ፈልግ

በፒተር ፖል ሩበንስ የተሳለ 'የእረኞች አምልኮ' የተሰኘው ሥዕል - ከፌርሞ አርት ጋለሪ በፒተር ፖል ሩበንስ የተሳለ 'የእረኞች አምልኮ' የተሰኘው ሥዕል - ከፌርሞ አርት ጋለሪ 

የፐርዙ ሊቀ ጳጳስ 'በኢየሱስ ማን እንድንሆን እንደተጠራን አይተናል' አ

የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መወለድ በፍርሀት እና ጥርጣሬ ጥላ በጨለመበት ዓለም ውስጥ በጣም ትልቅ የተስፋ ምልክት እና መልእክት ነው። ለዘንድሮው የገና በዓል የቫቲካን ረዲዮ የሃይማኖት መሪዎች እና የክርስቲያን በጎ አድራጎት ድርጅቶች ኃላፊዎችን “የጌታ ልደት የሰላም ልደት ነው” በሚል መሪ ቃል ላይ አስተያየታቸውን እንዲሰጡ ጠይቋል። የዛሬው መልእክት የመጣው ከአውስትራልያ የካቶሊክ ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዝዳንት ከሆኑት የፐርዝ ሊቀ ጳጳስ ጢሞቴዎስ ኮስቴሎ ነው፥ እንደሚከተለው ይቀርባል፦

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

                              የሊቀ ጳጳስ ጢሞቴዎስ ኮስቴሎ የገና መልእክት
               የፐርዝ ሊቀ ጳጳስ እና የአውስትራሊያ የካቶሊክ ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዝዳንት

በክርስቶስ የተከበራችሁ ወንድሞች እና እህቶች፣
ከታዋቂው የገና መዝሙሮቻችን አንዱ በነዚህ ቃላት ይጀምራል፡

ይህ በማርያም ጭን ላይ ያረፈው/ የሚተኛው ልጅ ማን ነው? በጣም በፍጥነት፣ መዝሙሩ ወደ መልስ ይሸጋገራል፡ ይህ፣ ይህ፣ ክርስቶስ ንጉስ/ሕፃኑ፣ የማርያም ልጅ ነው።

በየዓመቱ፣ የገና በዓል ሲመጣ፣ ይህንኑ ጥያቄ እንድንጠይቅ ተጋብዘናል - ይህ ልጅ ማነው? - በአእምሯችን እና በልባችን ውስጥ ይህ ጥያቄ ይነሳል፥ በሚመለሱት መልሶች ላይ እንድናሰላስል ይጋብዘናል።

ጥያቄው ለእኛ እጅግ አስፈላጊ ከሆኑት ውስጥ አንዱ ጥያቄ ነው። በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዘንድም ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ጉዳይ ነው። ኢየሱስ ለሐዋርያቱ፡- እኔን ማን ብላችሁ ትጠሩኛላችሁ? ብሎ የጠየቀበትን ጊዜ ታስታውሳላችሁ።

የአሥራ ሁለቱ ሐዋርያት መሪ ስምዖን ጴጥሮስ ለኢየሱስ ሲመልስ “አንተ ክርስቶስ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ነህ” አለው። ለገና በዓል ጊዜ ከተዘመረው መዝሙር ውስጥ ከተሰጠው ምላሽ ጋር የሚመሳሰል መልስ ነው። የክርስትና እምነት መሰረት የነበረው እና አሁንም የሆነው ተመሳሳይ መልስ ነው። ኢየሱስ በእኛ መሃከል የሚገኝ ጌታ ነው። እርስ በርሳችን እንደምንደራረሰው ሁሉ፥ እሱ ሰው በመሆን ወደ እኛ በመምጣት ለእኛ ተደራሽ ሆነ። እሱን ልናውቀው እንችላለን፥ እኛ እርስ በርሳችን እንደተዋወቅን ስለ እርሱ ባለን እውቀት ማደግ እንችላለን። እንዲሁም ልክ ለልባችን ቅርብ ለሆኑት ሰዎች ፍቅራችንን ማጠናከር እንደምንችለው ሁሉ እሱን መውደድ እንችላለን፥ ለእርሱ ባለን ፍቅር ማደግ እንችላለን።

ነገር ግን ኢየሱስ በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ ልዩ ቦታ አለው፥ በእምነት አይን እና ጆሮ ብንመለከት እና ብንሰማ ሰውነቱ አምላክነቱን ይደብቃል እንዲሁም ይገልጣል፥ እርሱን በማወቅ እግዚአብሔርን ማወቅ እንችላለን። ኢየሱስ ራሱ እንዲህ ብሏል። በአንድ ወቅት ከሐዋርያቱ ለአንዱ “እኔን ማየት አብን ማየት ነው” ሲል ተናግሯል። በተለይ በወንጌል ገፆች ውስጥ ሲናገር ስንሰማ የእግዚአብሔርን ቃል እና ድምፅ እየሰማን መሆኑን ያረጋግጥልናል። ለሰዎች ተስፋ እና ፈውስ ሲያመጣ ስናይ፣ በተግባር ለእግዚአብሔር ርህራሄ ምስክሮች ነን። ከሰዎች ጋር ባደረገው ግንኙነት ሁሉ፣ እግዚአብሔር በእውነት ማን እንደ ሆነ፣ እና እግዚአብሔር በህይወታችን ውስጥ ለማድረግ እና ለመሆን የሚፈልገውን ማስተዋል እየተሰጠን ነው።

ለዚህ ነው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱን እኔ መንገድ እና እውነት እንዲሁም ህይወት ነኝ ብሎ ማወጅ የቻለው። ከብዙ መንገዶች አንደኛው ብቻ ሳይሆን የእግዚአብሔር መንገድ ነው፥ አንዱን እውነት ከሌሎች ጋር የምናወዳድረው ብቻ ሳይሆን የእግዚአብሔር እውነት ነው፥ ለሕይወት አንድ አማራጭ ብቻ ሳይሆን ሕይወት ራሱ እሱ ነው፣ መለኮታዊ ሕይወት፣ እንደ ስጦታ የቀረበልን ህይወት ነው።

የኛ የአይሁድ-ክርስቲያን ባህልና ልምዶች በእግዚአብሔር መልክ እና አምሳል መፈጠርን የያዘ በጥልቅ እምነት ላይ ያረፈ ነው። ይህ እውነት ፍጹም ሰው ፍጹም አምላክ በሆነው በኢየሱስ ክርስቶስ ውስጥ ከፍ ያለ አገላለጽ ላይ ደርሷል። በእርሱ ውስጥ በማን እና ለምን እንደተፈጠርን እና ምን እንድንሆን እንደተጠራን እናያለን፥ በእርሱ ውስጥ በህይወታችን ጉዞ ላይ ጓደኛ እናገኛለን፣ ከፈቀድንለት የተጠራነው ማን እና ምን መሆን እንድንችል ያስችለናል።

በዚህ የገና በዓል ልክ እንደሌሎቹ የገና በዓላት፣ በኢየሱስ በኩል እውነተኛ እና ተጨባጭ የሆነውን፣ በደከመን እና ሸክም በበዛብን ጊዜ ወደ እርሱ እንድንመጣ እና እረፍታችንን በእርሱ እንድናገኝ የእግዚአብሔርን ጥሪ በድጋሚ እንድንሰማ ተጋብዘናል፥ በአንድ ወቅት በጨለማ ከተመላለሱት እና አሁን ግን በብርሃን ከሚመላለሱት ሰዎች ጋር እንድንኖር፥ እርሱ ከእኛ ጋር ስለሆነ እንዳንፈራ የሚነግረንን የድምፁን ማሚቶ በውስጣችን እንድንሰማ ለመፍቀድ እንድንችል ተጋብዘናል።

ይህ በማርያም ጭን ላይ ተቀምጦ የሚተኛ ልጅ ማን ነው?
ይህ እርሱ ክርስቶስ ጌታ ነው - ኑ እንስገድለት።

ይህ ጊዜ ጥልቅ የደስታ፣ የእርቅ እና የሰላም ጊዜ ይሁንላችሁ። እንዲሁም መጪው ጊዜ ለእናንተ፣ ለቤተሰቦቻችሁ እና ለምትወዷቸው ሁሉ አስደሳች የሆነ የተስፋ ጊዜ ይሁን። መልካም እና የተቀደሰ የገና በዓል ለሁላችሁ።

+ሊቀ ጳጳስ ጢሞቴዎስ ኮስቴሎ
     የፐርዝ ሊቀ ጳጳስ
 

26 December 2023, 15:53