ፈልግ

በቅድስት አገር ለሰላም የቀረበ የጸሎት ሥነ-ሥርዓት በቅድስት አገር ለሰላም የቀረበ የጸሎት ሥነ-ሥርዓት  (AFP or licensors)

የአውሮፓ ጳጳሳት የእስራኤል እና የሃማስ ጦርነት ለማስቆም የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረግ ተማጸኑ

በቅድስት አገር እየተፈጸመ ያለውን ጥቃት በመቃወም አውሮፓ ውስጥ የሚገኙ የአብያተ ክርስቲያናት መሪዎች፥ ሁሉም የፖለቲካ መሪዎች በሁሉም አቅጣጫ የተኩስ አቁም ስምምነት የማረጋገጥ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል። ይህ በእንዲህ እንዳለ የዮርዳኖስ አብያተ ክርስቲያናት መሪዎች፥ ሥቃይ ውስጥ ከሚገኙት ሰዎች ጎን ለመቆም በማሰብ የብርሃነ ልደቱን ክብረ በዓል መሰረዛቸውን አስታውቀዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

አውሮፓ ውስጥ የሚገኙ የአብያተ ክርስቲያናት መሪዎች በቅድስት አገር የሚካሄደውን ጦርነት በማስመልከት ባወጡት መግለጫ፥ “በሕይወት ላይ የሚደርስ ጥፋት ነፃነት፣ እውነት እና ፍትህ እንዳይኖር ያደርጋል” የሚለውን እውነታ በማጉላት፥ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ዓለም አቀፍ ሕግን በማጠናከር ውጤታማ የሆኑ የሰላም ድርድሮች እንዲካሄዱ ጠይቀዋል።

የአውሮፓ ጳጳሳት ምክር ቤት (ሲሲኢኢ) እና የአውሮፓ አብያተ ክርስቲያናት ጉባኤ (ሲኢሲ) የጋራ ኮሚቴ ምክር ቤት በመካከለኛው ምሥራቅ ያለውን ሁከት በማውገዝ ጥቅምት 27 ባወጡት መግለጫ፥ “ሁሉም የፖለቲካ መሪዎች በሁሉም አቅጣጫ የተኩስ አቁም ስምምነትን የማረጋገጥ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ” በማለት ጥሪያቸውን አቅርበዋል።

መግለጫው አክሎ እንዳስታወቀው፥ “አሸባሪዎች ለፍርድ እንዲቀርቡ፣ የሁሉም ሲቪሎች፥ የአይሁዶች፣ የክርስቲያን እና የሙስሊም ማኅበረሰቦች ደኅንነት እንዲጠበቅ፣ ሰብዓዊ ዕርዳታ እንዲደርሳቸው፣   እንክብካቤን ወደሚደረግላቸው ሥፍራ የሚያደርስ የመተላለፊያ መንገዶች እንዲከፈቱ” በማለት ጠይቋል።

መግለጫው በመቀጠልም፥ “ጋዛ ውስጥ የሚገኙ ሰዎች የሚኖሩበት ሁኔታ፣ መሠረታዊ መብታቸው ተገድቦ ኢ-ፍትሐዊ ድርጊት እንዲፈጸምባቸው የተገደዱበት አሳሳቢ ሁኔታ ረጅም ጊዜን አስቆጥሯል” ብሏል። "በእውነት እና በፍትህ ላይ ዘላቂ ሰላምን ለመፍጠር ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ዓለም አቀፍ ሕግን በተለይም የተባበሩት መንግሥታት የውሳኔ ሃሳቦችን እንዲያበረታታ እና እንዲያከብር እንጠይቃለን" ብሎ፥ “ጠንካራ ድርድር በእውነት እና በፍትህ ላይ ዘላቂ ሰላምን ለመፍጠር ያለመ መሆን አለበት" ብሏል።

በሁለቱም በኩል ከባድ ስቃይ ደርሷል

የአብያተ ክርስቲያናት መሪዎች፥ የሐማስ አሸባሪ ቡድን መስከረም 26/2016 ዓ. ም. በእስራኤል ላይ የፈጸመውን ጭካኔያዊ ጥቃት በማውገዝ ለተጎጂዎች እና ቤተሰቦቻቸው ያላቸውን ርህራሄ ገልጸው፥ እንዲሁም “የቅኝ ግዛት፣ ፀረ-ሴማዊነት እና በሙስሊሞች ላይ ያለው የጥላቻ ስሜት ታሪካዊ አውድ አሁን ወደሚታየው ሁኔታ እንደመራ” እና በዚህ ግጭት በሁለቱም ወገኖች ላይ የደረሰውን ከፍተኛ ስቃይ አምነዋል። "በእስራኤል እና በፍልስጤም ውስጥ ሰላምን ለማስፈን ከሚጥሩት ጋር ለመተባበር ጽኑ ፍላጎት አለን፤ ሁከት ችግሩ የሚወገድበት መንገድ ሊሆን አይችልም" በማለት ጽፈዋል።

የሁለት ግዛት የመፍትሄ ሃሳብ

አውሮፓ ውስጥ የሚገኙ የአብያተ ክርስቲያናት መሪዎች በመጨረሻም፥ ስቃይ ውስጥ ለሚገኙት በሙሉ ምእመናኑ እንዲጸልዩ ጋብዘው፣ የእግዚአብሔርን ምሕረት በመማጸን እና ሁሉም ሰው አንድ የጋራ ስብዕና ብቻ እንዳለው በማስታወስ፥ ለሁሉም ጥቅም ሲባል “ሁለት-ግዛት” የሚል የመፍትሄ ሃሳብን እንደሚደግፉት ገልጸዋል።

በተጨማሪም ሥልጣን ላይ የሚገኙ የአገራት መሪዎች፥ የሁሉንም ሰው ሰብዓዊ ክብር የሚያስከብር እውነተኛ ውይይት እንዲያደርጉ እንደሚጸልዩላቸው እና ተስፋ እንደሚያደርጉ በመግለጽ፥ “ሁለቱም ሕዝቦች በሁለት ግዛቶች ውስጥ በሰላም አብረው መኖር ይቻላሉ" ብለዋል።

ዘንድሮ ዮርዳኖስ ውስጥ የብርሃነ ልደቱ በዓል አይከበርም

በዮርዳኖስ የሚገኘው የአብያተ ክርስቲያናት መሪዎች ምክር ቤት በመግለጫው፥ ሥቃይ ውስጥ የሚገኙትን በማስታወስ ዘንድሮ ሊከበር የታሰበው የብርሃነ ልደቱ በዓል መሰረዙን አስታውቋል። ክብረ በዓሉ በጸሎት እና በቤተ ክርስቲያን ውስጥ በሚቀርቡ የጸሎት ሥነ-ሥርዓቶች ላይ ብቻ የተገደበ ሲሆን፥ መጪው እሁድ የሚሰበሰብ የቤተ ክርስቲያን ምጽዋዕት በሙሉ በጋዛ ሰርጥ ለሚሰቃዩ ሕዝቦች ይውላሉ ብሏል።

በዮርዳኖስ የሚገኙ አንዳንድ አብያተ ክርስቲያናት ለዚሁ ዓላማ በተዘረጉ ይፋዊ መስመሮች ምእመናን ዕርዳታቸውን እንዲልኩ በማበረታታት፣ የሃይማኖት መሪዎች የሰላም እና የስምምነት ጸሎት እንዲያቀርቡ ጥሪያቸውን አቅርበው፥ “በሁሉም አብያተ ክርስቲያናት ዘንድ መጭው እሁድ ለሰላም እና ለስምምነት ጸሎት ይደረጋል" ብሏል።

 

09 November 2023, 14:35