ፈልግ

Solemnity of Our Lord Jesus Christ, King of the Universe, BAV Arch. Cap. S. Pietro. B. 63, f. 188v

የኅዳር 23/2016 ዓ.ም የ34ኛ እለት ሰንበት ንባባት እና የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ

የኢየሱስ የዓለም ንጉሥ አመታዊ በዓል እና

በአገረ ስብከት ደረጃ የሚከበረው 38 ኛው የዓለም ወጣቶች ቀን ክበረ በዓል

የእለቱ ንባባት

1.      ት.ኢዝቄል 34፡11-12. 15-17

2.     መዝሙር 22

3.     1 ቆሮንጦስ  15፡20-26.28

4.    ማቴዎስ 25፡31-46

የእለቱ ቅዱስ ወንጌል

የመጨረሻው ፍርድ

“የሰው ልጅ ከመላእክቱ ሁሉ ጋር በክብሩ ሲመጣ፣ በክብሩ ዙፋን ላይ ይቀመጣል፤ ሕዝቦች ሁሉ በፊቱ ይሰበሰባሉ፤ እርሱም፣ እረኛ በጎችን ከፍየሎች እንደሚለይ፣ ሕዝቡን አንዱን ከሌላው ይለያል፤ በጎቹን በቀኙ፣ ፍየሎቹን ግን በግራው ያቆማቸዋል። “በዚያን ጊዜ ንጉሡ በቀኙ በኩል ያሉትን እንዲህ ይላቸዋል፤ ‘እናንት አባቴ የባረካችሁ ኑ፤ ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ የተዘጋጀላችሁን መንግሥት ውረሱ፤ ምክንያቱም ተርቤ አብልታችሁኛል፤ ተጠምቼ አጠጥታችሁኛል፤ እንግዳ ሆኜ ተቀብላችሁኛል፤ ታርዤ አልብሳችሁኛል፤ ታምሜ አስታምማችሁኛል፤ ታስሬ ጠይቃችሁኛል።’

“ጻድቃንም መልሰው እንዲህ ይሉታል፤ ‘ጌታ ሆይ፤ ተርበህ አይተን መቼ አበላንህ? ወይም ተጠምተህ አይተን መቼ አጠጣንህ? እንግዳ ሆነህ አይተን መቼ ተቀበልንህ? ወይስ ታርዘህ አይተን መቼ አለበስንህ? እንዲሁም ታምመህ ወይም ታስረህ አይተን መቼ ጠየቅንህ?’ “ንጉሡም መልሶ፣ ‘እውነት እላችኋለሁ፣ ከእነዚህ አነስተኛ ከሆኑት ወንድሞቼ ለአንዱ ያደረጋችሁት፣ ለእኔ እንዳደረጋችሁት ነው’ ይላቸዋል።

“ከዚያም በግራው በኩል ላሉት ደግሞ እንዲህ ይላቸዋል፤ ‘እናንተ የተረገማችሁ፤ ለዲያብሎስና ለመላእክቱ ወደ ተዘጋጀው የዘላለም እሳት ከእኔ ተለይታችሁ ሂዱ፤ ምክንያቱም ተርቤ አላበላችሁኝም፤ ተጠምቼ አላጠጣችሁኝም፤ እንግዳ ሆኜ አልተቀበላችሁኝም፤ ታርዤ አላለበሳችሁኝም፤ ታምሜና ታስሬ አልጠየቃችሁኝም።’ “እነርሱም መልሰው፣ ‘ጌታ ሆይ፤ ተርበህ ወይም ተጠምተህ፣ እንግዳ ሆነህ ወይም ታርዘህ፣ ታመህ ወይም ታስረህ አይተን መቼ አልደረስንልህም’ ይሉታል። “በዚያን ጊዜ እርሱም መልሶ፣ ‘እውነት እላችኋለሁ፣ ከእነዚህ አነስተኛ ከሆኑት ወንድሞቼ ለአንዱ አለማድረጋችሁ፣ ለእኔ እንዳላደረጋችሁት ነው’ ይላቸዋል። “እነዚህም ወደ ዘላለም ፍርድ፣ ጻድቃን ግን ወደ ዘላለም ሕይወት ይሄዳሉ።”

የእለቱ ቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ

የክርስቶስን የሕማማት ታሪክ ከማውጋቱ በፊት ያለውን የማቴዎስ ወንጌል (ማቴ 25፡31-46) ቀደም ሲል አዳምተናል። ኢየሱስ ለእኛ ያለውን ፍቅር በመስቀል ላይ ከመግለጹ በፊት የመጨረሻውን ምኞቱን አካፍሏል። ከታናናሾች ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ለአንዱ - የተራበም ሆነ የተጠማ፣ እንግዳ ለሆነ፣ ለተቸገረ፣ ለታመመ ወይም በእስር ቤት ላለ ወዘተ .... ሰው ማድረግ የሚገባንን መንፈሳዊ ተግባር እና መልካም ሥራ እንድናከናውን ይነግረናል (ማቴ. 25፡31-46)። በዚህ መንገድ ጌታ በሰማይ ከእኛ ጋር ለሚካፈለው ዘላለማዊ የሰርግ ድግስ “የስጦታ ዝርዝሩን” ይሰጠናል። እነዚያ ስጦታዎች ሕይወታችንን ዘላለማዊ የሚያደርጉት የምሕረት ሥራዎች ናቸው። እያንዳንዳችን እንዲህ ብለን መጠየቅ እንችላለን፥ እነዚህን ስራዎች በተግባር እፈጽማቸዋለሁኝ ወይ? ለተቸገረ ሰው የማደርገው ነገር አለ ወይ? ወይስ መልካም የምሠራው ለምወዳቸው እና ለጓደኞቼ ብቻ ነው? ምንም ነገር ሊመልስልኝ የማይችለውን ሰው እረዳለሁ ወይ? የምስኪን ሰው ጓደኛ ነኝ ወይ? እናም ራሳችንን ልንጠይቃቸው የምንችላቸው ሌሎች ብዙ ተመሳሳይ ጥያቄዎች አሉ። “እንደነዚህ ዓይነት ስፍራዎች ውስጥ እገኛለሁ ወይ? ኢየሱስ እንዲህ ይለናል “እዚያ እጠብቅሃለሁ፣ ባታስቡበትም ምናልባትም ምናልባት ማየት ባትፈልጉ፡ እነዚያ ድሆች ውስጥ መገኘት ትችላላችሁ ወይ? “እኔ እዛው ነኝ” ይላችኋል ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፣ በተቸገረ ሰው ውስጥ እገኛለሁና እኔን ማግኘት ከፈለጋችሁ ወደ እዚህ ሥፍራ ኑ ይለናል። እዛው ነኝ ይላል ኢየሱስ። በተጨማሪም ኢየሱስ እነዚህን ቃላት ይነግራችኋል፣ ወጣቶች፣ በህይወታችሁ ውስጥ ህልማችሁን ለማሳካት በምትጥሩበት ጊዜ ሁሉ እኔ በእዚያ እገኛለሁ ይለናል ጌታ።

እዛው ነኝ። ኢየሱስ እነዚህን ቃላት ከብዙ መቶ አመታት በፊት ለአንድ ወጣት ወታደር ተናግሮ ነበር። የአሥራ ስምንት ዓመት ልጅ ነበር እና ገና አልተጠመቀም። አንድ ቀን ሰዎች እንዲረዱት የሚለምን አንድ ምስኪን ሰው አየ፤ ነገር ግን “ሁሉም ምንም ሳይሰጡት ስለሄዱ” ምንም አላገኘም ነበር። ያ ወጣት “ሌሎች ርኅራኄ እንዳልነበራቸው ሲመለከት፣ ድሃውን ሰው እርሱ መርዳት እንዳለበት ተረዳ። ሆኖም እሱም ምንም ነገር አልነበረውም፣ ያለው የለበሰው የወታደር ዩኒፎርም ብቻ ነበር በወቅቱ የነበረው። የለበሰውን መጎናጸፊያውን ለሁለት ቆርጦ ግማሹን ለድሃው ሰው ሰጠ፣ ከአንዳንድ ተመልካቾችም የፌዝ ሳቅ ገጠመው። በሚቀጥለው ምሽት ሕልምን አየ፡ ኢየሱስን በድሃው ሰው ላይ ከጠቀለለው መጎናጸፊያው ግማሹን ለብሶ አየው፣ እናም እንዲህ ሲል ሰማ፡- ማርቲን፣ በእዚህ መጎናጸፊያ ሸፍንህኛል” ብሎ ሲናገር ሰማው።  ቅዱስ ማርቲን ያ ወጣት ነበር። ያን ሕልም አየ ምክንያቱም ሳያውቅ የዛሬ ቅዱስ ወንጌል እንደምያዘው በተግባር ፈጸመ።

ውድ ወጣቶች ፣ ውድ ወንድሞች እና እህቶች ፣ በታላቅ ህልም ተስፋ አንቁረጥ። የሚያስፈልገውን ነገር ብቻ አንፈልግ። ጌታ የአስተሳሰብ አድማሳችንን እንድናጠብ ወይም በህይወት መንገድ ላይ ቆመን እንድንቆይ አይፈልግም። በድፍረት እና በደስታ ወደ ከፍተኛ ግቦች እንድንሮጥ ይፈልጋል። የተፈጠርነው ስለ ዕረፍት ወይም ቅዳሜና እሁድ ለማለም ብቻ ሳይሆን የእግዚአብሔርን ህልሞች በዚህ ዓለም እውን ለማድረግ ጭምር ነው። የሕይወትን ውበት እንድንቀበል እግዚአብሔር ሕልምን ማለም እንድንችል አድርጎናል። የምሕረት ሥራዎች በሕይወት ውስጥ በጣም ቆንጆ ሥራዎች ናቸው። እነሱ በቀጥታ ወደ ታላቁ ሕልማችን ልብ ይሄዳሉ። ስለ እውነተኛ ክብር እያለምክ የዚህ ዓለም ክብር ሳይሆን የእግዚአብሔር ክብር፣ የምትከተለው መንገድ ይህ ነው። የዛሬውን የወንጌል ክፍል እንደገና አንብቡና አስቡበት። የምሕረት ሥራ ከምንም በላይ እግዚአብሔርን ያከብራልና። በጥሞና አድምጡ፡ የምህረት ስራ ከምንም በላይ ለእግዚአብሔር ክብር ይሰጣሉ። በመጨረሻ በምናደርገው እና በምንፈጽመው የምሕረት ሥራ ላይ መሰረት ባደረገ መልኩ ነው የሚፈረድልን።

ግን እንዴት ታላቅ ህልሞችን እውን ማድረግ እንጀምራለን? ምርጥ የሆኑ ምርጫዎችን በማድረግ። የዛሬው ቅዱስ ወንጌል ስለዚህ ጉዳይ ይነግረናል። በእርግጥም በመጨረሻው ፍርድ፣ በመረጥናቸው ምርጫዎች ላይ ጌታ ይፈርድብናል። እሱ የሚፈርድ አይመስልም ነገር ግን በጎቹን ከፍየሎች መለየት ይኖርበታል፣ ጥሩ ወይም ክፉ መሆን በእኛ ተግባር ላይ የተወመሰረት ነው። እሱ የኛን ምርጫ ውጤቶች ብቻ ያወጣል፣ ወደ ብርሃን ያመጣቸዋል እና ያከብራል። ሕይወትን ለማየት እንመጣለን፣ ጠንካራ፣ ቆራጥ፣ ዘላለማዊ ምርጫዎችን የምናደርግበት ጊዜ ነው። ተራ ምርጫዎች ወደ ተራ ሕይወት ይመራሉ፣ ለታላቅነት ሕይወት ትልቅ ምርጫዎች ያስፈልጋሉ። በእርግጥም ለበጎም ሆነ ለመጥፎ የመረጥነውን እንሆናለን። መስረቅን ከመረጥን ሌቦች እንሆናለን። ስለ ራሳችን ለማሰብ ከመረጥን ራሳችንን እናሳያለን። ለመጥላት ከመረጥን እንቆጣለን። በሞባይል ላይ ሰዓት ለማሳለፍ ከመረጥን ሱሰኛ እንሆናለን። ነገር ግን እግዚአብሔርን ከመረጥን በየቀኑ በእሱ ፍቅር እናድጋለን፣ እናም ሌሎችን ለመውደድ ከመረጥን እውነተኛ ደስታን እናገኛለን። ምክንያቱም የኛ ምርጫ ውበት የሚወሰነው በፍቅር ላይ ነው። ይህንን አስታውሱ ምክንያቱም እውነት ነው፡ የኛ ምርጫ ውበት የሚወሰነው በፍቅር ላይ ነው። ኢየሱስ ራሳችንን የምንማርክ ከሆንን፣ ደንታ ቢስ ከሆንን፣ ሽባ ሆነን እንደምንቀር ያውቃል፥ ነገር ግን ራሳችንን ለሌሎች ከሰጠን ነፃ እንሆናለን። የሕይወት ጌታ ሕይወታችን የተሟላ እንዲሆን ይፈልጋል፣ እናም የሕይወትን ምስጢር ይነግረናል፡ እርሱን ልናገኘው የምንችለው እሱን በመስጠት ብቻ ነው። ይህ የህይወት ህግ ነው፡ ህይወትን አሁን እና በዘላለማዊነት ለመያዝ የምንችለው እሱን በመስጠት ብቻ ነው።

እውነት ነው፣ ምርጫዎቻችንን አስቸጋሪ የሚያደርጉ መሰናክሎች አሉ፡ ፍርሃት፣ አለመተማመን፣ ብዙ ያልተመለሱ ጥያቄዎች… ፍቅር ግን ከእነዚህ ውስጥ እንድንሻገር ይጠይቀናል፣ እናም ለምን ህይወት በዚህ መንገድ እንደሆነ እያሰብን እና ለጥያቄዎች መልስ ከሰማይ እንዲወርድ በማሰብ እንጨነቃለን። መልሱ ይፋ ሆኗል፣ የወደደን ልጁንም የላከልን የአብ እይታ ነው። ፍቅር ለምን ከሚለው አልፈን እንድንሄድ ይገፋፋናል፣ ይልቁንም ለማን ብለን እንድንጠይቅ፣ “ለምን ሕያው ሆንኩኝ?” ብለን ከመጠየቅ እንድንሻገር ፍቅር ይገፋፋናል። "የምኖረው ለማን ነው?" "ለምንድን ነው ይህ በእኔ ላይ የሚደርሰው?" "ማንን መርዳት እችላለሁ?" ለማን? ለራሴ ብቻ አይደለም! ሕይወት ቀድሞውኑ ለራሳችን በምናደርጋቸው ምርጫዎች የተሞላች ናት፡ ምን ማጥናት እንዳለብን፣ የትኞቹን ዓይነቶች ጓደኞች እንደሚኖሩን ፣ የትኛውን ቤት እንደምንገዛ ፣ በምን ፍላጎቶች ወይም የትርፍ ጊዜ ማሳለፊያዎች ውስጥ መሳለፍ እንደምንፈልግ ወዘተ....። መውደድ ሳንጀምር ስለራሳችን በማሰብ አመታትን ማባከን እንችላለን። ይህንን በተመለከተ አሌሳንድሮ ማንዞኒ ( በጣሊያን በሚላን የተወለደ፣ እ.አ.አ 1785 -1873 የኖረ፣ ጣሊያናዊ ጸሐፊ፣ ገጣሚ እና ተውኔት ነበር) ጥሩ ምክር ሰጥቶ ነበር:- “ጥሩ ነገር ለማድረግ ከፈለግን ደህና መሆን አለብን። እናም በመጨረሻም የተሻለ ለመሆን ደግሞ መውጣት አለብን” ይል ነበር።

ጥርጣሬዎች እና ጥያቄዎች ታላቅ እና ለጋስ ምርጫዎችን ብቻ ሳይሆን ሌሎች ብዙ እንቅፋቶችን በየቀኑ ሊያበላሹ ይችላሉ። የዘመኑ ትኩሳት የሆነው ከልክ በላይ የሆነ የሸማችነት መንፈስ ልባችንን ከመጠን በላይ በሆኑ ነገሮች ልያጨናንቀው ይችላል። የመደሰት አባዜ ከችግሮች ለመዳን ብቸኛው መንገድ ሊመስል ይችላል፣ ነገር ግን በቀላሉ ያራዝመዋል። ከመብታችን ጋር መጣጣም ለሌሎች ያለንን ሀላፊነት ችላ እንድንል ያደርገናል። ከዚያም ስለ ፍቅር ትልቅ አለመግባባት አለ፣ እሱም ከኃይለኛ ስሜቶች በላይ፣ ነገር ግን በዋናነት ስጦታ፣ ምርጫ እና መስዋዕትነት የመክፈል ችልተኝነት አለ። በጥሩ ሁኔታ የመምረጥ ጥበብ በተለይ ዛሬ ተቀባይነትን አለማግኘት፣ የፍጆታ አስተሳሰብ ውስጥ መዘፈቅ ዋናው ነገር ተስፋ በሚያስቆርጥ ሁኔታ ውስጥ አለመግባት እና ለመልክ አምልኮ አለመስጠት ማለት ነው። ህይወትን መምረጥ ማለት ህይወታችንን ወደ መንግሥተ ሰማያት ግብ ወደ እግዚአብሔር ህልሞች ለመምራት "ተጠቅሞ የመጣል ባህል" እና ሁሉንም ነገር "አሁን ማግኘት አለብኝ" የሚል  ፍላጎትን መቃወም ማለት ነው። ሕይወትን መምረጥ መኖር ማለት ነው፣ እናም እኛ የተወለድነው ለመኖር ብቻ አይደለም። እንደ እናንተ የነበረው ወጣት ብፁዕ ፒየር ጆርጂዮ ፍሬሳቲ እንዲህ ብሎ ተናግሮ ነበር “ስኬታማ መሆን ብቻ ሳይሆን፣ መኖር እፈልጋለሁ” ብሎ ነበር።

በየቀኑ፣ በልባችን፣ ብዙ ምርጫዎች ያጋጥሙናል። ጥሩ እንድንመርጥ ልባችንን ለማሰልጠን አንድ የመጨረሻ ምክር መስጠት እፈልጋለሁ። ወደ ራሳችን ከተመለከትን፣ ሁለት የተለያዩ ጥያቄዎች ሲነሱ ማየት እንችላለን። አንዱ “እኔ ምን ማድረግ ነው የምፈልገው?” ብሎ ይጠይቃል። በጣም አስፈላጊው ነገር ስለራሳችን ማሰብ እና ምኞቶቻችንን እና ግፊቶቻችንን መፈፀም እንደሆነ ስለሚጠቁም ይህ ጥያቄ ብዙውን ጊዜ አሳሳች ነው። መንፈስ ቅዱስ በልባችን ውስጥ የተከለው ጥያቄ በጣም የተለየ ነው፡ “እኔ ምን ማድረግ ነው የምፈልገው?” የሚለው ሳይሆን ነገር ግን "ለአንተ የሚሻለው ምንድን ነው?" የሚለው ጥያቄ ሊሆን ይገባል፣ በየቀኑ ማድረግ ያለብን ምርጫ ይህ ነው፡ ምን ማድረግ እንዳለብኝ ይሰማኛል ወይስ ምን ይሻለኛል? ይህ ውስጣዊ ማስተዋል ወደ ብዙ ወደ ማይጨው ምርጫዎች ወይም ህይወታችንን በሚወስኑ ውሳኔዎች ላይ ሊያስከትል ይችላል - መልሱ በእኛ ላይ የተመሰረተ ነው። ወደ ኢየሱስ በመመልከት ድፍረት እንዲሰጠን እንጠይቀው፣ የሚበጀንን እንድንመርጥ፣ በፍቅር መንገድ እንድንከተለው ሊረዳን ይችላል። እናም በዚህ መንገድ ደስታን ለማግኘት እንችላለን። ለመኖር እንጂ እንዲያው በከንቱ በሕይወት መንገድ እንዳናልፍ እንዳልተጠራን እንድንገነዘብ እርሱ ሊረዳን ይችላል።

ይህንን በተግባር ማዋል እንችል ዘንድ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በአማላጅነቷ ትርዳን!!

ምንጭ፡ ኢየሱስ የዓለም ንጉሥ አመታዊ በዓል እና በአገረ ስብከት ደረጃ 38 ኛው የዓለም ወጣቶች ቀን በተከበረበት ወቅት እ.አ.አ በኅዳር 22/2020 ዓ.ም ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በቫቲካን በሚግኘው በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ባሳረጉት መስዋዕተ ቅዳሴ ላይ ካደረጉት ስብከት የተወሰደ!

አቅርቢ አባ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ፣

 

02 December 2023, 21:00