ፈልግ

ሶስቱ ተሸላሚ ሲስተሮች ሶስቱ ተሸላሚ ሲስተሮች 

ሶስት የካቶሊክ ገዳማዊያት እህቶች የ2023 የፀረ-ህገወጥ የሰዎች ዝውውር ሽልማትን አሸነፉ

በለንደን የሚገኘው ‘የመነኮሳት ፀረ-ህገወጥ የሰዎች ዝውውር ሽልማት’ ሲስተር ሴሊ ቶማስን፣ ሲስተር ፓትሪሺያ ኢቤግቡለም እና ሲስተር ፍራንሷ ጂራኖንዳን በዓለም ዙሪያ ላለው የፀረ-ህገወጥ የሰዎች ዝውውር እንቅስቃሴ ላበረከቱት አስተዋፅኦ በክብር ሸልሟቸዋል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

የመነኮሳት የፀረ-ህገወጥ የሰዎች ዝውውር ሽልማት ሥነ ስርዓት በቀድሞዋ የእንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስትር ቴሬዛ ሜይ እና አትሌት ሰር ሞ ፋራህ አስተናጋጅነት ጥቅምት 20, 2016 ዓ.ም. በለንደን ከተማ ተካሂደዋል።

በዚህም ሥነ ስርዓት ሶስት የካቶሊክ እህቶች ባበረከቱት ጉልህ ሚና የተሸለሙ ሲሆን፥ ሲስተር ሴሊ ቶማስ ከህንድ፣ ሲስተር ፓትሪሺያ ኢቤግቡለም ከናይጄሪያ፣ እንዲሁም ሲስተር ፍራንሷ ጂራኖንዳ ከታይላንድ ሽልማቱን ተቀብለዋል።

ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ናይጄሪያን አስጨንቋል

ሲስተር ፓትሪሺያ ኢቤግቡለም በማይናወጥ አቋም የፀረ-ህገወጥ የሰዎች ዝውውርን በመፋለም ከ20 ዓመታት በላይ በህገወጥ የሰዎች ዝውውር ላይ ግንባር ቀደም ተሟጋች ሆነው ሲሰሩ ቆይተዋል። ሲስተሯ ይህን አስመልክተው በሰጡት መግለጫ ላይ እንደተናገሩት፥ “ናይጄሪያውያን ሴቶች ብዙውን ጊዜ የሕገወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች ሰለባ በመሆን በአውሮፓ እና በመካከለኛው ምስራቅ ሃገራት የጉልበት ብዝበዛ ይደርስባቸዋል” ሲሉ ተናግረዋል።

እንደ ሲስተር ኢቤግቡለም አባባል “ብዙዎቹ ወደ ተሻለ የኑሮ ደረጃ ለመሻገር ስለሚያልሙ፥ ህገ ወጥ አዘዋዋሪዎቹ ይሄንን ተስፋቸውን እና ህልማቸውን በመጠቀም ወዳልተገባ የጉልበት ብዝበዛ ይመሯቸዋል” ብለዋል። በማከልም “የእነዚህን የእግዚአብሔር ልጆች ስቃይ ባየሁ ጊዜ ልቤ እጅጉኑ ይነካል” በማለት ተናግረዋል። 

ሲስተር ኢቤግቡለም ህገወጥ ዝውውርን ማስቆም እጅግ ከባድ እንደሆነ ቢያምኑም የማይቻል እንዳልሆነ ግን ያውቃሉ። ይህን ሲያብራሩም “የማይቻል አይደለም፥ የማይቻል ነው አልልም፥ ምክንያቱም ከእግዚአብሔር ጋር ስትሆን የማይቻል ነገር የለምና” ብለዋል።

በመላ ህንድ ውስጥ ሰለባ የሆኑ ማህበረሰቦች

ከህንድ የመጡት ሲስተር ሴሊ ቶማስ ሌላኛዋ ተሸላሚ ሲሆኑ፥ እሳቸውም ከዚህ ችግር ማህበረሰባቸውን ለመጠበቅ ሕይወታቸውን ሙሉ አሳልፈዋል። ሲስተሯ ህንድ ውስጥ ስላለው ህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ሲናገሩ “በገጠር አካባቢ የሕጻናት ጉልበት ብዝበዛን ወይም ሴት ልጇ በውሸት የሥራ ዕድል ወደ ከተማ ገብታ ለጉልበት ብዝበዛ የተዳረገችባት እና በሐዘን ላይ ያለች እናትን ለማግኘት በጣም ሩቅ መሄድ አያስፈልግም” ብለዋል። ሲስተር ሴሊ ቶማስ ለበርካታ ለክሪሽናጋር አከባቢ እናቶች እና ልጆች የተስፋ ብርሃን በመሆን ከሴተኛ አዳሪነት ህይወት ውስጥ እንዲወጡ መውጫ መንገዶችን አመቻችተዋል።

ሲስተር ሴሊ የድህነትን፣ የስራ አጥነትን እና የጉልበት ብዝበዛ መንስኤዎችን ለመፍታት ታልሞ በተቋቋመው ፕሮጄክት ውስጥ ከሥራ ቡድኖቻቸው ጋር በመሆን ከ500 በላይ ሴቶችን ረድተዋል። ይህንንም ሲገልፁ “ብዙ ችግሮች እንዳሉ ስለምናውቅ፥ የግንዛቤ ማስጨበጫ ፕሮግራሞችን ስናዘጋጅ በፀረ-ህገወጥ የሰዎች ዝውውር ላይ ብቻ ሳይሆን በተለያዩ ጉዳዮች ላይ መጥተው እንዲያናግሩን ጊዜ እንሰጣቸዋለንቦታ” ብለዋል።

ታይላንድ፡- የህገወጥ የሰዎች ዝውውር መገናኛ ቦታ

ከሶስቱ ተሸላሚዎች ውስጥ አንዷ የሆኑት እና ከታይላንድ የመጡት ሲስተር ፍራንሷ ጂራኖንዳ፥ ሕገወጥ የሰዎች ዝውውርን በመዋጋት ረገድ የአገልጋይ አመራር ሞዴል በመሆን ከ30 ዓመታት በላይ ሆኗቸዋል።
ሲስተር ጂራኖንዳ “በአሁኑ ጊዜ እነዚህ የወንጀል መረቦች ወደ 600,000 የሚጠጉ የታይላንድ ዜጎችን ለወሲብ ወይም ለጉልበት ብዝበዛ ዳርገዋል” ሲሉ በቁጭት ተናግረዋል።

ሃገራቸው ላይ ያለውን ችግር ሲገልፁ “ታይላንድ የህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር መናገሻ ቦታ ስትሆን፥ ከመላው እስያ በህገወጥ የሰው አዘዋዋሪዎቹ ሰለባ ለሆኑ ሰዎች መሸጋገሪያ እና መዳረሻ ሃገር ነች” በማለት ገልፀዋታል።

ሲስተር ጂራኖንዳ ‘ታሊታ ኩም ታይላንድን’ በማቋቋም እና በማሳደግ ረገድ ትልቅ አስተዋፅዖ አበርክተዋል። እዚህም ተቋም ዉስጥ ሆነው ሲሰሩ በደንብ የተደራጁ ወንጀለኞችን እንዳዩ እና ለእነዚህም የወንጀለኞች ተግባር በደንብ የተደራጀ ምላሽ የመስጠት ሥራ እንደሚሰራ ገልፀዋል። የተቋሙ የመጀመሪያ አስተባባሪ በመሆን በሃገር አቀፍም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቋሙ እንዲጎለብት ብዙ እህቶችን እና አባላትን በማሰማራት፣ በማሰልጠን እና በማብቃት ብዙ ስራ ሰርተዋል።

‘ታሊታ ኩም ታይላንድ’ በእሳቸው አመራር ለፀረ-ህገወጥ የሰዎች ዝውውር ትግል ልዩ አስተዋፅዖ አበርክቷል፥ በዚህም ሥራቸው ለድርጅታቸው የታይላንድ መንግስትን የተከበረ የሰራተኞች ሽልማት አስገኝተዋል።

“እግዚአብሔር በሰጠኝ ጊዜ፡ ህገ ወጥ የሰው ዝውውርን ለመከላከል ባገኘውት አጋጣሚ ሁሉ እታገላለሁ” በማለት ሲስተር ጂራኖንዳ ሃሳባቸውን ቋጭተዋል።
 

08 November 2023, 14:07