ፈልግ

ብፁዕ ካርዲናል ፒዛባላ በቤተልሔም በሚገኝ ቤተ ክርስቲያን - እሁድ ታህሳስ 14 ቀን 2016 ዓ.ም. ብፁዕ ካርዲናል ፒዛባላ በቤተልሔም በሚገኝ ቤተ ክርስቲያን - እሁድ ታህሳስ 14 ቀን 2016 ዓ.ም.  (AFP or licensors)

ብፁዕ ካርዲናል ፒዛባላ ጦርነቱ እንዲያበቃ እና ውይይቱ እንዲሳካ እጸልያለው አሉ

በኢየሩሳሌም የላቲን ሥርዓተ አምልኮን የምትከተል ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ካርዲናል ፒየርባቲስታ ፒዛባላ ለቫቲካን ዜና እና ለ ላ’ኦዘርቫቶሬ ሮማኖ ብቻ በላኩት የገና መልእክት፥ ሥጋ ለብሶ በመካከላችን ያደረውን አምላክ ትርጉም ባሰብን ቁጥር እርስ በርሳችን እንደ ወንድማማቾች እና እህትማማቾች እንድንተሳሰብ ጥሪ ካቀረቡ በኋላ፥ በመካከላችን ውይይት፣ እርቅ፣ ይቅርታ እና ወዳጅነት እንዲኖር አሳስበው፥ “አድማሱን መመልከት እና የእግዚአብሔር ስራ ሲሰራ ማየት” ያስፈልጋል ብለዋል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተወለደበት ምድር ከቆሰለው ልብ ውስጥ የተላለፈው የብፁዕ ካርዲናል ፒየርባቲስታ ፒዛባላ የገና መልእክት ለቫቲካን ዜና እና ለላኦዘርቫቶሬ ሮማኖ የተሰጠው መልዕክቱን እንዲያካፍሉት ታስቦ እንደሆነም ተገልጿል።

የጥላቻ ባህር ውስጥ መዘፈቅ

የብፁዕ ካርዲናል ፒዛባላ ሐሳብ የሚጀምረው ምድራችንን የተቆጣጠረ የሚመስለውን የግጭቶች መበራከት እና አሁን በቅድስት ምድር ምን እየተከናወነ እንደሆነ ግምት ውስጥ በማስገባት ነው። ለቫቲካን መገናኛ ብዙሀን በጣሊያንኛ በላኩት የቪዲዮ መልዕክታቸው ላይ “ዓለም ሁሉ ዓመፅ፣ ጥላቻ፣ መለያየት፣ የበቀል ስሜት የሰፈነበት ታላቅ የመከራ ጊዜ ላይ ያለ ይመስላል” ብለዋል።

ፓትርያርኩ “በሰሜን አውሮፓ” ስላለው ሁኔታ ስጋታቸውን ከገለጹ በኋላ በመካከለኛው ምስራቅ እየተከናወነ ባለው ነገር ላይ በማተኮር፥ “ከመስከረም 26 ጀምሮ በጥላቻ፣ ቂም በቀል እና የሞት ባህር ውስጥ ተዘፍቀናል” ካሉ በኋላ፥ “የጥላቻ ስሜት ሁለቱንም የእስራኤል እና የፍልስጤም ማህበረሰብን እየጎዳ ነው” በማለት ብጹዕ ካርዲናሉ ገልጸዋል። ከምንም በላይ በጋዛ ውስጥ እየተከሰቱ ያሉት ነገሮች ልባቸውን እንደሚነካ ቢናገሩም፥ ነገር ግን “በቤተልሔም የሚገኙትን በቁጥር አናሳ የሆኑትን የክርስቲያን ማኅበረሰብንም” እንደሚያስታውሱ ገልጸዋል።

ለእግዚአብሔር እሺ ማለት ዕርቅን መቀበል ነው

ብፁዕ ካርዲናል ፒዛባላ “እያንዳንዱ ሰው በእራሱ መከራ ውስጥ ታጥሮ ያለበትን በጣም አስቸጋሪ ሁኔታዎች” መገንዘብ እንደሚያስፈልግ ከገለፁ በኋላ “እግዚአብሔር ወደ እኛ ይመጣል፣ ራሱን ለእኛ ያቀርባል እንዲሁም ከሌላው ሰው ጋር ጥሩ ግንኙነት እንዲኖረን እና እሱም የህይወታችን አንድ አስፈላጊ አካል አድርገን እውቅና እንድንሰጥ ልባችንን ይከፍታል” በማለት የገናን የጎላ ጠቀሜታ እና ትርጉም አጽንኦት ሰጥተው ገልጸዋል።

ይህ ትርጉም ገና ካለው በርካታ ጥቅሞች አንፃር እንድናየው እንደሚረዳን ከጠቀሱ በኋላ “እነዚህ ሁሉ አሰቃቂ ግጭቶች ቢኖሩም የገና በዓል ለእኛ የሚያስተላልፈው መልዕክት ሁሌም እንደሚኖር መዘንጋት የለብንም፥ ምናልባትም በዚህ ወቅት ከመቼውም ጊዜ በበለጠ አስፈላጊ ነው። እግዚአብሔር ለኛ ካለው ጥልቅ ፍቅር የተነሣ ሥጋ ለብሶ መጥቷል፥ ለእኛ ባለው ፍቅር ሕይወቱን እስከመስጠት ደርሶ፥ በዓለም ላይ ከሌሎች ጋር የምንኖርበትን አዲስ መንገድ አሳይቶናል” ብለዋል።

ብጹእ ካርዲናል ፒዛባላ አክለውም የመሳሪያ ጋጋታ ምንም ሊቀይር እንደማይችል ሲያስረዱ “ለእግዚአብሔር የሚታዘዙ፣ ለወንድሞቻቸው እና እህቶቻቸው የሚታዘዙ ሰዎች በሞሉባት በቅድስት ሀገርም የገና በዓል ነው። ምክንያቱም ለእግዚአብሔርን እሺ ማለት ወይም መታዘዝ ለሌላውም እውቅና መስጠት ነው፣ ለሌሎች ወንድሞቻችን ወይም እህቶቻችን መታዘዝ ማለት ነው፥ ይህም ሲሆን ለውይይት ክፍት ለመሆን ፍቃደኞች ይሆናሉ፥ ለእርቅ እሺ ለማለት፣ ይቅር ለመባባል ፍቃደኛ ለመሆን እና ወዳጅነትን ለማጠናከር ይታዘዛሉ ማለት ነው” በማለት አጽንዖት ሰጥተው ተናግረዋል።

አሁን ካለው መከራ አሻግሮ የእግዚአብሄርን ስራ ማየት

በዚህ የከበረ ቀን ፓትርያርኩ በመጀመሪያ የአካባቢያቸውን የምዕመናን አባላትን እንደሚያነጋግሩ፥ ነገር ግን ይህንን መልእክት ለሚሰሙ ሁሉ እና “ወደዚህች ስፍራ ወደ ቅድስት ሀገር ለሚመለከቱ” ሁሉ መልዕክታቸውን እንደሚያስተላልፉ ገልጸዋል። ረጅም የመከራ ጊዜ ቢሆንም ቀጣይነት ያለው ጥሪ ጌታ እንደማይተው በእርግጠኝነት ፀንተው በሚያምኑ ሰዎች እንደሚገለጽም አረጋግጠዋል።

ብጹእ ካርዲናል ፒዛባላ ሲያጥቃልሉ “አሁን ከሚደርስብን ሥቃይ አሻግረን የእግዚአብሔርን ድንቅ ሥራ ለማየት ዓይኖቻችንን ቀና ማድረግ አለብን፥ ምክንያቱም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በእውነት ይህ የሚወለደው ሕፃን ስለሆነ፣ የእያንዳንዳችን የግል ታሪክ ባለቤት እና የዓለም ታሪክ ጌታ ስለሆነ ነው” ብለዋል።

ይህ ሁሉ ስቃይ ቢደርስብንም “እናምነዋለን” ብለን የምናውጅበት ጊዜ ነው። ዛሬ የገና በዓል ነው ሲሉ ብፁዕ ካርዲናል ፒዛባላ ካወጁ በኋላ፥ ሁሉም ሰው ተመሳሳይ መልእክት እንዲያውጅ አጥብቀው በማሳሰብ በሁሉም ላይ የእግዚአብሔርን በረከት እንዲወርድ ተመኝተዋል።
 

25 December 2023, 13:54