

 

 

 

30 January 2024, 17:07