ፈልግ

የ 'አዎር ሌዲ ኦፍ አረብያ' የሚሰኘው የእመቤታችን ምስል የ 'አዎር ሌዲ ኦፍ አረብያ' የሚሰኘው የእመቤታችን ምስል  (Copyright (c) 2018 Ryle Silva/Shutterstock. No use without permission.)

ኩዌት የ‘አዎር ሌዲ ኦፍ አረቢያ’ ቤተክርስቲያንን 75ኛ ዓመት ክብረ በዓል ልታከብር እንደሆነ ተነገረ

በጌታችን እናት ቅድስት ድንግል ማሪያም የተሰየመው በኩዌት የሚገኘው ቤተክርስቲያን በባህረ ሰላጤው ሀገራት ካሉት ቤተክርስቲያናት የመጀመሪያው ሲሆን 75ኛ ዓመት የአልማዝ ኢዩቤልዩ የምስረታ በዓሉን ለማክበር በዝግጅት ላይ እናዳለች ተነግሯል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

በኩዌት የሚገኘው የካቶሊክ ማህበረሰብ ለአንድ ዓመት ሙሉ ሲከበር የነበረውን፥ በኩዌት ምድር የመጀመሪያ የሆነችው ባህሬን፣ ኳታር እና ሳዑዲ አረቢያን ጨምሮ የሰሜን አረቢያ ሐዋርያዊት ሃገረስብከት “እናት ቤተክርስቲያን” የሆነችውን የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም ቤተክርስቲያን (አዎር ሌዲ ኦፍ አራቢያ) 75 ዓመት የኢዮቤልዩ ክብረ በዓል ሊጠናቀቅ እንደሆነ ነው የተነገረው።

የአልማዝ ኢዮቤልዩ አከባበር በታህሳስ 2 ቀን 2015 ዓ.ም. የተጀመረ ሲሆን፥ ታኅሣሥ 28 ቀን 2016 ዓ.ም. ዕለተ ዓርብ ላይ በሚከበረው በቅድስት ድንግል ማሪያም ዓመታዊ ክብረ በዓል፣ የሃገረ ስብከቱ ጳጳስ በሆኑት አልዶ ቤራርዲ በሚመራ ሥርዓተ ቅዳሴ ይጠናቀቃል ተብሏል።

ሥርዓተ ቅዳሴውን በኩዌት የቅድስት መንበር ተወካይ በሆኑት ሊቀ ጳጳስ ዩጂን ማርቲን ኑጀንት፣ የአረብ ሃገራት ካህን በሆኑት አባ ሚካኤል ፈርናንዴዝ እና በኩዌት ከሚገኙ ካህናት ጋር አንድ ላይ በመሆን እንደሚያሳርጉት ይጠበቃል። በተጨማሪም የኳታር እና የባህሬን ተወካዮችም ይገኛሉ ተብሏል።

በቅድስት ሀገር እየተካሄደ ባለው ጦርነት ምክንያት በዓሉ በድምቀት አይከበርም

ሊቀ ጳጳስ አልዶ ቤራርዲ ለፊደስ ኤጀንሲ እንደተናገሩት በጋዛ እየተካሄደ ባለው ጦርነት ለሚሰቃዩት የፍልስጤም ህዝብ አጋርነት ሲባል ለዚህ ዝግጅት የታቀዱ ሌሎች ሥነስርዓቶች በሙሉ በመንግስት ተሰርዘዋል ብለዋል።

የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቤተ ክርስቲያን መጀመሪያ ላይ በአል-አህማዲ ከተማ በሚገኘው አሮጌ የኃይል ማመንጫ ጣቢያ ውስጥ እ.አ.አ. በ1948 የተመሰረተች ሲሆን ከጊዜያት በኋላ ወደ አነስተኛ የጸሎት ቤትነት በመቀየር በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እናት የተሰየመች ትንሽ ቤተ ክርስቲያን ነበረች።

ከዚያም በ1952 የኩዌት ኦይል ኩባንያ በከተማው ውስጥ አዲስ ቤተ ክርስቲያን እንዲገነባ ፈቃድ በመስጠቱ እ.አ.አ. መስከረም 8 ቀን 1955 በርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፒየስ 12ኛ የተባረከ የመጀመሪያው የመሠረት ድንጋይ ተቀመጠ።

አዲሷ ቤተ ክርስቲያን ‘አዎር ሌዲ ኦፍ አረቢያ’ በመባል የተቀደሰችው በሚያዝያ ወር 1956 ዓ.ም. እንደሆነም ይታወቃል።

የቅድስት መንበር እና ኩዌት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት

ኩዌት እ.አ.አ በ1968 ከቅድስት መንበር ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በመመሥረት ከባህረ ሰላጤው የትብብር ምክር ቤት አባላት ውስጥ የመጀመሪያዋ ሃገር ነበረች።

ሆኖም ግንኙነቱን ለማጠናከር እና የሃይማኖቶች ውይይትን ለማስፋፋት ተብሎ ሐዋርያዊ ቢሮ በሀገሪቱ የተቋቋመው እ.አ.አ በ2000 ዓ.ም. እንደሆነ ተነግሯል።
 

07 December 2023, 14:09