ፈልግ

 ታህሳስ 17 ምሽት ላይ  እስራኤል በደቡብ ሊባኖስ በሚገኘው ቢንት ጀቢል ውስጥ ያደረሰችውን የቦምብ ድብደባ ተከትሎ በፈራረሰው ስፍራ ሰዎች ፍርስራሹን ሲፈትሹ ታህሳስ 17 ምሽት ላይ እስራኤል በደቡብ ሊባኖስ በሚገኘው ቢንት ጀቢል ውስጥ ያደረሰችውን የቦምብ ድብደባ ተከትሎ በፈራረሰው ስፍራ ሰዎች ፍርስራሹን ሲፈትሹ  (AFP or licensors)

የሂዝቦላህ እና የእስራኤል ግጭት በሺዎች የሚቆጠሩ ክርስቲያኖችን ከደቡብ ሊባኖስ አፈናቅሏል ተባለ

በደቡብ ሊባኖስ በሚገኙ የክርስቲያን መንደሮች ውስጥ ከሚኖሩት ክርስቲያኖች እስከ 90 በመቶ የሚደርሰው ህዝብ ከጥቅምት ወር ጀምሮ በእስራኤል-ሊባኖስ ድንበር ላይ በየቀኑ በሚደረገው የሮኬት ተኩስ ልውውጥ ለማምለጥ ሲሉ ቤታቸውን ለቀው እንደወጡ ተነግሯል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

በደቡብ ሊባኖስ አዋሳኝ መንደሮች የሚኖሩ ክርስቲያኖች በዚህ ዓመት ወደ ሊባኖስ ግዛት ወደተስፋፋው የጋዛ ጦርነት ጥላ ስር ሆነው በጣም የደበዘዘ የገና በዓል አክብረዋል።

የእስራኤል እና የሐማስ ጦርነት ከተቀሰቀሰበት ከመስከረም 26 ጀምሮ የሊባኖስ የሺዓ ታጣቂ ቡድን ሒዝቦላህ እና የእስራኤል ጦር ሁለቱንም ሃገራት በሚያዋስኑ ድንበር አከባቢ በየቀኑ በሚያደርጉት የተኩስ ልውውጥ እስካሁን በሊባኖስ በኩል 159 ሰዎች መሞታቸው የተዘገበ ሲሆን፥ ከነዚህም ውስጥ አብዛኞቹ የሂዝቦላህ ታጣቂዎች እና ተባባሪ ቡድኖቻቸው እንደሆኑ እና ቀሪዎቹ ቢያንስ 17 ሰላማዊ ሰዎች እንደሆኑ ተገልጿል።

የእስራኤል ጦር “ናስር” ተብሎ የሚታወቀውን ሁሴን ኢብራሂም ሳላሜህን ጨምሮ ስድስት የሂዝቦላህ ተዋጊዎችን ከገደለ በኋላ ግጭቱ ወደ አጠቃላይ ጦርነት ሊሸጋገር ይችላል የሚለው ፍራቻ ከቅርብ ቀናት ወዲህ እየተባባሰ መምጣቱ ተነግሯል።

የክርስቲያን መንደሮች በተባራሪ ተኩሶች መመታታቸው 

የእስራኤል ጥቃቶች በአብዛኛው የሺዓ አካባቢዎች ላይ ባሉ የሂዝቦላህ ታጣቂዎች ላይ ኢላማውን ያደረገ ቢሆንም፥ በርካታ የክርስቲያን መንደሮችም የግጭቱ ሰለባ በመሆን ጉዳት እንደደረሰባቸው እና ብዙ ቤተሰቦች ወደ ሰሜን እንዲሰደዱ አስገድዷቸዋል ተብሏል።

ለተጎዱ ሰዎች ድጋፍ የሚያደርገው የቤተክርስቲያን የዕርዳታ ድርጅት የሆነው ኤ.ሲ.ኤን የተባለው ጳጳሳዊ ተቋም ባሰባሰበው መረጃ መሰረት በጣም ከተጎዱት መንደሮች መካከል አልማ አልሻአብ በተባለው መንደር 15 ቤቶች በሚሳኤል መውደማቸውን ገልጿል።

በቤይሩት ያሉ ክርስቲያን ቤተሰቦች ለተፈናቀሉ ቤተሰቦች የመጠለያ ቦታ ቢያቀርቡም፥ ከተሰደዱት መካከል ጥቂቶቹ በሌሎች የሀገሪቱ ክፍሎች ለረጅም ጊዜ የሚቆይ መጠለያ እጥረት ስላጋጠማቸው ወደ ቀያቸው ተመልሰዋል።

በሊባኖስ የኤ.ሲ.ኤን የፕሮጀክቶች ኃላፊ የሆኑት ዣቪየር ስቴፈን ቢሲት የብዙ ቤተሰቦች መተዳደሪያ የነበሩ አንዳንድ የእርሻ መስኮችም በግጭቱ ምክንያት በመውደማቸው፥ ቀድሞውኑ በሊባኖስ ዘላቂነት ባለው የኢኮኖሚ እና የገንዘብ ቀውስ ሳቢያ ድሆች በነበሩ የበርካታ ቤተሰቦች ኑሮ ላይ ተፅእኖ ማሳደሩን ዘግበዋል።

አቶ ዣቪየር እንደተናገሩት ሁሉም ካህናቶች እና መነኮሳት በጣም ያረጁ ወይም ወደ ሌላ ቦታ ለመዛወር አቅም የሌላቸውን ሰዎች ለማገልገል በየመንደሩ ለመቆየት መወሰናቸውን ጠቁመዋል። ሃላፊው አክለውም የጢሮስ ማሮኒቴ ጳጳስ በቅርቡ በድንበር ላይ በምትገኘው ሪሚች መንደር በቦምብ ጥቃት ጥላ ሥር ሆነው የገናን መስዋዕተ ቅዳሴን እንዳከበሩ እና በድንበር አካባቢ የሚገኙትን ምእመናን ለማየት ጉብኝት ማድረጋቸውን በመግለፅ፥ “ይህ በዚህ ክልል ውስጥ ያሉ ህዝቦችን ጠንካራ እምነት እና ፅናት የሚያሳይ ነው” ብለዋል።

ጦርነቱ ወደ ሊባኖስ የመስፋፋት ስጋት

አቶ ዣቪየር ጦርነቱ እየተባባሰ መምጣቱን ካረጋገጡ በኋላ፥ አሁን ያለው ግጭት እ.አ.አ. በ2006 በእስራኤል እና በሄዝቦላህ መሃል የተደረግውን ጦርነትን ያስታውሰናል ብለዋል።

የአካባቢው የሀይማኖት መሪዎች የቤተክርስቲያን ዕርዳታ ድርጅት ለሆነው ኤ.ሲ.ኤን እንደተናገሩት ሌላ ጦርነት ከተከሰተ በአካባቢው ላለው ታሪካዊ የክርስቲያን መገኘት ትልቅ ስጋት ይሆናል ብለዋል። ኤ.ሲ.ኤን በደቡብ ሊባኖስ ውስጥ በሚገኙ የካቶሊክ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ላሉ ተማሪዎች የምግብ ፓኬጆችን፣ የሕክምና ዕርዳታን እና የኦንላይን ትምህርት እንዲያገኙ እየረዳ እንደሚገኝም ተገልጿል።

ፓትርያርክ በቻራ አልራሂ ሊባኖስ ገለልተኛ እንድትሆን ተማጽነዋል

በሂዝቦላህ እና በእስራኤል ጦር መካከል እየተደረገ ያለው ጦርነት እየተባባሰ ባለበት በአሁኑ ወቅት የማሮኒት ፓትርያርክ ካርዲናል ቤቻራ አልራሂ የገና በዓል ሥነ ስርዓት ላይ ደጋግመው እንደተናገሩት ሊባኖስ ገለልተኛ እንድትሆን በመማጸን፥ “ጦርነቱ ወደ ደቡብ መንደሮች እንዲስፋፋ መፍቀድ ዬለብንም” ሲሉ ፓትርያርኩ በገና ስብከታቸው ላይ ተናግረዋል። “ሊባኖስ የጦርነት ምድር ሳትሆን የውይይት እና የሰላም ምድር ነች” በማለትም አሳስበዋል።

ብፁዕ ካርዲናል ቤቻራ አልራሂ በጋዛ ስለተገደሉት ሰዎች በማውገዝ፥ ጦርነቱ ወደ ሊባኖስ መስፋፋቱ እ.አ.አ. በ2006 በእስራኤልና ሂዝቦላ መካከል የተደረገውን ጦርነትን ለማስቆም ከወጣው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ውሳኔ 1701 እና የሊባኖስ ገለልተኝነት በመካከለኛው ምስራቅ ክልል ውስጥ ያሉትን ክስተቶች በተመለከተ ከፀደቀው የ2012ቱ ‘ባብዳ ዴክላሬሽን’ ጋር የሚቃረን መሆኑን አስታውሰዋል።

ይህንንም አስመልክተው ፓትሪያርኩ ሃሳባቸውን ሲያጠቃልሉ “እ.አ.አ. ከ 1860 ጀምሮ የሊባኖስ ገለልተኝነት የሊባኖስ ማንነት ዋና መለያ አካል ሆኖ የቆየ ሲሆን፥ ውጊያን ከሚያስነሱ ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይም ገለልተኛ ናት” ብለዋል።
 

28 December 2023, 12:57