ፈልግ

 አባ ፍራንቸስኮ ፓቶን (የፋይል ፎቶ) አባ ፍራንቸስኮ ፓቶን (የፋይል ፎቶ) 

አባ ፓቶን ር.ሊ. ጳጳሳቱ ለቅድስት ምድር ያቀረቡት ጥሪ የዓለም መሪዎችን ልብ መንካት አለበት አሉ

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ በእስራኤል እና በሃማስ መካከል እየተደረገ ባለው ጦርነት የተኩስ አቁም ጥሪን በድጋሚ ማቅረባቸውን ተከትሎ የቅድስት ሀገር መነኩሴ ለሰላም የጸሎትን ኃይል አጉልቶ ያሳዩ ሲሆን የዓለም መሪዎች የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳቱን ልመና እንዲሰሙ አሳስበዋል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

የቅድስት ሀገር መነኩሴ የሆኑት አባ ፍራንቸስኮ ፓቶን ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ እሑድ ዕለት በተካሄደው የመልአከ እግዚያብሄር የሰላም ጸሎት ሥነ ስርዓት ላይ ባቀረቡት የሰላም ጥሪ አድናቆታቸውን ገልጸዋል። በዕለቱም “በእግዚአብሔር ስም እለምናችኋለሁ: የተኩስ አቁም ስምምነት ይደረግ፥ ተኩስ አቁሙ!” በማለት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ በድጋሚ ጥሪያቸውን አሰምተዋል። በማከልም “የግጭቱ መባባስ ሙሉ በሙሉ እንዲወገድ የሠላም መንገዶችን እንደሚከተሉ ተስፋ አደርጋለሁ” ብለዋል።

ሕፃናት ለሥቃይ ይበልጥ ተጋላጭ ናቸው

የዕለተ እሁዱን የመልአከ እግዚያብሄር የጸሎት ሥነ ስርዓት ሥርጭት በቀጥታ ያዳመጠው አባ ፓተን ለቫቲካን ዜና እንደተናገሩት የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳቱ የሰላም ጥሪ የዓለም መሪዎችን ‘ሕሊና ይነካዋል’ የሚል እምነት አላቸው። ይህንንም በማስመልከት “የጳጳሱ ቃላት በመጀመሪያ እዚህ እየሩሳሌም ልጆች ስለ ሰላም ሲጸልዩ ስለነበረው የትናንቱ ክስተት እንዳስብ አደረገኝ” ሲሉ ተናግረዋል።

እስራኤላውያን እና ፍልስጤማውያን፣ ክርስቲያኖች እና ሙስሊሞች ቅዳሜ ጠዋት በእየሩሳሌም በሚገኘው ‘ቴራ ሳንክትራ’ (Terra Sancta) ትምህርት ቤት በጋራ በመሆን ለሰላም ፀሎት አድርገዋል። ስለ ተማሪዎቹ ጸሎት በማስታወስ “ለአባቷ ስትጸልይ የነበረች የ5 ዓመቷ ልጅ ጸሎት በጣም ገረመኝ። ይህ ፍርሃት የልጅነት ጊዜዋን ብቻ ሳይሆን ምናልባትም መላ ህይወቷን ያመላክታል” ብለዋል አባ ፓቶን። አክለውም “ልጆች የሚያሳዩት የርኅራኄ ስሜት ምናልባትም ከአዋቂዎች የበለጠ ሊሆን ይችላል፥ ልጆች ሥቃይ በሁሉም ሰው እንደሚደርስ መገንዘብ ችለዋል” ብለዋል።

“በእየሩሳሌም ያለው ሁኔታ በድንግዝግዝ ስሜት ውስጥ ያለ ነው፥ ግልጽ የሆነ ፍርሃት አለ፣ እንዲሁም የጥላቻ እና የንዴት ስሜቶች ከችግር እና ከህመም ጋር ተደባልቀው ይገኛሉ። ይህም የጸሎቶቻችንን አስፈላጊነት እና የሰላማዊ መፍትሄዎችን አስፈላጊነት የበለጠ ጎልቶ እንዲታይ ያደርገዋል፥ ይህም ለሲቪል ህዝቦች በተለይም ለህፃናት ጥበቃ እንዲደረግ ያስችላል” ብለዋል።

መጪው ጊዜ ጥላ ያጠላበት ነው

አባ ፓቶን ህይወታቸውን ላጡ ሰዎች የተሰማቸውን ታላቅ ሃዘን በመግለፅ፥ በመጀመሪያ የመስከረም 26ቱን ጥቃት በመጥቀስ በጋዛ ሰርጥ ዙሪያ በሚኖሩ የእስራኤል ሲቪሎች ላይ አሰቃቂ ግድያ እንደነበር እንዲሁም በሺዎች የሚቆጠሩ ተጎጂዎች እና 250 እስራኤላዊያን መታገታቸውን አስታውሰዋል።

በአሁኑ ጊዜ በጋዛ የሟቾች ቁጥር ወደ 10,000 እየተጠጋ ነው፥ ከእነዚህም ውስጥ ግማሾቹ ህጻናት ናቸው። ይህንንም በማስመልከት “ይህ የሁሉንም ሰው ሕሊና ሊነካ የሚገባው አሳዛኝ ነገር ነው፥ በተለይ በዚህ ዓለም ውስጥ በስልጣን ላይ ያሉትን ወንዶች እና ሴቶችን፣ በአስቸኳይ ጉዳዮች እና ወደፊት በሚደረጉ ውሳኔዎች ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ሊያሳድሩ የሚችሉትን ሰዎች ልብ ሊነካ ይገባል” ብለዋል። 

ከአንድ ወር ገደማ በፊት የጀመረው የእስራኤል እና የሃማስ ጦርነት በቅድስት ሀገር ውስጥ ያሉ አረጋውያንን እንዴት ሊጎዳ እንደሚችልም አንስተዋል። “አረጋዊያኑ ጭንቀታቸው ለልጆቻቸውና ለልጅ ልጆቻቸው ነው። ስለወደፊታቸው ሳይሆን ስለ ወዳጅ ዘመዶቻቸው ነው የሚያስቡት” ሲሉ አባ ፓቶን ተናግረዋል። “ይህን በጋዛ ብቻ ሳይሆን እዚሁ እስራኤልም አይቻለሁ። ብዙ አዛውንቶች ለልጆቻቸው እና ለልጅ ልጆቻቸው ታላቅ የወደፊት ተስፋ አይታያቸውም፥ እናም ሌላ ቦታ ህይወት ለመምራት ሲሉ አገራቸውን ለቀው እንዲወጡ ይጋብዛሉ” ብለዋል። “ጦርነቱ ለክርስቲያኑ ማህበረሰብም በጣም አሳሳቢ ሆኗል ምክንያቱም በመካከለኛው ምስራቅ ያለው የክርስቲያኑን ማህበረሰብ ቁጥር በእጅጉ ይቀንሳልና” በማለትም አክለዋል።

ጋዛ ከሚገኘው ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ያለው ዜና

ወደ 700 የሚጠጉ ሰዎች አሁንም ድረስ በጋዛ በሚገኘው የሆሊ ፋሚሊ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ሰበካ ጊቢ ውስጥ ተጠልለዋል። አባ ፓተን እንደተናገሩት "የቅርብ ጊዜ መረጃ እንደሚያሳየው በቤተክርስቲያኑ ቅጥር ግቢ ውስጥ ከፍተኛ ፍንዳታ መድረሱን ነው" ብለዋል። የቅድስት ምድር መነኩሴው አክለው “ከፍንዳታው አንዱ በመነኮሳት በሚተዳደሩት ትምህርት ቤት ግቢ ውስጥም ደርሶ ነበር” ብለዋል።

አባ ፓቶን ቃለ ምልልሱን ያጠናቀቁት በጋዛ ደብር ተጠልለው የሚገኙ ህጻናት ሰኞ ዕለት ሌሎች ህፃናት ከጳጳሱ ጋር ተገናኝተው ስለ ሰላም እንዲጸልዩ የጋበዙበትን ቪዲዮ በማስታወስ ነው። የልጆቹ ቪዲዮ “የክርስቲያናዊ ተስፋን መልካም ጎን” ያሳያል ብለዋል።
 

06 November 2023, 16:36