ፈልግ

አቶ ጌሪ ድሪንካርድ በቫቲካን ሬዲዮ ቃለ ምልልስ ሲያደርጉ አቶ ጌሪ ድሪንካርድ በቫቲካን ሬዲዮ ቃለ ምልልስ ሲያደርጉ 

ሳንት ኤጂዲዮ የተባለው የካቶሊክ ማህበር ሞት የተፈረደበትን ‘የኬኔት ስሚዝን ህይወት እናድን’ አለ

የ ሳንት ኤጂዲዮ ወይም የቅዱስ አጂዲዮ ማህበረሰብ (የ ‘ሳንት ኤጂዲዮ ማህበረሰብ’ ተብሎ የሚጠራው ማህበር እ.አ.አ. በ1968 በአንድሪያ ሪካርዲ መሪነት የተመሰረተ እና ለማህበራዊ አገልግሎት የተሠጠ የካቶሊክ እምነት ተከታዮች ማህበር ነው) በአሜሪካ አላባማ ግዛት ሞት የተፈረደበትን የኬኔት ስሚዝ ህይወት ለማዳን “የሞት ቅጣት ይብቃ” በማለት ጥሪውን በይፋ አስተላልፏል። ጥሪው የተላለፈው “ከተሞች ለህይወት - የሞት ቅጣትን የሚቃወሙ ከተሞች” በሚል መሪ ቃል ለሁለት ቀናት በተደረጉት ዝግጅቶች ላይ እንደሆነም ታውቋል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

ኬኔት ስሚዝ የአንድ ፓስተር ሚስት በመግደል ክስ ተከሶ የሞት ፍርድ እንደተፈረደበት እና የሞት ፍርድ ውሳኔውም የሕግ ክፍተት አለበት በሚል የውዝግብ ማዕከል ለመሆን እንደቻለም ተነግሯል። አቶ ኬኔት ከዚህ በፊትም ያልተሳካ የሞት ቅጣትን እንዳስተናገደ እና አሁን ደግሞ የአላባማ አስተዳደር ለእንስሳት እርድ እንኳን የማይፈቀደውን ናይትሮጅን ሃይፖክስያ የተባለ ንጥረ ነገር ወይም ጋዝ ጥቅም ላይ ለማዋል እንደፈለገም ለማወቅ ተችሏል። ይህ ጭካኔ የተሞላበት የአገዳደል ዘዴ ከዚህን በፊት በማንም ላይ ተሞክሮ እንደማያውቅ እና አሁን በሰው ላይ ሲተገበር ለመጀመሪያ ጊዜ እንደሚሆንም ተገልጿል።

በሮም ላይ የተመሰረተው የሳንትኤዲዮ ማህበረሰብ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ክርስቲያኖች በዓለም ዙሪያ የሞት ቅጣትን ለማስወገድ እንዲሰሩ ላቀረቡት ጥሪ ምላሽ ለመስጠት የተደረገ እንደሆነም ተነግሯል።

ይህ ማህበር አቶ ኬኔት ስሚዝን ለማዳን ያቀረበው ጥሪ ማህበረሰቡ ያዘጋጀው እና ለሁለት ቀናት “ከተሞች ለህይወት - የሞት ቅጣትን የሚቃወሙ ከተሞች” በሚል መሪ ቃል ከህዳር 19-20 ድረስ ሲካሄድ የነበረው ዝግጅት አካል እንደሆነ የተገለፀ ሲሆን፥ ይህም ዝግጅት በመርሃ ግብሩ ላይ የሞት ቅጣትን የሚቃወሙ ዓለም አቀፍ ኮንፈረንሶችን አካቷል።

የሞት ፍርድ ተፈርዶባቸው የነበረው አቶ ጌሪ ድሪንካርድ ከቫቲካን ዜና ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፥ አሁን ከሳንት ኤጊዲዮ ጋር በመሆን የሞት ቅጣትን የመቃወም ዘመቻ እያካሔዱ እንደሆነ ገልፀዋል።

አቶ ጋሪ የቀደመ ታሪካቸውን ሲናገሩ ጸሎት እና የሰዎች መስተጋብር ባልፈጸሙት ግድያ የተፈረደባቸው የስምንት ዓመት እስራትን እንዴት ታግሰው እንዲወጡ እንደረዳቸው ተናግረዋል። በማከልም የሞት ቅጣት በሰለባው ቤተሰቦች ላይ ‘የጥላቻ ስሜትን’ ስለሚያሳድር ከባድ ነገር እንደሆነም ጠቅሰዋል።

የአቶ ጌሪ ድሪንካርድ ታሪክ

እ.አ.አ. በ1990ዎቹ አጋማሽ ላይ ነበር አቶ ጌሪ ድሪንካርድ በዝርፊያ እና በግድያ ወንጀል ተከሰው በአላባማ ክልል የሞት ፍርድ የተፈረደባቸው። ስለዚህም ጉዳይ ሲያብራሩ “በወቅቱ ስለ ጉዳዩ ፈፅሞ የማያውቁ እና ብቃት የሌላቸው ጠበቆች ተሾሙብኝ፥ ከሶስት ቀናት በኋላ ጥፋተኛ ሆኜ ተገኝቼ በኤሌክትሪክ ወንበር ላይ የሞት ቅጣት እንዲፈፀምብኝ ተፈርዶብኝ ነበር” ብለዋል አቶ ጌሪ ድሪንካርድ።

አቶ ጌሪ የጥፋተኝነት ውሳኔውን ይግባኝ በመጠየቅ ጉዳዩን ብቃቱ ወዳላቸው በርካታ ጠበቆች በማዞር መርታት ችለዋል። “በወቅቱ እስር ቤት እያለሁ” ይላሉ አቶ ጌሪ፥ “ሰዎች እንዲያገኙኝ እና እገዛ እንዲያረጉልኝ ለሁሉም ሰው እየጻፍኩ እለምን ነበር” ብለዋል።

ይግባኝ ከማቅረባቸውም በፊት በአላባማ የሚገኙ የሀገር ውስጥ ጋዜጦች “ድሪንካርድ የሚመኘውን ቡድን አገኘ” የሚል ርዕስ ይዘው ይወጡ ነበር፥ ምክንያቱም በዚያን ጊዜ አቶ ጌሪ ድሪንካርድ ንፁህ መሆናቸውን ያረጋገጡ ጥሩ ጠበቆች ስለ ነበሩ ነው።

እምነት እና ጓደኝነት

አቶ ጌሪ ድሪንካርድ በመቀጠልም፥ እምነት እና የብዕር ጓደኞች የሞት ፍርድ በተፈረደባቸው ወቅት የረዷቸው ነገሮች እንደሆኑ ገልፀዋል። በተጨማሪም መላውን የቤተ ክርስቲያን ጉባኤዎች ጨምሮ ብዙ ሰዎች ስለ እርሳቸው ይጸልዩ እንደ ነበር ተናግረዋል።

“ጸሎት እኔን ከሞት ፍርዱ ለማውጣት ትልቅ እገዛ እንደነበረው በእውነት አምናለሁ” ሲሉ አቶ ጌሪ ድሪንካርድ አረጋግጠዋል።

ለኬኔት ስሚዝ የተደረገ ጥሪ

ከላይ እንደተጠቀሰው አቶ ጌሪ ድሪንካርድ በግል ለሚያውቁት በኬኔት ስሚዝ ላይ የተላለፈውን የሞት ፍርድ ከማህበሩ ጋር ሆኖ ለመቃወም ሳንት ኤጂዲዮ ባዘጋጀው ዝግጅት ላይ ለመካፈል ሮም ተገኝተው ነበር።

“በአላባማ የሞት ፍርድ የተፈረደበትን የኬኔት ስሚዝን ህይወት ለመታደግ የግባኝ ጥሪያችንን ማሰማት ጀምረናል” ሲሉ የሳንትኤጊዲዮን ማህበረሰብ የሞት ቅጣትን በአሜሪካ ለማስቀረት የሚያደርገውን ዘመቻ የሚመሩት ካርሎ ሳንቶሮ ገልፀዋል።

አቶ ካርሎ ሳንቶሮ ከአንድ ዓመት በፊት አቶ ኬኔት ስሚዝ ላይ ከ6 ሰዓታት በላይ የፈጀው እና በመጨረሻም የከሸፈውን የሞት ቅጣት ሙከራ እንዴት እንደተፈፀመ አብራርቷል።

ባለፈው ወር አሉ አቶ ካርሎ በመቀጠል፥ የአላባማ ጠቅላይ ፍርድ ቤት “በእንስሳት ላይ እንኳን ለመተግበር የማይፈቀደውን ናይትሮጂን ሃይፖክሲያ ጋዝ በመጠቀም ሌላ ኢሰብአዊ የሆነ የሞት ቅጣት እንዲፈፀም ወስኖ ነበር” በማለት ተናግረዋል። አቶ ካርሎ ከኬኔት ስሚዝ ጀምሮ የሞት ቅጣትን ለማስወገድ የሳንትኤጊዲዮ ማህበር ያለውን ቁርጠኝነት በድጋሚ ሲገልጹ፥ “ሁሉም ሰዎች የተቃውሞ ጥሪውን እንዲቀላቀሉን እና ለአላባማ ገዥ አቤቱታ እንዲልኩ እንጋብዛለን” ብለዋል።

                                         “በዓለም ላይ ያለውን የሞት ቅጣት አንድ ላይ እናስቁም!”

ቤተሰብን መቅጣት ይቁም

አቶ ጌሪ ድሪንካርድ የሞት ቅጣት የትኛውም “የሰለጠነ” አገር ሊፈቅደው የማይገባው አረመኔያዊ ተግባር እንደሆነ በማብራራት፥ የሞት ቅጣትን እንደ ቂም በቀል እንጂ ቅጣት እንዳልሆነ ገልጸዋል። ይህንንም ሲያስረዱ “እስረኛውን አይቀጡም፥ እስረኛው ሞት ሲፈረድበት መሞቱን ይቀበላል፥ በተለይ ከአምላክ ጋር ሰላም ካደረገ አይቀጣም” ካሉ በኋላ በድርጊቱ የሚቀጣው ግን የተጎጂ ቤተሰቦችና የእስረኞች ቤተሰቦች መሆናቸውን ጠቁመዋል።

አቶ ጌሪ ድሪንካርድ የሞት ቅጣትን ለመሰረዝ ያቀረቡትን ጥሪ በመድገም፥ ቅጣት የሚደርስባቸው ፍርዱ የተወሰነበት ሰው ቤተሰቦች እንደሆኑ ያላቸውን እምነት በድጋሚ ተናግረዋል። ምክንያቱም ደግሞ ይላሉ፥ “አቃቤ ህግ በተጠቂው ቤተሰቦች ላይ የጥላቻ መንፈስ ያሰርፃል፥ ስለዚህ የሚቀጡት የቤተሰቡ አባላት እንጂ እስረኛው አይደለም” ብለዋል።

በመጨረሻም “በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ብቻ ሳይሆን በሁሉም የሞት ቅጣት በሚተገበርባቸው ሃገራት በሙሉ የሞት ቅጣትን ለማስቀረት ሁሉም ሰው እንዲረዳን እንጸልያለን” ሲሉ ተናግረዋል።
 

01 December 2023, 14:33