ፈልግ

የዮሞል አ'ቴል ቡድን በሥራ ላይ  የዮሞል አ'ቴል ቡድን በሥራ ላይ  

ሜክሲኮ፡ ‘በጥሩ ሁኔታ የመኖር’ ጥበብ በሴቶች በኩል ይገለፃል

በዛሬው የላውዳቶ ሲ ታሪካችን በሜክሲኮ ውስጥ ፍጥረትን መንከባከብን፣ ሴቶችን ማብቃትን እና ሀገር በቀል ባህሎችን ማክበርን አጣምሮ የሚሰራ በአገሬው ተወላጆች የሚተዳደር ንግድን እንቃኛለን።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

ሜክሲኮ ውስጥ በሚገኘው በሰሜናዊው የቺያፓስ ጫካ፥ ለሃያ ዓመታት፣ በሴልታሌስ ተወላጅ ሴቶች እና ቤተሰቦቻቸው የሚተዳደሩ ማህበራዊ-ተኮር የንግድ ድርጅቶች ቡድን ለፍትህ እና ለመሬታቸው ጥበቃ ሲሰሩ ቆይተዋል። 

ቡድኑ ‘ዮሞል አ’ቴል’ ይባላል፤ ትርጉሙም “አብረን እንሰራለን፣ አብረን እንራመዳለን፣ አብረን እናልማለን” እንደ ማለት ነው።

የኩባንያው የማህበራዊ ፈጠራ አስተባባሪ የሆነችው ኤሪካ ላራ 32 ዓመቷ ሲሆን፥ በቢዝነስ የትምህርት ዘርፍ ዲግሪ አግኝቷል። የእርሷ ሚና የምርት አጋሮቻቸውን በጨርቃ ጨርቅ ማምረት ሂደት ውስጥ ማገዝ እና ማሰልጠን ነው።
ላራ እንዳለችው የዚህ የህብረት ስራ ማህበራት ግብ፥ የሴቶችን ተሳትፎ በዲሞክራሲያዊ ሂደቶች ውስጥ ማሳደግ፣ ድምጽ መስጠት እና ወደ ኢኮኖሚው እንዲገቡ ማድረግ እንዲሁም በራሳቸው ቤት ውስጥ የራስ ገዝነታቸውን ማረጋገጥ ነው ብላ ገልፃለች።

የእነርሱ ፍልስፍና ‘ሌክዌል ኩክሲሌጃሊል’ ወይም “ጥሩ ኑሮ መኖር” የሚል ሲሆን፥ ዓላማቸውም በዘላቂነት እና ትርፋማነት ማህበራዊ ጥቅምን ማመቻቸት ነው።

የዚህ 'ትልቅ አምራች ቤተሰብ' የንግድ አባላት መካከል ‘ዛፖንቲክ’ (Xapontic) ወይም 'የእኛ ሳሙና' በሚል የምርት ስም የንፅህና መጠበቅያዎችን የሚያመርት ማምረቻ ይገኝበታል። እ.አ.አ. ከ 2007 ጀምሮ እንደ ሻምፖዎችን፣ ሳሙናዎችን እና የሰውነት ክሬም ያሉ የግል ንፅህና መጠበቂያ ምርቶችን እያመረተ ይገኛል።

የዚህን የኅብረት ሥራ ማኅበራት ትሥሥርን ያስተዋወቀው በባቻጆን የሚገኘው በአካባቢው ካሉ ማህበረሰቦች እና የስልታሌስ ቤተሰቦች ጋር ከ60 ዓመታት በላይ ያስቆጠረው የጀሱሳዊያን ተልእኮ ማህበር ነው።

በተጨማሪም ጥንታዊውን የ ‘ሎሚሎ’ ስፌት ዘዴ (በተፈተሸ ጨርቅ እና ክር) በመጥቀም በእጅ የተሰሩ የቆዳ ቦርሳዎችን፣ የውበት መጠበቂያ ቁሶች መያዣዎችን፣ ቦርሳዎችን፣ ግድግዳ ላይ ማንጠልጠያ እና አምባሮችን ይሠራሉ። ላራ እንዳለችው ይሄንን ባህላዊ ዘዴ መጠቀማችን ታናናሾቻችን ማንነታቸውን እንዳይረሱ ያደርጋል ብላለች።

መሬት ከኢኮኖሚ ቁስ በላይ ነው

እነዚህን ባህላዊ ልማዶች ከመጠበቅ አንፃር የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ሃዋሪያዊ ደብዳቤ የሆነው ላውዳቶ ሲ ውስጥ የተናገሯቸውን ቃላት ያስተጋባሉ። በዚያ ሰነድ ላይ በግልፅ እንደተገለፀው፥ ለአገሬው ተወላጅ ማህበረሰቦች እና ባህላዊ ትውፊቶቻቸው ልዩ ትኩረት እንዲሰጥ ቅዱስ አባታችን በክፍል 146 ላይ “ከሌሎች መካከል እንደ አንድ አናሳ ሰው የሚታዩ ብቻ ሳይሆኑ ዋና ዋና የውይይት አጋሮች መሆን አለባቸው በተለይም መሬታቸውን የሚነኩ ትልልቅ ፕሮጀክቶች ሲቀርቡ” በማለት በግልጽ ተናግረዋል። ቅዱስ አባታችን በመቀጠልም እንዲህ ሲሉ ያስረዳሉ፥ “ለእነሱ መሬት ማለት ሸቀጥ አይደለም ይልቁንም ከእግዚአብሔር እና በዚያ መሬት ላይ ያረፉት ቅድመ አያቶቻቸው የተሰጣቸው ስጦታ ነው፥ ማንነታቸውንና እሴቶቻቸውን የሚጠብቁበት እና ከቅድመ አያቶቻቸው ጋር የሚገናኙበት ቅዱስ ቦታ ነው” ብለዋል።

የእነዚህ ኩባንያ ሰራተኞች ጠንክረው በመስራት ጥሩ መዓዛ ያላቸው ተክሎች እና ተፈጥሮአዊ ምርቶችን ያመርታሉ። የአካባቢን ስነ-ምህዳራዊ ብዝሃ ህይወትን ለማክበር እና ለመጠበቅ ጥንቃቄ በማድረግ የተፈጥሮ ሃብትን ከመጠን በላይ ከመበዝበዝ እና ፀረ ተባይ ኬሚካሎችን ወይም ማዳበሪያዎችን ከመጠቀም ይቆጠባሉ።

ላራ እነዚህ ዘዴዎች የሴልታልስ ሴቶች በዎርክሾፖች ውስጥ ለሚያመርቱት የእጅ ጥበብ የሚሰሩ መዋቢያዎች አስፈላጊ መሆናቸውን ገልጻለች። ጥሩ መዓዛ ያላቸው እፅዋቶች የያዙት ውሀ ከውስጣቸው ከወጣ በኋላ በደንብ ይነጠሩና የመዋቢያ ምርቶች አካል ይሆናሉ። ይህ ሙሉ በሙሉ ተፈጥሯዊ መሰረት ያለው የተጠናቀቀ ምርትን ያመጣል። ተሽጦ የሚገኘውም ትርፍ በቀጥታ ወደ ሴት አባላት እንጂ ለውጭ አቅራቢዎች አይደለም።

የዛፖንቲክ ምርቶችን ስናመርት ምድር፣ ተራሮች እና አበቦች እንደ ጥቁር፣ አረንጓዴ፣ ቀይ እና ሮዝ ባሉ ባህላዊ ቀለሞቻቸውን በመጠቀም ይወከላሉ ትላለች ላራ። አክላም “ለብራንዳችን እውነተኛ እና ብቸኛው መነሳሻ ተፈጥሮ ነው” ስትል አስተባባሪዋ ጠቁማለች።

እነዚህ ሴቶች ባህላቸውን ለመጠበቅ ጥንቃቄ እያደረጉም ቢሆን፥ አንዳንድ ዘመናዊ ቴክኒኮችን ተግባራዊ በማድረግ የበለጠ ውብ እና ልዩ ቀለም ያላቸው ጨርቆችን ያመርታሉ።  ላራ ስለዚህ ጉዳይ ስትገልፅ በዚህ መንገድ ቀደም ሲል ለመፎካከር በጣም አስቸጋሪ ወደነበሩባቸው ገበያዎች ቀስ በቀስ እየገቡ ነው፥ ምክንያቱም ባህላዊ ልብስ ብቻ የሚለብሱ ሰዎች ቁጥር አነስተኛ ስለሆነ በዚህ መንገድ ወደ ሁሉም መድረስ ይችላሉ ብላለች።

እሴት የማመንጨት ሌሎች መንገዶች

ከዘላቂ የልማት ግቦች ጋር ተያይዞ ሴት አምራቾች እና ቤተሰቦቻቸው ጥሩ ኑሮ እንዲመሩ እና መሰረታዊ ፍላጎቶቻቸውን ለማሟላት በቂ ገቢ እንዲኖራቸው ኩባንያው ፍትሃዊ ዋጋ ለማውጣት ይፈልጋል። በተጨማሪም ላራ የደመወዝ ክፍተቱን ለመቀነስ እና የሥርዓተ-ፆታ እኩልነትን ለማስፈን የሚደረገውን የማያቋርጥ ትግል አንስታለች።

ነገር ግን የድርጅቱ ቁርጠኝነት በዚህ ብቻ አያቆምም፥ ሌላው ተነሳሽነቱ በራሱ የትምህርት ሥርዓት (ሁልጊዜ ትምህርት ቤቶችን አያጠቃልልም) ለአገሬው ተወላጅ ሴቶች የሥራ ዕድል መፍጠር ነው። ይህም በአኗኗራቸው እና በተግባራቸው ላይ ተመስርተው እሴቶቻቸውን፣ ባህላቸውን እና ልምዶቻቸውን በማገናዘብ በአካባቢው ስር እንዲሰድዱ እና የመጪውን ትውልድ ህይወት እንዲጠብቁ ያስችላቸዋል።

ሰራተኞቹ የእንቅስቃሴው እምብርት ናቸው ማለት መፈክር ብቻ ሳይሆን እውነታ ነው፥ በዛፖንቲክ ምርት እና በነዚህ አይነት ኢንተርፕራይዞች ውስጥ የአካታችነት፣ የፍትህ እና የእኩልነት መርሆዎች ሁሉንም ተሳታፊዎች የሚያካትቱ መዋቅሮች ያሏቸው በአግድም ድርጅታዊ እና ውሳኔ ሰጪነት ላይ የተመሰረቱ ናቸው። እያንዳንዳቸው በየስድስት ወሩ በሚካሄዱት አጠቃላይ ስብሰባዎች ውስጥ የመናገር መብት አላቸው።

የሴቶችን ክብር መጠበቅ

ላራ እንደገለፀችው በሜክሲኮ በገጠር ድህነት ከከተማ በ20% ከፍ ያለ ሲሆን ከአገሬው ተወላጆች ደግሞ በ30% ይበልጣል ብላለች።

ከገጠር ወደ ከተማ ከሚደረገው ፍልሰት ጀርባ ቢያንስ አራት ምክንያቶች አሉ፥ እነዚህም ኢኮኖሚያዊ ሁኔታዎች፣ ትምህርት፣ የአካባቢ መራቆት እና የተደራጁ ግጭቶች ናቸው።

ከ 16 እስከ 80 የእድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ሴቶች በኅብረት ሥራ ማህበሩ ውስጥ እየሰሩ የሚገኙ ሲሆን፥ በአብዛኛዎቹ ሁኔታዎች ከ 30 ዓመት በታች የሆኑ ሰዎች ትንሽ ወይም ምንም ትምህርት የሌላቸው ናቸው። ከ 30 ዓመት በላይ የሚሆኑት ደግሞ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ብቻ ያላቸው ናቸው።

እንደ ላራ አገላለፅ “እነዚህ ልዩነቶች ሴቶችን በቤት ውስጥ ሥራዎች እና በአትክልት ግብርና ላይ ብቻ ገድቧቸዋል” ያለች ሲሆን፥ በአንፃሩ ወንዶች ምርቶቻቸውን ወይም የቀን ስራቸውን በመሸጥ ገቢ የማግኘት ሚና እንዲጫወቱ አድርጓል ብላለች። ይህ ሁኔታ ለወንዶች የበለጠ ኃይልን የሚሰጥ እና ለቤተሰብ ቀዳሚ የኢኮኖሚ ምንጭ ያደረጋቸው ሲሆን፥ ነገር ግን በተመሳሳይ ጊዜ የሴቶችን በምርታማ እንቅስቃሴዎች ውስጥ እንዳይሳተፉ ይከለክላል። ለዛም ነው ወንዶች የበላይ በሆኑበት ስርዓት ውስጥ ሴቶቹ በዛፖንቲክ ውስጥ ሆነው ለእኩልነት የሚታገሉት።

ላራ “ሴቶች የቤቱን እና በዙሪያው ባሉ ነገሮች ሁሉ ባለቤቶች እና ተንከባካቢዎች ሲሆኑ፥ ወንዶች ግን የመሬትና የግብርና ሥራን ይንከባከባሉ” ብላለች።

ቢሆንም አንዳንድ ሴቶች በከፍተኛ የአመራር ደረጃቸው ተለይተው ይታወቃሉ። ለዚህም ነው ላራ ቤተሰብን እና ሰፊውን ማህበረሰብ በማደራጀት ረገድ የሚጫወቱትን ቁልፍ ሚና አፅንዖት የሰጠችው።

የዚህ ፕሮጀክት የጀርባ አጥንት ለሆነችው ላራ፥ የሴቷ የወደፊት እጣ ፋንታ የተመሰረተው በጋራ ኢኮኖሚ ውስጥ በመሳተፍ እና “በጥሩ ሁኔታ መኖር” ፕሮጄክትን በማበረታታት ላይ ነው።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ በተለያዩ ጊዜያት እንዳስጠነቀቁት ይህ ስለ ስራ ፈትነት ወይም ስለ ዶሊቼ ቪታ (የቅንጦት ኑሮ) አይደለም፥ ይልቁንም ከተፈጥሮ ጋር ተስማምቶ መኖር እና ስምምነትን መፈለግ ነው፥ ይህም ከሚዛናዊነት የላቀ ነው።

“እንዴት ተስማምተን መንቀሳቀስ እንዳለብን ማወቅ ነው፥ ያ ነው 'በጥሩ ሁኔታ መኖር' የምንለውን ጥበብ የሚሰጠን። በአንድ ሰው እና በማህበረሰቡ መካከል ያለው ስምምነት፣ በአንድ ሰው እና በአካባቢው መካከል ያለው ስምምነት፣ በአንድ ሰው እና በአጠቃላይ ፍጡር መካከል ያለው ስምምነት። ይሄ ነው ከአከባቢው ጋር ተስማምቶ መኖር”
 

30 November 2023, 15:23