ፈልግ

የህንድ ወጣት ካቶሊኮች በማህበራዊ ሚዲያ ላይ በደንብ መሳተፍ እንዲችሉ ምርጥ ልምዶችን እየወሰዱ የህንድ ወጣት ካቶሊኮች በማህበራዊ ሚዲያ ላይ በደንብ መሳተፍ እንዲችሉ ምርጥ ልምዶችን እየወሰዱ 

የህንድ ካቶሊክ ወጣቶች ሚዲያ ላይ በንቃት እንዲሳተፉ 'በሙልአት መገኘት' ሰነድ ላይ ስልጠና ተሰጣቸው

በህንድ ከ450 በላይ የሚሆኑ የወጣት መሪዎች በጉዋሃቲ ከተማ በተካሄደው 5ኛው ሀገር አቀፍ የወጣቶች ኮንፈረንስ ላይ ተገኝተው በቤተሰብ እሴቶች እና ኃላፊነት የተሞላበት የማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም ላይ በማተኮር “በሙልአት መገኘት” በሚለው የቫቲካን ሰነድ ላይ ስልጠና ወስደዋል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

የህንድ ሰሜን ምስራቅ ግዛት በሆነችው ጉዋሃቲ ከተማ በተካሄደው የህንድ ካቶሊክ ወጣቶች ንቅናቄ (ICYM) ባዘጋጀው 5ኛው ሀገር አቀፍ የወጣቶች ኮንፈረንስ ላይ ከ450 በላይ የወጣቶች መሪዎች እና የወጣቶች ዳይሬክተሮች ተሰብስበዋል።

በናሬንጊ መንደር በሚገኘው በቅዱስ ፍራንቺስኮ ደ ሳሌስ ትምህርት ቤት ውስጥ ከጥቅምት 12 እስከ 16 2016 ዓ.ም. ድረስ የተካሄደው ይህ ስልጠና በህንድ የካቶሊክ ጳጳሳት ጉባኤ የወጣቶች ኮሚሽን ጽ/ቤት እና የጉባኤው ዋና ጸሃፊ ሆነው በማገልገል ላይ በሚገኙት በአባ ቼታን ማቻዶ አስተባባሪነት የተዘጋጀ ነው።

ኮንፈረንሱ አውደ ጥናቶችን፣ የቡድን ውይይቶችን፣ እና ክልል ተኮር የባህል ዝግጅቶችን ጨምሮ የተለያዩ ተግባራትን አቅርቧል። በዚህም ዝግጅት ላይ ከተለያዩ አካባቢዎች እና የተለያየ ባህል ያላቸው ተሳታፊዎች ተገኝተውበታል።
የኮንፈረንሱ ዋና ትኩረት የቤተሰብን፣ የወላጆችን፣ የአያቶችን እና አዛውንቶችን የቤተሰብ ግንኙነቶችን መረዳት ያለውን ጠቀሜታ በጥልቀት መመርመር ነበር።

የህንድ ካቶሊክ ወጣቶች ንቅናቄ ብሔራዊ ፕሬዝዳንት የሆኑት አንቶኒ ጁዲ ወጣቶቹ የኮንፈረንሱ መሪ ቃል ያስተላለፈውን ጥልቅ መልእክት ላይ እንዲያሰላስሉ አሳስበዋል። ፕሬዝዳንቱ በተጨማሪም ወጣቶቹ ለወላጅቻቸው እና ለአረጋዊያን ያላቸውን ፍቅር፣ አድናቆት እና ጽኑ ታዛዥነታቸውን እንዲያሳዩ ጠይቀዋል።

በኮንፈረንሱ ከቀረቡት አስር አውደ ጥናቶች አንዱ “የማህበራዊ ሚዲያ በወጣቶች ስብዕና እና አእምሮአዊ ደህንነት ላይ የሚኖረውን ተፅእኖ ይፋ ማድረግ” በሚል ርዕስ የህንድ የካቶሊክ ጳጳሳት ጉባኤ ሃዋሪያዊ ሚዲያ አስተባባሪ በሆኑት በአባ ሲረል ቪክቶር ጆሴፍ ቀርቧል።

በሙልአት መገኘት

በዚህ ወርክሾፕ ወቅት ተማሪዎች በቅድስት መንበር ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ (የቫቲካን ዜና መስራች ድርጅት) ከታተመው “በሙልአት መገኘት” በሚል ርዕስ በቅርቡ ስለወጣው ሰነድ ግንዛቤ እንዲኖራቸው ተደርጓል።  በተጨማሪም ተሳታፊዎቹ ማህበራዊ ሚዲያ ላይ በኃላፊነት ስሜት እንዲሳተፉ እና በዲጂታል ማህበረሰብ ውስጥ “ጥሩ ሳምራውያን” እንዲሆኑ ተበረታተዋል።

አውደ ጥናቱ በማህበራዊ ሚዲያ መስፋፋት እና በወጣቶች መካከል ያለውን ግንኙነት እና መስተጋብር እንዴት እንደለወጠው አብራርቷል። ተሳታፊዎች በወጣቶች መካከል ያለውን የማህበራዊ ሚዲያ ተሳትፎ ድግግሞሽ እና ቆይታ በመዳሰስ፥ የማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም ዘይቤዎች ላይ በሰፊው ተወያይተዋል። በተጨማሪም ተሳታፊዎቹ እንደ ‘የመጥፋት ፍራቻ’ (Fear of Missing Out) እና የማያቋርጥ ማህበራዊ ንፅፅር ስለሚያስከትላቸው ተጽዕኖዎች ዙሪያ ጥያቄዎችን አንስተው ውይይት አድርገውባቸዋል።

አባትህን እና እናትህን አክብር

በኮንፈረንሱ ላይ ልዩ እና ትልቅ ትርጉም ያለው አርማ ቀርቦበታል። ይህ አርማ ወላጆች በቤተክርስቲያኒቷ በኩል ወደ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሚወስደው መንገድ ልጆቻቸውን ወደ መስቀል ሲመሩ ያሳያል። በአርማው ላይ የቤተሰቡ ታላቅ  ልጅ የወላጆቹን አመራር እና ፈለግ በመከተል ታናናሽ ወንድሞቹን እና እህቶቹን በመምራት ወላጆቻቸው ኢየሱስን እንደ ቤተሰብ ለመከተል ላቀረቡት ጥሪ መታዘዝን ያሳያል።

ለጉባኤው የተመረጠው መሪ ሃሳብ፥ “ልጆች ሆይ ለወላጆቻችሁ በጌታ ታዘዙ ይህም ትክክል ነውና” ከሚለው ከ3ኛው የዓለም አያቶች ቀን እንደተወሰደም ተነግሯል።
 

09 November 2023, 13:30