ፈልግ

በናይጄሪያ ፕላቶ ግዛት ውስጥ የተጠቂዎቹ ቤተሰቦች ዘመዶቻቸውን በጅምላ ሲቀብሩ በናይጄሪያ ፕላቶ ግዛት ውስጥ የተጠቂዎቹ ቤተሰቦች ዘመዶቻቸውን በጅምላ ሲቀብሩ   (AFP or licensors)

አንግሊካኑ ካህን ናይጄሪያ ውስጥ ለደረሰው ጥቃት ምላሽ ለመስጠት ክርስቲያናዊ ህብረት ያስፈልጋል አሉ

የናይጄሪያ ተወላጅ የሆኑት የአንግሊካን ካህን ዶክተር አባ አንቶኒ ኢሻያ የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ምክር ቤት በጣሊያን በሚገኘው ከቦሴ ማህበረሰብ ገዳም ጋር ባሰናዳው የክርስቲያናዊ አንድነት ፕሮግራም ላይ የተሳተፉ ሲሆን፥ በትውልድ አገራቸው ለተፈጸመው ጥቃት ምላሽ ክርስቲያናዊ ህብረት ስላለው ሚና ለማውሳት ከቫቲካን ዜና ጋር ቆይታ አድርገዋል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

የገና በዓል ሊከበር ጥቂት ቀናት ቀደም ብሎ በነበሩት ተከታታይ ጥቃቶች በሰሜናዊ ናይጄሪያ የሚገኙ ታጣቂ ሃይሎች ከ200 በላይ ሰዎችን ገድለው ከ500 በላይ የሚሆኑትን ደግሞ አቁስለዋል። ጥቃቱ የተከሰተው በፉላኒ እረኞች እና በሐውዜን ገበሬዎች መካከል ረጅም ጊዜን ባስቆጠረው ተደጋጋሚ ጥቃት እና ግጭትን ተከትሎ እንደሆነም ይነገራል።

በናይጄሪያ ስላለው የሽብርተኝነት ጉዳይ የአንግሊካኑ ካህን አባ አንቶኒ ኢሻያ (ዶ/ር) ሲገልጹ “በጣም ውስብስብ እና ለመናገር በጣም አስቸጋሪ ጉዳይ ነው” ካሉ በኋላ “ብዙ ሰዎች በዚህ ጉዳይ አባቶቻቸውን፣ እናቶቻቸውን፣ ወንድሞቻቸውን እና እህቶቻቸውን እንዲሁም መተዳደሪያቸው አጥተዋል” ብለዋል።

በደቡብ አፍሪካ የሚገኘው የዴዝሞንድ ቱቱ ማዕከል ተመራማሪ የሆኑት አባ ኢሻያ በዓለም አብያተ ክርስቲያናት ምክር ቤት በጣሊያን በሚገኘው የቦሴ ገዳም ኢኩሜኒካል ኢንስቲትዩት ክርስቲያናዊ ህብረት ፕሮግራም ላይ እየተሳተፉ ሲሆን፥ የናይጄሪያ ክርስቲያኖችን በመርዳት ረገድ ክርስቲያናዊ ህብረት ስላለው ሚና ከቫቲካን ዜና ባልደረባ ዣን ቤኖይት ሃሬል ጋር ቆይታ በማድረግ ተወያይተዋል።

ይህንን ዝግጅት በድምጽ ለማዳመጥ ተጫወት የሚለውን ምልክት ይጫኑ

አባ ኢሻያ በተለይ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ “የደም ክርስቲያናዊ ህብረት” ወይም “ecumenism of blood” ሲሉ የጠሩት እና በክርስቶስ በማመናቸው ብቻ የተገደሉት ሰዎች ደም “ክርስቲያኖች የሚሰባሰቡበት የህብረት መድረክ እንዲሆን ያደርጋል” ሲሉ አጽንዖት ሰጥተው ተናግረዋል።

በዚህ ጉዳይ ላይ የቤተ እምነት ልዩነቶች አስፈላጊ እንዳልሆነ በመግለጽ፥ “ናይጄሪያ ውስጥ እየተከሰቱ ባሉት ሁኔታዎች ምክንያት ማህበረሰቦቻችንን እና ቤተክርስቲያኖቻችንን ለመጠበቅ በናይጄሪያ ካሉን የጸጥታ ኤጀንሲዎች ጋር በትብብር በመስራትም ቢሆን እንዴት ሀሳቦችን፣ ግብዓቶችን እና መረጃ መለዋወጥ እንደምንችል መማራችን በጣም አስፈላጊ ነው” ብለዋል።

አባ ኢሻያ “ቶሎ የሚቀበል ክርስቲያናዊ ህብረት” እየተባለ የሚጠራውን ሃሳብ አስፈላጊነት ጎላ አድርገው በመግለጽ፥ ይህም አስተምሮ የተለያዩ የክርስቲያን ቤተ እምነቶች እርስ በርስ ምን ሊሰጡ እና ሊቀበሉ እንደሚችሉ መወያየትን ይጨምራል ብለዋል።

ካህኑ አክለውም እንደተናገሩት ከክርስቲያናዊ ህብረት በተጨማሪ በሰሜን ናይጄሪያ እና በመላ አገሪቱ ስላለው የሃይማኖት ተቋማት ውይይት አስፈላጊነትን በመናገር፥ “እግዚአብሔር በሥልጣኑ ሁለቱንም ክርስቲያኖችን እና ሙስሊሞችን እንዲሁም እምነት የሌላቸውንም ጭምር ናይጄሪያውያን እንዲሆኑ ያደረጋቸው በስህተት አይደለም” ካሉ በኋላ “በጣም አስፈላጊው ጥያቄ በናይጄሪያ እንደ ወንድሞችና እህቶች አብረን የምንኖረው እንዴት ነው? የተለያየ የሃይማኖት፣ የብሔር፣ የጎሣ መደብን ማንሳት ከመጀመራችን በፊት እንደ ሰው በመጀመሪያ እንዴት አብረን እንኖራለን? የሚለውን ጥያቄ መመለስ አለብን” ብለዋል።

ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ እንዳሉት በጋራ መራመድ እና መነጋገር አለብን፥ ከምንም በላይ ደግሞ እነዚህን ሁሉ ለማጠናከር እና ልዩነቶችን ወደ ጎን መተው የምንችለው እርስ በርሳችን መደማመጥ ስንችል ነው” በማለት ሃሳባቸውን ቋጭተዋል።
 

26 January 2024, 12:31