ፈልግ

የኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን 10 ዓመት የቤተክርስቲያን ዕቅድ ትግበራን የማስጀመሪያ መርሃግብር ስብሰባ ሲካሄድ የኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን 10 ዓመት የቤተክርስቲያን ዕቅድ ትግበራን የማስጀመሪያ መርሃግብር ስብሰባ ሲካሄድ 

የኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን 10 ዓመት የቤተክርስቲያን ዕቅድ ትግበራን የማስጀመሪያ መርሃግብር ተጀመረ

ታህሳስ 9 ቀን 2016 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ከተማ በሚገኘው ‘ኢንተር ላግዤሪ ሆቴል’ ከጥዋቱ ሦስት ሰዓት እስከ አስር ሰዓት ድረስ የኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን የአስር ዓመት ዕቅድ ትግበራ ማስጀመሪያ መርሃግብር ተካሂዷል።

የአስር ዓመት የቤተክርስቲያን አቀፍ ስልታዊ ዕቅድ የካቶሊክ ጳጳሳት ጥረቶችን ለመምራት እና ለማስተባበር የተዘጋጀ ዋቢ ሰነድ ነው። ይህ ሰነድ በሁሉም የቤተክርስቲያኒቷ ባለድርሻ አካላት ሲካሄድ የነበረ ተከታታይ የአንድ ዓመት የውይይት ውጤት እንደሆነም ተገልጿል።

አዘጋጅ እና አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

ይህ የኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን የአስር ዓመት ዕቅድ በአራት መሰረታዊ ክፍሎች የተዋቀረ ሲሆን እነዚህም የቤተክርስቲያን ቀኖናዊ መዋቅር፣ የሃዋሪያዊ አገልግሎት፣ የልግስና አገልግሎት እና የቤተክርስቲያን አስተዳደር ሲሆኑ፥ ከነዚህም በተጨማሪ ሥርዓታዊ አቅምን ማረጋገጫ የሆኑትን ከለላ እና ጥበቃ ማድረግ፣ ክትትል፣ ግምገማ፣ ተጠያቂነት እና መማማርን ማጎልበት እንዲሁም አካታችነት፣ ተግባቦት እና ዋቢነትን አካቶ የያዘ ሰነድ እንደሆነ ተገልጿል።

ይሄንን መርሃ ግብር ብጹዕ ካርዲናል አቡነ ብርሃነኢየሱስ ሊቀ ጳጳሳት ዘካቶሊካዊያን፡ የኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ጳጳሳት ጉባኤ ፕረዚዳንት በጸሎት እና ቡራኬ ያስጀመሩ ሲሆን፥ በዚህ ታላቅ መርሃግብር ላይ የኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ብፁዓን ጳጳሳት፣ በኢትዮጵያ የቅድስት መንበር ተወካይ፣ የሁሉም ሀይማኖት ተቋማት መሪዎች እና ተወካዮች፣ የኢፌዴሪ የሚኒስትር መስሪያ ቤቶች ተወካዮች፣ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅት ተወካዮች፣ አጋር ድርጅቶች፣ የተለያዩ ሀገራት የኢምባሲ ተወካዮች፣ የቤተክርስቲያኒቱ ካህናት፣ ደናግል፣ የሃገረ ስብከት አመራሮች፣ ምዕመናን፣ ወጣቶች፣ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች እና ከ200 በላይ የሚሆኑ ተሳታፊዎች ተገኝተዋል።

የዚህ ዕቅድ ዋና ራዕይ የኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን በሲኖዶሳዊ መንፈስ እውነተኛ የስብከተ ወንጌል ሥራ ሰርታ ደቀመዛሙርትን ማፍራት እንደሆነም ተነግሯል። ተልዕኮውም እውነተኛ የወንጌል ምስክርነት በመስጠት ትክክለኛ ሥርዓተ አምልኮ በመፈጸም ለሁለንተናዊ የሰው ልጅ እድገት በመስራት፥ ከሌሎች ቤተ እምነቶች ጋር በመቀራረብ እና ብቁ እና ጥልቀት ያለው የእምነት አስተምሮ በማስተማር ስብከተ ወንጌልን ማጠናከር እንደሆነም ተገልጿል።

በተጨማሪም ይህ መሪ ስልታዊ ዕቅድ ሥራዎችን በጥልቀት ለመስራት፣ ዕቅዶችን እና ድርጊቶችን በማጣጣም ተልዕኮዎችን ለማሳካት ያሉትን ፍላጎቶች እውን በማድረግ ላይ እንደሚያተኩር ተመላክቷል።  

ይህ ሰነድ ያሉትን ወሳኝ ዕድሎችን በመጠቀም እና ያገጠሙትን አስቸጋሪ ተግዳሮቶችን ደግሞ ለማሸነፍ አማራጮችን ያስቀመጠ ነው ተብሏል። በተጨማሪም የጠቅላይ ጽ/ቤቱን እና የሃገረ ስብከቶቹን ዕቅዶች በማውጣት ቅድምያ በመስጠት እና በመምራት ረገድ ቁልፍ ሚና እንደሚጫወትም ተገልጿል። ሌሎች ከቤተክርስቲያኗ ውጪ ያሉ አካላትም የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ዬት እና እንዴት ጥሪቷን እና ሃብቷን ጥቅም ላይ ማዋል እንዳሰበች እንዲያውቁ ይረዳል ተብሏል። በተጨማሪም ከውስጥ እና ከውጭ ያሉ የቤተክርስቲያኒቷ አጋሮች፣ ለጋሾች፣ መንግስት፣ እና መንግስታዊ የሆኑ ባለድርሻ አካላት ጋርም ግንኙነት ለማድረግ እንደሚረዳም ተገልጿል።

አጠቃላይ አላማውም ቤተክርስቲያኒቷ እኛ የምንፈልገው ቤተክርስቲያን እንድትሆን አቅጣጫዎችን እንደሚያስቀምጥ እና ስልታዊነት እና ቀጣይነት ባለው የሃይማኖት መሰረት ወይም በመለኮታዊ ስርዓተ አምልኮ መሰረት ወንጌልን መስበክ እንዲቻል ብሎም በህብረት፣ በአንድነት እና በጋራ መጓዝ እንዲቻል እንደሚያግዝ ተገልጿል።

ይህ የአስር ዓመት የቤተክርስቲያን አቀፍ ስልታዊ ዕቅድ ህብረተሰቡን በትምህርት፣ በጤና እና በማህበራዊ ዘርፎች በተቀናጀ እና በተናበበ መልኩ ለማገልገል እንዲቻል መሪ ሰነድ ሊሆን እንደሚችልም ተመላክቷል።   

20 December 2023, 12:57