ፈልግ

Christians protest in Karachi against violence

እምነትህን በሚገባ ማወቅ ትፈልጋለህ?

አንዳንድ ጊዜ ስለ እምነትና ተያያዥ ርዕሰ ጉዳዮች ከጓደኞችህ፤ ከስራ ባልደረቦችህ፤ ከቤተሰቦችህ ጋር መወያየት ትፈልጋለህ ግን ቢጠይቁኝ ምን እመልሳለሁኝ? የሚል ስጋት ይከብሃል፡፡ እምነትህን ለሌሎች መመስከር ትፈልጋለህ ነገር ግን ፍርሃት አለብህ፤ ፍርሃትህ ከቤተክርስቲያን አስተምህሮ ጋር ያለህ ቁርኝት የሳሳ ከመሆኑ የመነጨ ነው፡፡ በማህበረሰቡ መካከል “እኔ ካቶሊክ ነኝ!” ብለህ ራስህን በይፋ ለመገለጽ ያሳፍርህና ያሰፈራህ ይሆናል፡፡ ዋናው ነገር የመጀመርያው መስመር ላይ የቀረበልህን ጥያቄ በሚገባ መመለስህ ነው፤ እምነትህን በሚገባ ማወቅ፤ ማድነቅ፤ መንከባከብና ለሌሎች በሙላት ማካፈል ትፈልጋለህ? መልስህ “አዎን እፈልጋለሁ” የሚል ከሆነ እነሆ እንጀምር፡፡

የእዚህ ዝግጅት አቅራቢ አባ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

ይህ የሕንፀት መርሐ-ግብር በአይነቱ ለየት ያለ ነው፤ በዚህ መርሐ-ግብር ውስጥ የምንነጋገረው እምነታችንን በሚመለከት ለሌሎች እንዴት አድርገን ማስረዳት እንደምንችል ነው፡፡ የምናምነውን ነገር ለማመን ምክንያታችን ምንድን ነው? ስለ ቤተክርሰቲያን፤ ስለ ስርዓተ-አምልኮ፤ ስለ አማላጅነት፤ ስለ መዳን፤ ስለ መፅሐፍ ቅዱስ፤ ስለ ሐጢአት፤ ስለ ፈውስ፤ በእምነት ብቻ ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ ስለመዳን፤ ስለ ምንኩስና ክህነታዊ ሕይወት ወ.ዘ.ተ... የሚነሱብንን ጥያቄዎች በምን መልኩ መመለስ አለብን? ለሚጠራጠሩ፤ በከፍተኛ ግራ መጋባት ውስጥ ለሚገኙ፤ በጭራሽ ሊያምኑን ለማይፈልጉ፤ ቀድሞ ካቶሊክ ለነበሩ እና አሁን ሌላ ቤተ-እምነት ለተቀላቀሉ፤ ከካቶሊክ ቤተክርሰቲያን ለመውጣት ጠርዝ ላይ ለደረሱ ሁሉ አሳማኝ መልስ መስጠት የምንችለው እንዴት ነው? በዚህ ዓይነት ሁኔታ ውስጥ ለሚገኙ ሰዎች ጠለቅ ያለ መጽሐፍ ቅዱሳዊ፤ ታሪካዊ፤ ምክንያታዊ እና ማህበራዊ ምላሽ መስጠት ያስፈልጋል፡፡

ሊቀ ሐዋርያት ቅዱስ ጴጥሮስ እምነታችንን በሚመለከት ምን ማድረግ እንዳለብን በግልፅ ይነግረናል፡፡ ይህ አሁን የምንወስደው ስልጠና ሁሉ ፍፃሜ የሊቀ ሐዋርያት የቅዱስ ጴጥሮስ ሓሳብ ነው፡፡ ሐዋርያው እንዲህ ይላል፡-

“ዳሩ ግን ጌታ ክርስቶስን በልባችሁ ቀድሱት፤ በእናንተ ስላለው ተስፋ ምክኒያት ለሚጠይቋችሁ ሁሉ መልስ ለመስጠት ዘወትር የተዘጋጃችሁ ሁኑ፤ ነገር ግን በየዋህነት እና በፍርሃት ይሁን” (1 ጴጥ 3፡15)

በዚህ ቃል በመመስረት ካቶሊካዊ እምነታችንን በሚመለከት ለሚነሱብን ማናቸውም አይነት ጥያቄዎች በጨዋነት እና በየዋህነት ለሁሉም ተገቢ የሆነ መልስ መስጠት አለብን፡፡ ይህንን ዓይነት ዝግጁነት እንዲኖረን ከሁሉ በፊት እኛ በበቂ ደረጃ መታነጽ ይገባናል፡፡ መጽሐፍ እንደሚያስተምረው ሰው የሚናገረው ከልቡ ሞልቶ የተረፈውን ነው፡፡

ስለ እምነትህ መልስ ለመስጠት በርካታ መጽሐፍትን ማንበብ፤ መልዕልተ ባሕርያዊ የሆነ ዕውቀት፤ እንደ ሐዋርያው ጳውሎስ አይነት የስብከት ችሎታ ወ.ዘ.ተ. አያስፈልግህም፤ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የመረጣቸው እና ለስብከተ ወንጌል አገልግሎት የላካቸው ሐዋርያት ልክ እንደ እኛ ተራ ሰዎች እንደነበሩ አስታውስ፡፡ ስለክርስትናህ ለመመስከር ተጠርተሃል፡፡ ዋናው ነገር ስለ እግዚአብሔር ቃል ሚዛናዊ የሆነ ግንዛቤ ያለህ መሆኑ ነው፤ መጽሐፍ ቅዱስን ማወቅ ያስፈልግሃል፡፡ ስለምታምነው ነገር ለሌሎች ማስረዳት ግዴታህ ነው፤ የክርስትና ትምህርት ያልሆነውን አስተሳሰብ ምክንያታዊ በሆነ ወንድማዊ ውይይት ወደ ትክክለኛው መስመር እንዲመለስ መጣር አለብህ፡፡ ይህንን ስታደርግ ግን ጨዋነት መታወቂያህ ይሁን! ምንም ጊዜ ቢሆን የተሳሳተውን አመለካከት በገርነት ለማቅናት መሞከር እንጂ ግለሰቡን ማሳዘን አይገባም፡፡ የዋንጫውን ዝገት ለማስለቀቅ ዋንጫውን በምትፍቅበት ጊዜ ዋንጫው ራሱ እንዳይሰበርብህ ተጠንቀቅ፡፡ ለዚህ ሁሉ ስራ አንተ አስቀድመህ መዘጋጀት አለብህ፡፡

ስለ እምነትህ መልስ ለመስጠት ሲባል ጥናት ማድረግ ለምን አስፈለገ? የሚል ጥያቄ ይነሳ ይሆናል፡፡ ስለ እምነትህ መልስ ለመስጠት ራስህን እንድታዘጋጅ የሚያስገድዱህ በርካታ ምክንያቶች አሉ፤ እስቲ ከዚህ የሚከተሉትን እንመልከት፡-

1ኛ-    ከሁሉ በላይ እምነታችንን በገርነት እና በጨዋነት እንድንከላከል መጽሐፍ ቅዱስ ያዘናል (1ኛ ጴጥ 3፡15)

2ኛ-    እምነታችንን ለመከላከል የምናደርገው ጥረት የበለጠ ስለእምነታችን እንድናውቅ ያደርገናል፡፡ በሚያሳዝን ሁኔታ በርካታ ክርስትያኖች ጠለቅ ያሉ የክርስትና ትምህርት እውነታዎችን ቀርቶ መሰረታዊ የክርስትና አስተምህሮዎችንም ቢሆን በሚፈለገው ልክ አያውቁም፡፡ ከዚህ በተነሳ ቀለል ባለ አቀራረብ ለወንድሞቻቸው ማካፈል ስለማይችሉ ወንድሞቻቸው ሌሎች ቤተ-እምነቶችን ሲቀላቀሉ በእነርሱ ላይ ከመፍረድ የዘለለ ሐዋርያዊ ስራ ለመስራት አይችሉም፡፡

3ኛ-    ስለ እምነታችን የመመስከር ኃላፊነት ሰዎችን ወደ እግዚአብሔር መንግስት የመመለስ ኃላፊነት ነው፡፡ ክርስትያኖች ሆነን ሳለ የወንጌልን መልካም ዜና እንዳልሰሙ ሰዎች መኖር አይገባንም፡፡ ስለ ክርስቶስ አዳኝነት መመስከር ያስፈልጋል፡፡ ሥራ ፈት ክርስትያኖች መሆን የለብንም፡፡ ሰዎች ከኃጢአት እንዲቆጠቡ መምከር የእኛ ኃላፊነት ነው፤ በዚህ ዓይነት ግኑኝነት ውስጥ ከተለያየ የሕይወት አቅጣጫ የሚመጡት ሰዎች ለሚያነሷቸው የተለያዩ ገለፃ ማድረግ የግድ ነው፤ ይህንን በልበ ሙሉነት ሊያደርገው የሚችለው ደግሞ የተዘጋጀ ማንነት ያለው ሰው ነው፡፡

4ኛ-    የመገናኛ ብዙሃን በተለያዩ ጊዜያት የቤተክርስቲያንን ገጽታ ጥላሸት በመቀባት ሰዎች በቤተክርስትያን ላይ ተዓማኒነት እንዳያሳድሩ የከፈቱትን ዘመቻ መቃወም ያስፈልጋል፡፡ ይህ በዘመናዊ መልኩ የሚፈጸመው ኢ-ክርስትያናዊ ተግባር መልስ ሊያገኝ ይገባዋል፡፡ እኛ ለዚህ ጉዳይ መልስ የማንሰጥ ከሆነ ሰዎች በቤተክርስትያን ላይ ያላቸው እምነት ውሎ አድሮ መጥፋቱ አይቀርም፤ ስለዚህ በዚህ ዙርያ እምነታችንን መከላከል እና ትክክለኛውን የክርስትና ምስል ማንጸባረቅ ያስፈልጋለ፡፡

5ኛ-    እምነታችንን የበለጠ ባወቅን ቁጥር እውነትን የበለጠ እናውቃለን፤ በዚህም መሰረት በዚህ ተለዋዋጭ በሆነ ዓለም ውስጥ ለሚነሱ የጊዜው ጥያቄዎች መልስ መስጠት የምንችለው እውነቱን በተረዳን መጠን ነው፡፡ “ከጊዜው ጋር አብረን መጓዝ” በሚል ምክኒያት በተለያዩ አብያተ ክርስቲያናት መሰረታዊ የወንጌል አስተምሕሮዎች ሲለወጡ ታዝበናል፡፡ ይህ ክስተት በእኛ ቤተክርስቲያ ቢፈጠር መልሳችን ምንድነው? ለምሳሌ የተመሳሳይ ፆታ ጋብቻ ወ.ዘ.ተ. በዚህ ዘመን የቤተክርስቲያን ጠንካራ ተግዳሮት ናቸው፡፡ እነዚህን ዓይነት ሁኔታ ውስጥ ስንገኝ ማድረግ ያሉብንን ነገሮች ለማወቅ እምነታችንን በሚገባ ማወቅ፤ መንከባከብ እና ማሳደግ ይጠበቅብናል፡፡

6ኛ-    በአሁኑ ጊዜ በርካታ የተሳሳቱ ትምህርቶች የቤተክርስቲያን አባላትን ግለሰባዊ ድክመቶ እየፈለጉ እንደ ማስረጃ እየተጠቀሙ አማኞችን ያስታሉ፡፡ ሰዎች ሁሉ የራሳቸው ዓለም ውስጥ እግዚአብሔር አምላክ ሆነው መኖር እንደሚችሉ፤ ምሥጢረ ስላሴ የሚባል ነገር አለመኖሩን፤ ገሃነመ እሳት የሚባል ነገር አለመኖሩን፤ 144000 የተመረጡ ነፍሳት ብቻ ወደ መንግስተ ሰማያት እንደሚገቡ፤ ኢየሱስ አምላክ እንዳልሆነ እና ከሞት እንዳልተነሳ ወ.ዘ.ተ. በማስተማር በርካታ አማኞች ከእውነተኛይቱ ቤተክርስቲያን እቅፍ ነጥቀው እየወሰዱ ይገኛሉ፡፡ ሊቀ ሐዋሪያት ቅዱስ ጴጥሮስ ስለዚህ ጉዳይ ያስጠነቅቀናል “ንቁ፤ ባላጋራችሁ ዲያብሎስ የሚውጠውን ፈልጎ እንደሚያገሳ አንበሳ በዙርያችሁ ያደባልና” (1ኛጴጥ 5፡8)፡፡ ስለዚህ ለእነዚህ የተሳሳቱ ትምህርቶች ተገቢውን ምላሽ በመስጠት ወንድሞቻችንን የማዳን ኃላፊነት አለብን፡፡

7ኛ-    ኢ-ክርስቲያናዊ እና ኢ-ግብረገባዊ የሕይወት ዘይቤ መስፋፋት፡፡ ይህ ማኅበራዊ ቀውስ ለክርስትናም ይተርፋል፡፡ ሰው ኃጢአት የሚባል ነገር በፍጹም እንደሌለ አድርጎ ኑሮውን በጭፍን ቀጥሏል፡፡ በእግዚአብሔር ሕላዌ የሚያምኑ እና የመንጌልን የምስራች ቃል የሰሙት ሳይቀሩ ኢ-ክርስቲያናዊ የሆነ፤ ለግል ጥቅም እና ምቾት ብቻ የሚጨነቅ፤ ለሌሎች ሰዎች መሰረታዊ ፍላጎቶች ደንታ የሌለው ሕይወት በመኖር ላይ ይገኛሉ፡፡ ከራሳቸው የምቾት አጥር በላይ ምንም አይታያቸውም፡፡ የትዳር መሰረታዊ ለዘላለሙ አብሮ የመኖር ቃልኪዳን ክብሩን አጥቷል፡፡ የትዳር መፍረስ፤ ፍቺ፤ የኮንትራት ጋብቻ፤ ውርጃ ወ.ዘ.ተ.  በከፍተኛ ሁኔታ በማህበረሰቡ ውስጥ ዘልቀው ገብተዋል፡፡ ስለዚህ የእኛ ውጊያ ከእነዚህ የክፋት ኃይሎች ሁሉ ጋር ነው፡፡ በዘመናችን የክፋት ኃይሎች ሹክሹክታ ከጌታች ወንጌል የበለጠ ተቀባይነት አግኝቷል፡፡ እኛም ተስፋ ሳንቆርጥ ስለ እርሱ መዋጋት አለብን፡፡ “በቀረውስ ወንድሞች ሆይ፤ እውነተኛ የሆነውን ነገር ሁሉ፤ ጭምትነት ያለበትን ነገር ሁሉ፤ ፅድቅ የሆነውን ነገር ሁሉ፤ ንጹህ የሆነውን ነገር ሁሉ፤ ፍቅር ያለበትን ነገር ሁሉ፤ መልካም ወሬ ያለበትን ነገር ሁሉ፤ በጎነት ቢሆን፤ ምስጋና ቢሆን፤ እነዚህን አስቡ” (ፊሊጶ 4፡8)፡፡

8ኛ-    የትምህርት ተቋሞቻችን የክርስትና እሴቶች ተቃዋሚ እየሆኑ ነው፡፡ በከፍተኛ የትምህርት ተቋሞቻችን ውስጥ የወጣት ተማሪዎችን ክርስቲያናዊ ስብዕና የሚሸረሽሩ በርካታ ነገሮች መሽገዋል፡፡ የወጣቶች ፆታዊ ግብረገብ በብዙ መልኩ ይፈተናል፤ የከፍተኛ ትህርት ተቋማት ውስጥ የክርስትና እሴቶችን በመሸርሸር በምትኩ ትልልቅ የኮንዶም፤ የወሊድ መቆጣጠርያ መድኃኒቾችን የሚያስተዋውቁ የማስታወቂያ ሰሌዳዎችን በመትከል የክርስትናን አስተምሕሮ በይፋ ይቃወማሉ፡፡ ወጣቶች ቀስ በቀስ የክርስትናቸውን እሴቶች ወደ ጎን አየተዉ ይመጣሉ፡፡ በዚህ ሁኔታ ውስጥ ትምህርታቸውን ለሚከታተሉ ወጣቶች ከሌሎች ወጣቶች የተለየ ክትትል ያስፈልጋቸዋል፤ እነርሱም የእምነታቸውን አብይ ቁምነገር በሚገባ ማጥናት እና ማሰላሰል አለባቸው፡፡ በዚህ አይነት ለሚገጥሟቸው ማህበራዊ፤ ስነልቦናዊ እና ሃይማኖታዊ ተግዳሮቶች ተገቢውን ምላሽ ለመስጠት ዝግጁ ይሆናሉ፡፡

ምንጭ፡ “የእምነት ቀናኢነት፣ ካቶሊካዊት እምነትን ማወቅ፣ መጠበቅ እና መንከባከብ፥ ካቶሊካዊ እምነታችንን ለሌሎች ማካፈል” በሚል አርዕስት የአዲስ አበባ ካቶሊካዊ ሰበካ የሐዋርያዊ አገልግሎት ማስተባበሪያ ጽ/ቤት በ2010 ዓ.ም ካሳተመው መጽሐፍ ከገጽ 3-5 ላይ የተወሰደ።

 

30 November 2023, 15:17