ፈልግ

በጋዛ የሚገኘው የሆሊ ፋሚሊ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን (ፎቶ ፋይል) በጋዛ የሚገኘው የሆሊ ፋሚሊ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን (ፎቶ ፋይል) 

አንድ የጋዛ ነዋሪ 'በጋዛ እየተካሄደ ያለው ጦርነት እርስ በርስ እንድንተሳሰብ አድርጎናል’ አለ

ሱሃይል አቦ ዳውድ የተባለው በጋዛ ሆሊ ፋሚሊ አጥቢያ ቤተክርስቲያን ተጠልሎ የሚገኘው የ18 ዓመቱ የካቶሊክ እምነት ተከታይ ጦርነቱ ካመጣቸው በጎ ነገሮች ውስጥ ሰዎች እርስ በርስ እንዲዋደዱ እና አመለካከታቸውን እንዲቀይሩ እድል እንደሚፈጥር ያለውን እምነት ገልጿል።

   አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

መስከረም 26, 2016 ዓ.ም. ላይ የእስራኤል-ሀማስ ጦርነት ከተነሳ በኋላ ከ700 በላይ የሚሆኑ ሰዎች በሰሜን ጋዛ በሚገኘው የሆሊ ፋሚሊ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ጊቢ ውስጥ ተጠልለው ይገኛሉ። እነዚህ ነዋሪዎች እንደ አንድ የክርስቲያን ማህበረሰብ በህብረት በየቀኑ ሁለት ጊዜ የቅዳሴ ሥነ ስርዓት ላይ እንደሚሳተፉ እና ሰላምና ጥበቃ እንዳይለያቸው ለበርካታ ጊዜያትም ደጋግመው የመቁጠሪያ ጸሎት እያደረጉ ይገኛሉ።

ነገር ግን የውሃ እና የምግብ አቅርቦቶች እያሽቆለቆለ በመምጣቱ እንዲሁም በቤተክርስቲያን ውስጥ ከ3 ሳምንታት በላይ በመኖራቸው ሞራላቸውን እየነካ መምጣቱን ተናግረዋል። ቤተክርስቲያኒቷ ቅጥር ጊቢ ውስጥ ከተጠለሉት መካከል አንዱ የሆነው ወጣት ሱሃይል አቦ ዳውድ በምንም ነገር እርግጠኛ መሆን በማይቻልበት እና ፈተናዎች በሚበዙበት ጊዜ ከክርስቶስ ጋር መጣበቅ አስፈላጊ እንደሆነ የሚገልጹ አጫጭር ደብዳቤዎችን በመላክ ለውጭው ዓለም የማስተዋል እና የተስፋ ድምጽ ሆኗል።

የእግዚአብሔር መልእክት ለጋዛ ክርስቲያኖች

ወጣት አቦ ዳውድ በቅርብ ከፃፈው መልዕክቶቹ ውስጥ ጥቅምት 19 ሰኞ ዕለት የፃፈው መልዕክቱ በቫቲካን ዜና የታየለት ሲሆን፥ በደብዳቤውም ላይ ‘ሌላ ከባድ እና አስቸጋሪ ጦርነት እዚህ ጋዛ ውስጥ’ ማሳለፉን ገልጿል።

በተመሳሳይ ጊዜ፣ ከጦርነት ፖለቲካ የሚርቁ ጥቂት ‘ቀላል መንፈሳዊ ሀሳቦችን’ ለማቅረብም እድሉን ተጠቅሞበታል። “ይህ ጦርነት ለእኛ እዚህ ላለነው ጨምሮ ለመላው የሰው ዘር፣ ለሁሉም የሚሆን መልእክት አለው ብዬ አምናለሁ” ካለ በኋላ “እንዲሁም በተጨማሪ በጋዛ ላሉት ክርስቲያን ማህበረሰብ ከእግዚአብሔር የተላከ መልእክት እንዳለው አስባለሁ” ሲል ፅፏል።

ሌላውን ሰው መውደድ እና መስዋዕትነት መክፈልን መማር

በድሮ ጊዜ “ደመና ሁሉ የብር ሽፋን አለው” የሚል ምሳሌያዊ አባባል ነበረ። ከእያንዳንዱ መከራ ጀርባ ጥሩ ነገር ይኖራል እንደማለት ነው፥ እናም ወጣት አቦ ዳውድ ጦርነቱ ‘ከባድ የህይወት ትምህርት’ እንደሰጠው ይሰማዋል።

“ምናልባት ሁላችንም ከጦርነቱ በኋላ ልክ እንደ አንድ ቤተሰብ፣ ልክ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሌሎችን እንዴት እንደረዳ እና እንዳገለገለ ሁሉ፣ የበለጠ እንድንዋደድ እና የበለጠ እንድንረዳዳ ተጠርተናል ፤ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለእኛ ሲል መስዋእት እንደሆነ እኛም ለሌሎች ሰዎች መስዋዕትነት መክፈል አለብን” ብሏል። ከእንደዚህ አይነት አስቸጋሪ ጊዜ በኋላ የአስተሳሰብ እና የባህሪ ለውጥ ሊኖር ይገባል በማለትም ይመክራል ወጣት አቦ ዳውድ።

“ከጦርነቱ በኋላ በፊት እንኖርበት ከነበረው በተለየ የአኗኗር ዘይቤ እንደምንኖር ይሰማኛል፥ ጌታች ኢየሱስ ክርስቶስ በትልቁ እና ውብ በሆነው ነፍሱ ሰዎችን ከብዙ ደዌ እንደፈወሰ ሁሉ፡ እኛም ትልቅ እና ልዩ በሆነ ልብ እርስ በርሳችን በመረዳዳት ህዝቡን እናገለግላለን” በማለት ወደፊት እንዴት መኖር እንዳለበት ያልማል ወጣቱ።

ሰማያዊ መኖሪያ
ወጣቱ ካቶሊክ ጥቅምት 14, 2016 ዓ.ም. ረቡዕ ዕለት በጋዛ የሚገኘውን ምድራዊ መኖሪያ ቤቱ በእስራኤል የአየር ድብደባ ከወደመበት በኋላ አንድ የተረዳውን ነገር በማስታወስ ደብዳቤውን አጠናቋል። “ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን እንደ እውነተኛ ቤቴ እቆጥረዋለሁ። ኢየሱስ በዚህ ጭካኔ በተሞላበት ዓለም ውስጥ የሰላም እና የፍቅር ቤቴ ነው” ሲል ጽፏል።

እናም ወጣት አቦ ዳውድ የወደፊቱን በማየት “ምድራችን ሰማይ ሊፈውሰው የማይችለው ሃዘን የላትም” የሚለውን የቶማስ ሙር አባባል አስታውሷል።
 

01 November 2023, 14:01