ፈልግ

አባ ኢብራሂም ፋልታስ በሳን በርናርዶ ቤተ ክርስቲያን መስዋዕተ ቅዳሴ ሲያሳርጉ አባ ኢብራሂም ፋልታስ በሳን በርናርዶ ቤተ ክርስቲያን መስዋዕተ ቅዳሴ ሲያሳርጉ  

በቅድስት ሀገር እየተካሄደ ባለው ጦርነት ሰለባ የሆኑ ህጻናትን ለማስታወስ በሮም መስዋዕተቅዳሴ ተደረገ

የቅድስት ሀገር ጠባቂ ቤተክርስቲያን ካህን የሆኑት አባ ኢብራሂም ፋልታስ በእስራኤል እና በሃማስ መካከል በተደረገው ጦርነት ለተጎዱ በሺዎች ለሚቆጠሩ ህጻናት ለመጸለይ በሮም የተደረገውን ልዩ መስዋዕተ ቅዳሴ በመሳተፍ አሳርገዋል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

በቅድስት ሀገር በተቀሰቀሰው ጦርነት ሰለባ ለሆኑ ህጻናት ሁሉ ህዳር 16 ቀን 2016 ዓ.ም. እሁድ ዕለት በሮም ልዩ ቅዳሴ ተካሂዷል። በሳን በርናርዶ ቤተ ክርስቲያን የተደረገውን የመታሰቢያ መስዋዕተ ቅዳሴውን የኢየሩሳሌም ጠባቂ ቤተክርስቲያን ካህን የሆኑት አባ ኢብራሂም መርተዋል።

አባ ኢብራሂም ፋልታስ “ከጋዛ እስከ ቤተልሔም፣ ከኢየሩሳሌም እስከ ቴልአቪቭ፣ እስከ ጄኒን ላሉት ለሁሉም ልንጸልይ እና ልናስታውሳቸው እንፈልጋለን” ብለዋል።

አባ ፋልታስ ከቫቲካን ዜና ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፥ በጋዛ ከ6,000 በላይ ህጻናት በቦምብ እንደተገደሉ እና ያልተቆጠሩትን በተለይም በፍርስራሾች ውስጥ ተቀብረው የጠፉትን ጨምሮ አጠቃላይ የሟቾች ቁጥር “እስከ 20,000 ሊደርስ ይችላል” ካሉ በኋላ፥ ከእነዚህም መካከል “ብዙዎቹ ሕፃናት፣ ሴቶች፣ አረጋውያን እና አካል ጉዳተኞች ናቸው” በማለት በቁጭት ተናግረዋል።

በመስከረም ወር መጨረሻ ላይ ሐማስ በእስራኤል ላይ በፈጸመው ድንገተኛ ጥቃት 1200 ሰዎች መግደሉን እና ከ220 በላይ ሰዎችን ደግሞ አግቶ ወደ ጋዛ ሰርጥ መውሰዱ ይታወሳል። ይህንንም ተከትሎ እስራኤል በጋዛ ላይ ለሳምንታት ባካሄደችው ወታደራዊ ዘመቻ አብዛኞቹ ሴቶች እና ሕጻናት የሆኑባቸው ከ14 ሺህ በላይ ፍልስጤማውያን መገደላቸውን በሐማስ የሚመራው የጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።

ጦርነቱ ከተጀመረ ከ50 ቀናት በኋላ ትናንት ህዳር 17 ቀን 2016 ዓ.ም. በአራተኛው ዙር 30 ህጻናትን ጨምሮ 33 ፍልስጤማውያን እስረኞች ተፈትተዋል። በእስራኤል እስር ቤቶች 6 ሺህ 704 ፍልስጤማውያን ታስረው እንደሚገኙ የመብት ተቋማት ያስታወቁ ሲሆን ከእነዚህም ውስጥ 2 ሺህ ሰባ የሚሆኑት ፍርድ ቤት አልቀረቡም ወይም ክስ እንዳልተመሰረተባቸውም ተነግሯል። አስተዳደራዊ እስራት ተብሎ በሚጠራውም ሁኔታ በእስራኤል እስር ቤቶች እንደሚገኙ ሃሞኬድ የተባለው የእስራኤል የመብት ድርጅት አስታውቋል።

የሐማስ እና የእስራኤል የተኩስ አቁም ፋታ ተከትሎም በአራት ዙሮች 150 ፍልስጤማውያን ተፈትተዋል። በኳታር አደራዳሪነት ሐማስ እና እስራኤል ለአራት ቀናት ተኩስ ለማቆም የደረሱት ስምምነት ሰኞ ዕለት ለሁለት ተጫማሪ ቀናት መራዘሙ ይታወሳል። ለተጨማሪ 48 ሰዓታት ተኩስ ለማቆም በተደረሰው ስምምነት ወቅት ሦስት ፍልስጤማውያን በአንድ እስራኤላዊ ለመለወጥ ሐማስ እና እስራኤል ተስማምተዋል።

የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ለአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በጋዛ የሚፈጸመውን የቦምብ ጥቃት ህዳር 18 ማክሰኞ ዕለት ለማስቀጠል ማሰባቸውን እንደተናገሩ አስታውቀው ነበር።

እስካሁን ድረስ የተደረጉ የታጋቾች ልውውጥ

እሁድ ዕለት በጊዜያዊ የተኩስ አቁም ስምምነት ፋታው አራተኛ ቀን፥ በሦስተኛ ዙር፥ ሃማስ ተጨማሪ 14 እስራኤላውያንን እና ሶስት ታይላንድን በአጠቃላይ 17 ታጋቾችን የለቀቀ ሲሆን፥ እስራኤል በምላሹ 39 የፍልስጤም እስረኞችን ፈታለች።

ሃማስ መስከረም 27 በደቡብ እስራኤል ባደረገው ጥቃት ከተያዙት 240 ያህል ታጋቾች መካከል 62ቱ ተፈተዋል። አንዱ ታጋች በእስራኤል ጦር የተፈታ ሲሆን ሁለቱ ደግሞ ጋዛ ውስጥ ሞተው ተገኝተዋል።
 

28 November 2023, 15:15