ፈልግ

2019.12.01 stella di Natale

ወደፊት የምትሄድ ቤተክርስቲያን

እግዚአብሔር በእርሱ የሚያምኑትን ‹‹ወደፊት እንዲሄዱ›› እንዴት እንደሚጠይቃቸው የእግዚአብሔር ቃል ያለማቋረጥ ይነግረናል፡፡ አብርሃም ወደ አዲስ ምድር እንዲሄድ ጥሪ ደረሰው (ንጽ.ዘፍጥ.12፡1-3)፡፡ ሙሴ ‹‹ሂድ፣ እልክሃለሁ›› (ዘጸ.3፡10) የሚለውን የእግዚአብሔርን ጥሪ ሰማ፤ ሕዝቡንም ወደ ተስፋይቱ ምድር መራ (ንጽ.ዘፀ.3፡17)፡፡

የእዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

እግዚአብሔር ኤርምያስን ‹‹ወደምልክህ ሁሉ ትሄዳለህ›› (ኤር.1፡7) አለው፡፡ በዘመናችንም ‹‹ሂዱና ደቀ መዛሙርቴ አድርጉአቸው››! የሚለው የኢየሱስ ትዕዛዝ በተለዋዋጭ ሁኔታዎችና ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተለወጡ በመጡ የቤተክርስቲያን የስብከተ ወንጌል ተልእኮ አዳዲስ ተግዳሮቶች ውስጥ ያስተጋባል፡፡ እኛም ሁላችን በዚህ አዲስ የ‹‹ሂዱ›› ተልእኮ እንድንሳተፍ ተጠርተናል፡፡ እያንዳንዱ ክርስቲያንና ማህበረሰብ ጌታ የሚያሳየውን መንገድ ለይቶ ማወቅ አለበት፡፡ ነገር ግን፣ ሁላችንም የወንጌልን ብርሃን ፍለጋ ከራሳችን ምቹ አካባቢ ተነሥተን ወደ ‹‹ዳርቻ›› ሁሉ እንድንሄድ የሚጠይቀንን የእርሱን ትዕዛዝ ማክበር አለብን፡፡

የደቀ መዛሙርት ማኅበርን የሚያደምቀው የወንጌል ደስታ የተልእኮ ደስታ ነው፡፡ ሰባ ሁለቱ ደቀ መዛሙርት ከተልእኮአቸው በተመለሱ ጊዜ የተሰማቸው ይኸው ነው (ንጽ.ሉቃ.10፡17)፡፡ ኢየሱስም በመንፈስ ቅዱስ  ሐሴት አድርጎ ራሱን ለድሆችና ለሕፃናት የገለጸውን አብን ባመሰገነ ጊዜ የተሰማው ይኸው ነው (ንጽ. ሉቃ.10፡21)፡፡ በጴንጠቆስጤ ዕለት ሐዋርያት ‹‹በገዛ ቋንቋቸው›› (የሐዋ.2.6) ሲናገሩ የሰሙ የመጀመሪያዎቹ ምእመናን የተሰማቸው ይኸው ነበር፡፡ ይህ ደስታ ወንጌል ለመሰበኩና ፍሬ ለማፍራቱ ምልክት ነው፡፡ ሆኖም የመሄድና የመስጠት፣ ከራሳችን ወጥተን የመሄድ፣ መልካም ፍሬ መዝራት የመቀጠላችን ተነሣሽነት ምን ጊዜም አይቋረጥም፡፡ ጌታ ‹‹ከዚህ ተነሥተን በአቅራቢያ ወዳሉት መንደሮች እንሂድ፤ እዚያም ልስበክ፤ የመጣሁት ለዚሁ ነውና››  (ማር.1፡38) አለ፡፡ በአንድ ስፍራ አንዴ ዘሩ ከተዘራ በኋላ ኢየሱስ ነገሮችን ለማብራራት ወይም ተጨማሪ ተአምራት ለማድረግ ሲል ወደ ኋላ አልቀረም፤ ወደ ሌሎች መንደሮችም እንዲሄድ መንፈስ ገፋፋው፡፡

የእግዚአብሔር ቃል ኃይል አስቀድሞ አይታወቅም፡፡ ወንጌል ገበሬው ተኝቶ ሳለ እንኳ አንዴ ከተዘራ በኋላ በራሱ ስለሚያድግ ዘር ይናገራል (ማር.4፡26-29)፡፡ ቤተክርስቲያንም ከእኛ ግምትና አስተሳሰብ በላይ በሆኑ መንገዶች የፈለገውን ማድረግ የሚችለውን የዚህን ቃል ፍጹም ነጻነት አውቃ መቀበል አለባት፡፡

ቤተክርስቲያን ለኢየሱስ ያላት ቅርበት የጋራ ጉዞ አካል ነው፤ ‹‹አንድነትና ተልእኮ በመሠረቱ እርስ በርስ የተቆራኙ ናቸውና››፡፡ የጌታዋን አብነት በታማኝነት በመከተል ቤተክርስቲያን ዛሬ ሄዳ ወንጌልን ለሁሉ፣ በሁሉ ቦታ፣ በሁሉም አጋጣሚ፣ ያለ ማመንታት፣ ያለ ማወላወል ወይም ያለ ፍርሃት መስበክ እጅግ ያስፈልጋታል፡፡ የወንጌል ደስታ ለሁሉም ሕዝብ ነው፤ ከእርሱ የሚቀር ማንም የለም፡፡ ‹‹አትፍሩ፣ ለሕዝቡ ሁሉ ታላቅ ደስታ የሚሆን መልካም ዜና ይዤላችሁ መጥቻለሁ›› (ሉቃ.2፡10) በማለት መልአኩ ለቤተልሔም እረኞች የተናገረው ይህንን ነው፡፡ የዮሐንስ ራእይ መጽሐፍ ‹‹በምድር ላይ ለሚኖሩ ለሕዝብ፣ ለነገድ፣ ለቋንቋና ለወገን ሁሉ ስለሚሰበከው የዘላለም ወንጌል›› (ራእይ.14፡6) ይናገራል፡፡

 

14 December 2023, 15:27