ፈልግ

PALESTINIAN-ISRAEL-CONFLICT PALESTINIAN-ISRAEL-CONFLICT  (AFP or licensors)

የጋዛ ነዋሪዎች አስቸኳይ እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው ‘ካፎድ’ የተባለው ተቋም አስታወቀ

ካፎድ (CAFOD እ.አ.አ. በ 1960 የተቋቋመ ዓለም አቀፍ ድንበር ተሻጋሪ የልማት በጎ አድራጎት ድርጅት ሲሆን በእንግሊዝ እና በዌልስ የሚገኙ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ኦፊሴላዊ የእርዳታ ኤጀንሲ ነው) አስቸኳይ የተኩስ አቁም ጥሪውን በድጋሚ ያቀረበ ሲሆን፥ ሰዎች በረሃብ እና በብርድ እየተሰቃዩ ባሉበት እና ከጠቅላላው ህዝብ ግማሽ ያህሉ የተፈናቀሉበት እና ብዙ መዘዝ ባስከተለው ጦርነት ምክንያት የጋዛን ህዝብ ለመርዳት የሚያስችል ዘመቻ ጀምሯል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

በእንግሊዝ እና በዌልስ የሚገኘው የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ይፋዊ የእርዳታ ኤጀንሲ (CAFOD) ለጋዛ ህዝብ ሲባል አስቸኳይ የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረግ እና እርዳታ በተጠናከረ ሁኔታ እንዲሰጥ ጥሪውን በድጋሚ አስተላልፏል።

የመካከለኛው ምሥራቅ የካፎድ አገር አቀፍ ፕሮግራሞች ተወካይ የሆኑት ወ/ሮ ኤልሳቤት ፉኔል ለቫቲካን ዜና እንደተናገሩት “መድኃኒቶች እንፈልጋለን፣ ነዳጅ፣ ምግብ እና ውሃ በጣም ይፈለጋሉ” ብለዋል።

ካፎድ የእስራኤል-ፍልስጤም ጦርነት እንዲያበቃ ያስተላለፈው ድንገተኛ ጥሪ፥ በጋዛ ውስጥ ያሉ ሰዎች የሚያጋጥማቸው ሰብአዊ ሁኔታ ከጊዜ ወደ ጊዜ ተስፋ አስቆራጭ እየሆነ በመምጣቱ እና በሰባት ቀናቱ የተኩስ አቁም ጊዜያት ወደ ጋዛ የገቡት አቅርቦቶች እያለቀ በመምጣቱ ነው ተብሏል።

ጦርነቱ እንደገና ከተጀመረበት ከኅዳር 21 ጀምሮ “ሁኔታው በጣም በፍጥነት እየከፉ ነው” ሲሉ ወ/ሮ ኤልሳቤት ፉንኔል ተናግረዋል። አክለውም “ሰዎች በጣም ተዳክመዋል፣ ተርበዋል፤ በተጨማሪም ሰዎች እንዴት እንደሆኑ እና የት እንዳሉ መረጃ ማግኘት በጣም ከባድ ነው” ብለዋል።

“ሰዎች ተዳክመዋል፣ ተርበዋል፤ በተጨማሪም ሰዎች እንዴት እንደሆኑ እና የት እንዳሉ መረጃ ለማግኘት በጣም አስቸጋሪ ነው”

በጋዛ ከተማ በሚገኘው የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ቅጥር ግቢ ውስጥ የተጠለሉ ሰዎች “እንደ ምግብ እና ውሃ ያሉ መሠረታዊ ነገሮች በጣም ይፈልጋሉ፥ እነዚህን መሠረታዊ ነገሮች ለማግኘት እየተካሄደ ያለው ጦርነት በጣም ከባድ ስለሆነ ወደ ውጭ ለመውጣት ይፈራሉ” ሲሉም ገልጸዋል።

እስካሁን ድረስ ወደ ጋዛ መግባት የቻሉት አቅርቦቶች “በውቅያኖስ ላይ እንደተጨመረች ጠብታ ናት” ሲሉ ወ/ሮ ኤልሳቤት ፉንኔል ከገለጹ በኋላ የዕርዳታ አቅርቦቱን መጨመር እጅግ አስፈላጊ መሆኑንም አክለዋል።

ነዳጅ በጣም አስፈላጊ ነው

የምግብ፣ ውሃ እና ነዳጅ እጥረት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ እንደሆነ እና በማሞቂያ መሳሪያ ውስጥ ያሉ ያለጊዜ የተወለዱ ሕፃናትን ህይወት ለማዳን በሆስፒታሎች ውስጥ ለሚገኙ የኃይል ማመንጫዎች ነዳጅ በጣም አስፈላጊ እንደሆነ ተገልጿል። በተጨማሪም የውሃ ማጣሪያ ማሽኖቹን ለማንቀሳቀስም ነዳጅ ወሳኝ እንደሆነ ተነግሯል።

                               “በጣም አስፈላጊ አገልግሎቶችን ለማስቀጠል ነዳጅ ያስፈልጋል”

“እቃዎች ከግብፅ ወደ ጋዛ ሰርጥ መግባት ቢችሉም ለጭነት መኪናዎች የሚሆን ነዳጅ ከሌለ እቃዎቹ ለተረጂዎቹ ሊከፋፈሉ አይችሉም” ሲሉ ሃላፊዋ ገልጸዋል።

ለመሠረታዊ ፍላጎቶች ምላሽ የሚሰጡ የአካባቢ አጋሮች

ካፎድ ጋዛ ውስጥ በግጭቱ የተጎዱትን ለመድረስ ከአካባቢው አጋሮች ጋር በቅርበት እየሰራ እንደሚገኝ፥ እንዲሁም ምንም እንኳን አደጋው ከባድ ቢሆንም ይህ ችግር ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ የእርዳታ ሠራተኞች የህዝቡን ፍላጎት ለመመለስ ሲሉ እየታገሉ እንደሚገኙ ተገልጿል።

ከህዳር 14 እስከ ህዳር 21 ባለው ጊዜያዊ የተኩስ አቁም ስምምነት ወቅት ከተንቀሳቃሽ የህክምና ቡድኖች ጋር በመሆን አስቸኳይ የህክምና እርዳታን በደቡብ የጋዛ ክፍል ለማድረስ ችለዋል። እንዲሁም ሰዎች ወደ አካባቢው ገበያ ሄደው ያለውን ሁሉ እንዲገዙ የገንዘብ ድጋፍ አድርገዋል።

የካፎድ አጋሮች አሁንም ድረስ ለተጎጂዎቹ በጣም የሚያስፈልጋቸውን ነገር በማድረስ የተለያዩ ሥራዎችን እየሰሩ እንደሚገኙ እና “አስቸጋሪ ሁኔታዎች ቢኖሩም አስደናቂ ብልሃትን እና ጽናትን እያሳዩ ነው” ብለዋል ወ/ሮ ኤልሳቤት።

የካፎድ ተወካይዋ ሰዎች ወደ ካፎድ የአደጋ ጊዜ ጥሪ ድህረ ገጽ ገብተው በጣም አስፈላጊ የሆነውን የገንዘብ ድጋፍ እንዲለግሱ በመጋበዝ፥ “ሰዎች መስጠት ከቻሉ ገንዘባቸው በጋዛ ውስጥ ያሉ የተቸገሩ ሰዎችን ለመደገፍ በጥሩ ሁኔታ ጥቅም ላይ ይውላል” ብለዋል።

የአየሩ ሁኔታ በጣም ቀዝቃዛማ እየሆነ ነው

ወ/ሮ ኤልሳቤት በአሁኑ ወቅት የጋዛ የአየር ንብርት ቀዝቃዛማ እና እርጥበታማ እየሆነ መምጣቱን ጠቁመው “በዚህ ዓመት በጋዛ ውስጥ ነበርኩ እናም ብዙ ጊዜ ጎርፍ ያጋጥማል፥ ስለዚህ ሰዎች በቦንቡ ድብደባ የፈራረሱ ሕንፃዎችን ለመሸፈን እነዚያን የመጠለያ ዕቃዎች ማለትም ድንኳኖችን እና ንጣፎችን በጣሙኑ ይፈልጋሉ” ብለዋል።

በአከባቢው ላይ ያሉት የካፎድ አጋሮች እነዚህን ነገሮች መግዛትና ማከፋፈል እንደቻሉ፥ “ነገር ግን በጋዛ ውስጥ ያሉት እቃዎች እያለቁ ስለሆነ የበለጠ አስቸጋሪ እየሆነ መጥቷል” ሲሉም የጉዳዩን አሳሳቢነት ተናግረዋል።

                                                 'በጋዛ ውስጥ የነበሩ እቃዎች እያለቁ ነው'

የተላላፊ በሽታዎች ስጋት

ጦርነቱ ከጀመረ ሶስተኛ ወሩን የያዘ ሲሆን፥ እስካሁን ከ18,000 በላይ ፍልስጤማውያን እና 1,400 እስራኤላውያን እንደተገደሉ፣ በሺዎች የሚቆጠሩት እንደቆሰሉ እና ከ1.9 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ደግሞ እንደተፈናቀሉም ለማወቅ ተችሏል።

የሰዎችን በተደጋጋሚ የመፈናቀል ሁኔታ ሲገልፁ፥ “ጥቃት እንደሚደርስባቸው ሲነገራቸው ተፈናቅለው ካረፉባቸው አካባቢዎች በድጋሚ ምንም ደህንነቱ የተጠበቀ ቦታ ሳይኖራቸው ለመፈናቀል ይገደዳሉ” ሲሉ ሃላፊዋ ገልጸዋል።

“ከጋዛ ህዝብ ግማሽ ያህሉ የሚኖረው በደቡባዊ ጋዛ ራፋህ በተባለ አካባቢ ብቻ እንደሚኖር እና ይህ አከባቢ ቀድሞውንም በዓለም ላይ በጣም ብዙ ሰዎች ከሚኖሩባቸው አካባቢዎች አንዱ ነው” ብለዋል።

                                    "ከጋዛ ህዝብ ግማሽ ያህሉ የሚኖረው በአንድ አካባቢ ብቻ ነው"

እንደዚህ ባሉ የተጨናነቁ ሁኔታዎች ለሰው ልጅ አስፈላጊ የሆኑ ነገሮች ሳይኖሩ የንጽህና ደረጃዎችን መጠበቅ ከባድ እንደሆነ ይታወቃል።

“እንደ የዓለም ጤና ድርጅት ያሉ ድርጅቶች የሚከሰተው በሽታ በጦርነቱ ከሚሞቱ ሰዎች ይበልጥ ብዙ ሰዎችን ሊገድል እንደሚችል ያላቸው ስጋት እየጨመረ ነው” ሲሉ ወ/ሮ ኤልሳቤት ተናግረዋል።

የገና ስጦታዎች ለጋዛ ሰዎች

በመጪዎቹ የገና በዓል ሳምንታት፥ ሰላም የሚፈልጉ ሰዎችን ለመርዳት፣ በጋዛ ውስጥ የሚሰቃዩ ሰዎችን ለመርዳት፥ በጸሎትም ይሁን፣ በጥሪ ወይም በመዋጮ ለመርዳት የሚቻሉባቸው መንገዶች እንዳሉም ተናግረዋል። ጋዛ ውስጥ ያሉ የካፎድ አጋሮች “ስለወደፊቱ ሁኔታ ስጋት እንደገባቸው እና የልጆቻቸውን ሰላማዊ የወደፊት ህይወት ለማየት በጣም እንደሚፈልጉ” አፅንዖት ሰጥተው በመናገር፥ ሁሉም ሰው እንዲጸልይላቸው አበረታተዋል።

ወ/ሮ ኤልሳቤት ፉኔል በመጨረሻም “በክልሉ ካሉ የቤተ ክርስቲያናችን አጋሮች ጋር ስነጋገር በጣም የተገለሉ እንደሆኑ እና አንዳንድ ጊዜ እንደተረሱ ሆነው ይሰማቸዋል፥ እናም ሰዎች ለእነሱ እየጸለዩ እንደሆነ ስነግራቸው በጣም ያበረታታቸዋል” ብለዋል።

ካፎድ እንዲደረግ የሚያበረታታው ሌላው ተግባር፥ ዜጎች ለተመረጡት ተወካዮቻቸው ዘላቂ የሆነ የተኩስ አቁም ስምምነትን እንዲደግፉ ወይም የገንዘብ ድጋፍ እዲያደርጉ በመጠየቅ እንዲጽፉ ነው ተብሏል።
 

18 December 2023, 15:53