ፈልግ

በኢየሩሳሌም ያሉ ተማሪዎች ሰላም እንዲሰፍን ሲጠይቁ በኢየሩሳሌም ያሉ ተማሪዎች ሰላም እንዲሰፍን ሲጠይቁ 

የእስራኤል እና የፍልስጤም ህፃናት የቅዱስ ፍራንቺስኮስን የሰላም ጸሎት እየጸለዩ እንደሆነ ተነገረ

በቅድስት ሀገር የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ካህን የሆኑት አባ ኢብራሂም ፋልታስ ህፃናቱ በጋዛ ለሞቱት የብዙ እኩዮቻቸው የተሰማቸውን ሃዘን እና ስቃይ እንዲሁ የቅድስት ሀገር ልጆች ለሰላም ያላቸውን ቁርጠኝነት እና ተስፋቸውን ይጋራሉ።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

በእየሩሳሌም የሚገኘው የፍራንቺስካዊያን ትምህርት ቤት ሙስሊም እና ክርስቲያን ተማሪዎች ባለፈው ጥቅምት 24, 2016 ዓ.ም. ቅዳሜ ጠዋት ላይ አብረው ሥዕሎችን ለመሳል፣ ለመጻፍ እና ለመጸለይ ተሰብስበዋል፥ እንዲሁም ጦርነቱ እንዲቆም በጋራ ጠይቀዋል። እነዚህ ከሶስት እስከ አስራ ስምንት ዓመት እድሜ ያላቸው 400 የሚሆኑ ህጻናት እና ታዳጊዎች ግጭቱ እንዲቆም ተማጽነዋል፥ በተጨማሪም የጥላቻን እና የመገዳደል ስሜትን በፅናት አብረው እንደሚታገሉም ልጆቹ ገልፀዋል።

በእየሩሳሌም የሚገኘው የቅድስት ሃገር ጠባቂ ቤተክርስቲያን ካህን የሆኑት ፍራንቺስካዊው አባ ኢብራሂም ፋልታስ እንደሚናገሩት ህፃናቱ በአንድነት እንዲሰበሰቡ እና ተቃውሟቸውን እንዲገልጹ፣ እንዲሁም በአንዳንድ የኢየሩሳሌም ግንቦች ላይ ስለ ሠላም የሚገልፁ ስዕሎችን እንዲስሉ ያደረጉት እሳቸው እንደሆኑ ገልፀዋል። ከስዕሎቹም ውስጥ አንደኛው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሕጻናት ጋር ሆኖ ያሳያል፥ ስዕሉ ላይ ካሉ ህፃናት ደግሞ አንደኛው የመከፋት እና የሃዘን ስሜት ከፊቱ ይነበባል። ‘ይሄንን ሆን ብዬ ነው ህፃናቱን ያሳልኩት’ ይላሉ ካህኑ። አባ ፋልታስ ስለ ስዕሉ ተጠይቀው ሲያብራሩ “ምክንያቱም ስዕሉ በቅድስት አገር ማለትም በጋዛ፣ ጄኒን፣ ናቡልስ፣ ቴል አቪቭ፣ እና ጃፋ ውስጥ ያሉ ፍልስጤማዊያን እና እስራኤላውያን ልጆችን ሁሉ ስለሚወክል ነው፥ ምክንያቱም ሁሉም የቅድስት ሀገር ልጆች በዚህ ጦርነት እየተሰቃዩ ነው” ካሉ በኋላ “እነዚህ ልጆች በዓለም ላይ እንዳሉት ሌሎች ልጆች ሁሉ መኖርን እና እዚህ በቅድስት ሀገር በሰላም መኖርን ይፈልጋሉ” በማለት ለቫቲካን ዜና ተናግረዋል።

የሲስተር ናቢላ ትምህርት ቤት በቦምብ መመታቱ

ጥቅምት 24, 2016 ዓ.ም. ጧት ላይ በእየሩሳሌም የሚገኙ ህፃናት እና ወጣቶች ስለ ሰላም ሲሉ ዘምረዋል፣ ሰላም እንዲሰፍን በህብረት ጸልየዋል። ይህ በእንዲህ እንዳለ ግን የእስራኤል የአየር ሃይል ጋዛን በቦምብ መደብደቡን አጠናክሮ በመቀጠል እስካሁን ድረስ ከ 10,000 በላይ የሚሆኑ ሰዎች መሞታቸው ተዘግቧል።

የተለያዩ ትምህርት ቤቶች፣ ሆስፒታሎች እንዲሁም የ ‘ሮዛሪ ሲስተርስ’ ትምህርት ቤት በእስራኤል ቦምቦች ተመተዋል። እንደ እድል ሆኖ በግቢው እና በአካባቢው ባሉ ሕንፃዎች ላይ የደረሰ ጉዳት እንጂ ምንም አይነት ሞት አልደረሰም። የሮዛሪ እህቶች ትምህርት ቤት ርእሰ መምህር የሆኑት ሲስተር ናቢላ ሳሌህ ስለ ጥቃቱ የተናገሩ ሲሆን፥ ይህ ትምህርት ቤት በጋዛ ሰርጥ ከሚገኙ ትምህርት ቤቶች ትልቁ መሆኑን ገልፀው፥ 1,250 ተማሪዎች ያሉት መሆኑንና አብዛኞቹ ተማሪዎችም ሙስሊሞች መሆናቸውን ጭምር ገልፀዋል። ሲስተር ነቢላ ትምህርት ቤታቸው ከተመታ በኋላ ልክ እንደሌሎች ሁሉ ጋዛ ውስጥ በሚገኘው የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ወደ ሆነው ወደ ሆሊ ፋሚሊ ደብር ተፈናቅለው ሸሽተዋል።

ስለ ሰላም ማስተማር

አባ ፋልታስ ስለ ህፃናቱ ስብስብ ዓላማ ሲናገሩ “በአሁኑ ጊዜ ህፃናትን ስለ ሰላም ማስተማር አለብን፥ ለዚህም ነው እነዚህን ውጥኖች እያስተዋወቅን የምንገኘው” ካሉ በኋላ በመቀጠልም “ለእነዚህ በከፍተኛ ነፃነት ራሳቸውን በስዕላቸው ለገለጹት ህጻናት የተሻለ የወደፊት እድል እንዲገጥማቸው ከፈለግን ስለ ሰላም ማስተማር ይገባናል” ብለዋል።

ልጆቹ ካስተላለፏቸው በርካታ መልእክቶች መካከል ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ይህ ጦርነት እንዲያበቃ እንዲረዷቸው የሚጠይቁ መልእክቶችም አሉበት። ፍራንቺስካዊው ካህን በመቀጠል “ከዚያም ሁሉም ልጆች የቅዱስ ፍራንቸስኮስ ጸሎት የሆነውን 'የሰላም መሳሪያ እንድሆን አድርገኝ’ የሚለውን ጸሎት በጋራ ጸልየዋል” በማለት ገልፀዋል።

ከፍርስራሹ ስር የተቀበሩ ነፍሳት

አባ ኢብራሂም ፋልታስ የጋዛ ህጻናትን ሲያስቡ ድምፃቸው በሲቃ ይቆራረጣል። የሰላም ተስፋቸውን የገለፁበትን የልጆቹን ሥዕል ሲመለከቱ፥ በቦምብ ተደብድበው የተቀበሩትን ከአስር ሺሕ በላይ የሚሆኑትን ወጣቶችን፣ ሴቶችን፣ አዛውንቶችን፣ አካለ ስንኩላንን፣ ሆስፒታሎች በመውደማቸው ቆስለው መታከም ያልቻሉትንን ሰዎች ከማሰብ በቀር ሌላ ነገር ማሰብ እንደማይችሉ ተናግረዋል።

“ከፍርስራሹ ስር ብዙ ልጆች አሉ፥ ሌላ ምን እንደምል አላውቅም” በማለት በሃዘን በተሰበረ ልብ ተናግረዋል።
ካህኑ በመቀጠል “ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ብቻ ናቸው የተኩስ አቁም ጥሪ ያቀረቡት፥ ከዓለም ኃያላን መካከል አንዳቸውም ይሄን አላደረጉም፥ የተኩስ አቁም ስምምነት ማድረግ ብቸኛው መፍትሔ ቢሆንም ከእሳቸው በቀር ማንም አላቀረበም፥ ምክንያቱም በአሁኑ ሰዓት በጋዛ ውስጥ ሰዎች ቤት ዬላቸውም፣ ብርሃን ዬላቸውም፣ ውሃ ዬላቸውም፣ ምግብ ዬላቸውም፣ መድኃኒት አያገኙም፤ የእውነት ገሃነም ውስጥ እንደመኖር ነው፥ ገሃነም ስል አሳንሼው ነው” በማለት በምሬት ተናግረዋል።

“ስቃዩ በዌስት ባንክም ጭምር አለ፥ ከመስከረም 26 ጀምሮ ቢያንስ 150 ሰዎች የሞቱበት፣ በሺዎች የሚቆጠሩ የቆሰሉበት፣ ብዙ ሁከት ያለበት እና ሰዎች እስር ቤት ውስጥ እንደሚኖሩ የሚያስቡበት ቦታ ሆኗል” በማለት አክለው ተናግረዋል።

“ይህ ብቻ አይደለም፥ ቤተልሔምም ተዘግታለች፣ ቱሪዝም ቆሟል፣ ጉዞዎች ታግደዋል። በኢየሩሳሌም እና በናዝሬት የሚገኙ ክርስቲያኖችም መውጣት ይፈልጋሉ፤ ምንም ሥራ ዬለም” ብለዋል። በዚህም ምክንያት የቅድስት ሀገር ፍራንቺስካውያኑ ካህን አባ ኢብራሂም ፋልታስ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ “ለእግዚአብሔር ፍቅር ሲባል የጦር መሣሪያዎች ዝም ይበሉ፣ ይህ ጦርነት እንዲያበቃ በእውነት እንፈልጋለን” ብለው ያቀረቡትን ጥሪ ከልብ እንደሚጋሩት ገልፀዋል።
 

07 November 2023, 15:51