ፈልግ

የዓለም አቀፍ የበላይ አለቆች ኅብረት ለመጀመሪያ ጊዜ በኮፕ ጉባኤ ላይ ተሳትፏል የዓለም አቀፍ የበላይ አለቆች ኅብረት ለመጀመሪያ ጊዜ በኮፕ ጉባኤ ላይ ተሳትፏል 

ገዳማዊያት በአካባቢያቸው ያሉትን እና የተገለሉ ሰዎችን ድምጽ ወደ ኮፕ28 ጉባኤ ማምጣታቸው ተነገረ

ገዳማዊያቱ በአከባቢያቸው የሚገኙትን ማህበረሰቦች እና የተገለሉትን ሰዎች ድምጽ በዱባይ በተካሄደው የኮፕ28 ጉባኤ ማምጣታቸው የተነገረ ሲሆን፥ ይህ የተባበሩት መንግስታት ኮንፈረንስ በማጠቃለያው እንደ የነዳጅ ቅሪተ አካል ሎቢ አይነት ውስብስብ ጥያቄዎችን ያስተናገደ ቢሆንም ለፕላኔቷ ጥበቃ ያለውን ቁርጠኝነት ያሳያል ሲሉ የዓለም አቀፍ የበላይ አለቆች ኅብረት (UISG) (ከዓለም ዙሪያ ከ 80 አገሮች የተውጣጡ ወደ 600,000 የሚጠጉ እህቶች እና መነኮሳትን የሚወክል የካቶሊክ ድርጅት ነው) ባወጣው መግለጫ ላይ ተናግረዋል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ገዳማዊያቱ በየአከባቢያቸው ያሉ ማህበረሰቦችን ድምጽ ወደ ዓለም አቀፋዊ የሆኑ ተቋማትና እና ግንኙነቶች በማምጣት ማሰማታቸውን ይቀጥላሉ ሲል ከኮፕ28 ጉባኤ የተመለሰው የዓለም አቀፍ የበላይ አለቆች ህብረት ያወጣው መግለጫ አረጋግጧል።

የዓለም አቀፍ ልማት ተግዳሮቶችን ለመቅረፍ ቁርጠኛ የሆነው ይህ የገዳማዊያቱ እናት ድርጅት የሆነው ህብረት በዱባይ ተሰናድቶ ጥቅምት 2/2016 ዓ.ም. የተጠናቀቀው ለአየር ንብረት ለውጥ በተዘጋጀው የአባል ሃገራት ጉባኤ አካል ሆኖ በመሳተፍ ይህ የመጀመሪያው ነው ተብሏል።

የህብረቱ የ ‘ለምድራችን ተስፋን መዝራት’ የተባለው ዘመቻ አስተባባሪ የሆኑት ሲስተር ማማሊፋር ፖሬኩ “የኮፕ28 ማጠቃለያ ላይ ውስብስብ ጥያቄዎችን አስተናግደናል” ብለዋል።

የኮፕ28 ጉባኤ በአንድ በኩል የፕላኔታችንን ጥፋት ለማስቆም የሚያስፈልጉትን እርምጃዎች የሚቃወመውን የነዳጅ ቅሪተ አካል ሎቢን በንቃት የተጋፍጠ ሲሆን፥ በሌላ በኩል ደግሞ የጋራ ቤታችንን ለመጠበቅ እና ለማደስ የተሰማሩትን የዓለም አቀፍ ህብረቶች ጥንካሬ፣ ተደራሽነት እና ቁርጠኝነት አጉልቶ አሳይቷል ተብሏል።

በኮፕ 28 ላይ የተነሱ ቁልፍ ነጥቦች

ሲስተር ማማሊፋር ፖሬኩ የዓለም አቀፍ የበላይ አለቆች ህብረት በኮፕ ጉባኤ ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ መሳተፉ፥ ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ለውጥ ውይይቶችን ለመረዳት፣ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የድጋፍ ትብብሮች ላይ ከተሰማሩ የሃይማኖት ቡድኖች ልምድ ለመቅሰም እና ለወደፊት ትብብር የተቀናጁ ስልቶችን ለመዳሰስ ጥሩ እድል እንደሆነ ገልፀዋል።

ኅብረቱ ቅድሚያ ከሚሰጣቸው ጉዳዮች አንዱ በአየር ንብረት ለውጥ በግንባር ቀደምትነት የተጎዱ ሰዎችን ድምፅ የዓለም አቀፉ ውይይት ማዕከል መሆኑን ማረጋገጥ ነበር።

የበላይ አለቆቹ ህብረት ወደ ኮፕ28 ያመጣቸው ቁልፍ ነጥቦች “የብዝሀ ሕይወት መጥፋትን፣ ብክለትን እና ሌሎች የአካባቢ ተግዳሮቶችን ለመፍታት የሚያግዙ መንገዶችን ሁለገብ በሆነ አቀራረብ ከአየር ንብረት እርምጃዎች ጋር ማቀናጀት ሲሆን፥ የአካባቢ ጥበቃን እና የሰው ልጆችን እንክብካቤ ማዋሃድ፣ አጥፊ የፍጆታ ልማዶችን የሚደግፍ ሰዋዊ እይታን አለመቀበል፣ እና በጣም ተጋላጭ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎችን ጥያቄዎች በተቋም እና በአመራር ማዕቀፎች ውስጥ ማቀናጀት” የሚሉት ናቸው ተብሏል።

ተግዳሮቶችን ለመፍታት በዓለም አቀፍ ደረጃ የተገናኙ ሲስተሮች

በዓለም ዙሪያ ያሉ ሲስተሮች በአካባቢያቸው ባሉ ማህበረሰቦች ፍላጎት ላይ የተመሰረተ በውይይት የዓለም አቀፍ ልማቶች ላይ ጫና በማሳደር የአካባቢያዊ ተግዳሮቶችን በተግባር እና በማስተባበር ለመቅረፍ ቆርጠዋል።

እ.አ.አ. በ2022 ከግሎባል ሶሊዳሪቲ ፈንድ በተገኘ ድጋፍ ህብረቱ 'ገዳማዊያት ለአካባቢ ጥበቃ፡ የተገለሉ ሰዎችን ድምጾች በማዋሃድ፣ የሲስተሮቹን በእምነት ላይ የተመሰረተ እና ሥነ-ምህዳራዊ ለውጥን ራዕይ የሚገልጽ እና ለትብብር ሥራዎች ቅድሚያ የሚሰጥ' ጉዳዮችን የሚዘረዝር መግለጫ አውጥቶ ነበር። ይህ መግለጫ ህብረቱ ለመጀመሪያ ጊዜ ለተሳተፈበት የኮፕ ጉባኤ ላይ የተሟጋችነት ድምጹን እንዲያሰማ አዘጋጅቶታል ተብሏል።

ለወደፊቱ ቅድሚያ የሚሰጣቸው ነገሮች

ህብረቱ በሚቀጥለው ዓመት ማለትም እ.አ.አ. በ2024 ቅድሚያ ከሚሰጣቸው ጉዳዮች ውስጥ በዓለም አቀፍ የትብብር መድረኮች ላይ ስልታዊ ተሳትፎ ማድረግ፣ በሀገር አቀፍ ደረጃ የአካባቢ ጥበቃ ላይ የሚሰሩትን ተቋማት ማጠናከር እንዲሁም እንደ ዘላቂ ግብርና እና ማዕድን ኢንዱስትሪዎች ባሉ ዘርፎች ላይ በትኩረት ለመስራት እንዳሰበ ገልጿል።

ሲስተር ማማሊፋር አፅንዖት ሰጥተው እንደተናገሩት “የዚህን አሳሳቢ ቀውስ ዋና መንስኤዎች ለመፍታት መሪዎቻችን ለነዚህ አስቸጋሪ ተግዳሮቶች ሥር ነቀል መፍትሄዎችን እንዲፈልጉ ማበረታታት አለብን” ብለዋል።

በመጨረሻም የህብረቱ የዘመቻ አስተባባሪ የሆኑት ሲስተር ማማሊፋር “የዓለም አቀፍ የበላይ አለቆች ኅብረት በሁሉም የዓለም ክፍል ከሚኖሩ ማህበረሰቦች ጋር ጎን ለጎን ለመራመድ ቆርጦ በመነሳት፥ ለሁሉም የሰው ልጅ እና ለተቀደሰችው ምድራችን አስተማማኝ፣ ፍትሃዊ እና ሰላማዊ የወደፊት ህይወት በጋራ ለመጓዝ ቁርጠኛ ነው” በማለት ደምድመዋል።
 

15 December 2023, 14:31