ፈልግ

የፍልስጤም እና የእስራኤል ጦርነት የፍልስጤም እና የእስራኤል ጦርነት  (AFP or licensors)

ፓትርያርክ ፒየርባቲስታ፥ “ችግር ላይ ለወደቁት አጋርነታችንን የምንገልጽበት ጊዜው አሁን ነው”

በኢየሩሳሌም የላቲን ሥርዓተ አምልኮን የምትከተል ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ብጹዕ ካርዲናል ፒየርባቲስታ ፒዛባላ በሐማስ ታጣቂዎች እና በእስራኤል ወታደሮች መካከል እየተካሄደ ያለውን ጦርነት በማስመልከት ቃለ ምልልስ አድርገዋል። “ሎዜራቫቶሬ ሮማኖ” ከተሰኘ የቅድስት መንበር ዕለታዊ ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፥ ጋዛ ውስጥ በሚገኝ የሐማስ ታጣቂ ቡድን እና በእስራኤል መካከል ከተቀሰቀሰ አንድ ወር ያስቆጠረውን ጦርነት በማስመልከት በሰጡት አስተያየት፥ “ችግር ላይ ለወደቁት ሰዎች አጋርነታችንን የምንገልጽበት ጊዜ አሁን ነው” ብለዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

"በሁለቱ ወገኖች መካከል የተፈጠረው ግጭት ተወግዶ ሰላም እንደሚወርድ ተስፋ አደርጋለሁ። ነገር ግን ይህን እውን ለማድረግ ረጅም ጊዜ እና ከፍተኛ ጥረትን ይጠይቃል" ያሉት ብፁዕ ካርዲናል ፒየርባቲስታ ፒዛባላ ከአንድ ወር በፊት የተጀመረውን የሐማስ እና የእስራኤል ጦርነት በማስመልከት ቃለ ምልልስ አድርገዋል። ጦርነቱ ሲቀሰቀስ ጣሊያን ውስጥ እንደ ነበሩ የሚያስታውሱት ፓትርያርኩ፥ በመኪና ረጅም እና አስቸጋሪ ጉዞ በማድረግ ወደ ኢየሩሳሌም መግባታቸውን ገልጸዋል።    

ወደ ኢየሩሳሌም ሲደርሱ የመጀመሪያዎቹ ጥቂት ቀናት አስቸጋሪ እንደ ነበሩ የሚገልጹት ብፁዕ ካርዲናል ፒየርባቲስታ ፒዛባላ፥ በአካባቢው የሚሆኑትን ነገሮች ለማየት እና ለመረዳት ከመሞከር በተጨማሪ የማኅበረሰቡን ደህንነት ማረጋገጥ እና በጋዛ ያሉ ክርስቲያኖችን ለመርዳት የተለያዩ መንገዶችን ሲፈልጉ መቆየታቸውን ገልጸዋል። በከፍተኛ ጉዳት ውስጥ እንደሚገኙ የሚናገሩት ብፁዕ ካርዲናል ፒየርባቲስታ፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እንደተናገሩት ሰላም እንዲመጣ ጥረት ማድረግ ማለት ገለልተኛ መሆን ማለት እንዳልሆነ ገልጸው፥ ነገር ግን በእነዚህ የህመም እና የቁጣ ጊዜያት ውስጥ ይህን ሁሉም ሰው እንዲረዳው ማድረግ ከባድ እንደሆነ አስረድተዋል።

ከአብያተ ክርስቲያናት የሚወጡ የተወሰኑ መግለጫዎችን ተከትሎ የተፈጠረውን ውዝግብ በማስመልከት እንደተናገሩት፥ ከሁለቱም ወገኖች ወቀሳ እንደደረሳቸው ገልጸው፥ መጀመሪያ ላይ የክስተቶቹን ስፋት ለመረዳት ቢቸገሩም ነገር ግን ከሁሉም ጋር በድጋሚ ከመወያየት ወደ ኋላ እንደማይሉ አስታውቀዋል።

ጋዛ ውስጥ በሚገኝ ሆስፒታል ላይ የተፈጸመው ጥቃት እና የሃማስ ታጣቂዎች በእስራኤላውያን ላይ የፈጸሙት ጥቃት በእርግጥ ዘግናኝ እና አስደንጋጭ እንደ ነበር የሚገልጹት ብፁዕ ካርዲናል ፒየርባቲስታ፥ በኢየሩሳሌም ለ 34 ዓመታት መኖራቸውን ገልጸው፥ በእነዚያ ዓመታት ውስጥ በዚያች አገር በርካታ ነገሮች እንዳጋጠማቸው እና ሁሉም በአንድ ሰው ላይ ሊደርሱ የሚችሉ ናቸው ተብለው የሚገመቱ እንዳልሆኑ አስረድተዋል።

ባለፉት ዓመታት ውስጥ በቅድስት አገር ሆነ ከሌላው ዓለም ውስጥ ብዙ ግንኙነቶችን ማድረጋቸውን የሚገልጹት ብፁዕ ካርዲናል ፒየርባቲስታ፥ በፖለቲካው ዓለም ሳይሆን ነገር ግን በሰዎች መካከለ የሚፈጠር ግንኙነት፣ በፍልስጤማውያን እና እስራኤላውያን መካከል ስላለው ግንኙነት እንደሆነ ተናግረው፥ ይህም በድንገት ወደማይቻል ደረጃ መድረሱን ገልጸዋል። ሕይወትን በሙሉ ለመልካም ማኅበራዊ ግንኙነት በመሥራት እና በማስተባበር ከቆዩ  በኋላ ግጭቶች እና ቅራኔውች ሲፈጠሩ ለማስታረቅ አለመቻል አሳዛኝ ነው ያሉት ብፁዕ ካርዲናል ፒየርባቲስታ፥ አመክንዮ ሲፈርስ ልዩ ልዩ ስሜቶች ቦታውን እንደሚረከቡ ገልጸው፥ ለጥቃት የተዘጋጀ ክፉ ፈተና ሲያጋጥም፥ በሰይጣን ፊት አቅም እንደሌለ ሊሰማ ይችላል ብለዋል። ይህን በመሰለ ችግር መካከል አንድ ክርስቲያን እንዴት ሊኖር ይችላል በማለት የጠየቁት ብፁዕ ካርዲናል ፒየርባቲስታ፥ ሰዎች የቅርብ እርዳታን ስለሚገልጉ፥ የመጽናኛ ቃልን እንደሚጠብቁ እና ክርስቲያኖች ሕይወታቸውን ከክፉ መንፈስ ጋር እየተዋጉ ስለሚኖሩ ድጋፍንእየሰጡ አብሮአቸው መሆን እንደሚጋባ አስረድተዋል።

ለሀገረ ስብከታችው ሐዋርያዊ መልዕክት መጻፋቸውን የተናገሩት ብፁዕ ካርዲናል ፒየርባቲስታ፥ ሐዋርያዊ መልዕክታቸው በሀገረ ስብከታቸው ውስጥ ለሚገኙት ወንድም እና እህቶች ብቻ ሳይሆን በግል ለራሳቸውም እንደሚያስፈልግ የተሰማቸው መሆኑን አስረድተው፥ ይህ ሐዋርያዊ መልዕክታቸው   ሃሳባቸውን በማደራጀት የግል ሚናቸውን እና የክርስቲያኖችን ሚና ለመረዳት እንደሚያግዛቸው ገልጸዋል። ቅድስት አገር ውስጥ ክርስቲያን መሆን እንደ አውሮፓ ውስጥ አይደለም ያሉት ብፁዕ ካርዲናል ፒየርባቲስታ፥ ክርስትና በቅድስት አገር ውስጥ የባለቤትነት ምልክት እንደሆነ እና በሕይወት ዘመን በሙሉ አብሮ የሚጓዝ የሕይወት መንገድ መሆኑን ተናግረዋል።

በቅድስት አገር ውስጥ የሚገኙ ክርስቲያኖች በተለያየ እውነታ ውስጥ እንደሚገኙ የገለጹት ብፁዕ ካርዲናል ፒየርባቲስታ፥ ከሦስቱ የአብርሐም መሠረት ካላቸው ሃይማኖቶች መካከል ሰዎችን በማንነታቸው የማትለይ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ብቻ እንደሆነች ገልጸው፥ በእስራኤል በኩል ሆነው ጋዛ ውስጥ የሚገኙ ካቶሊክ ወታደሮች እንዳሉ እና እነሱም ቢሆኑ የምዕመናኖቻቸው አካል እንደሆኑ አስረድተው፥ እንደዚሁም ከአይሁድ ማኅበረሰብ የሆኑ የውጭ አገር ዜጎች እና ስደተኛ ሠራተኞች መኖራቸውን ገልጸው፥ ልዩነቶች ቢኖሩም አንድነትን ለመጠበቅ ተጨማሪ ድፍረትን እንደሚጠይቅ አስረድተዋል።

በካኅናቱም መካከል የተለያዩ እውነታዎች እንዳሉ የሚገልጹት ብፁዕ ካርዲናል ፒየርባቲስታ፥ ሁሉም ሰው ሃሳቡን እንዲገልጽ መፍቀድ አስፈላጊ እንደሆነ ተናግረዋል። ለሀገረ ስብከታቸው ምዕምናን የላኩት ሐዋርያዊ መልዕክታቸው መጀመሪያ እና መደምደሚያ መሠረቱ ቅዱስ ወንጌል እንደሆነ ገልጸው፥ ምናልባት በዚህ ዓይነት አቋም መልዕክታቸውን ሁሉም ሰው በሚገባ ባይረዳውም ወይም ባይቀበለውም ነገር ግን እውነትን መናገር እና ቅዱስ ወንጌልን መሠረት ማድረግ አስፈላጊ እንደሆነ አስገንዝበው፥  በመጀመሪያ ደረጃ ክርስቲያኖች እንደ መሆናችን እንደ ክርስቲያን እንዴት መኖር እንዳለብን እራሳችንን መጠየቅ አለብን ብለዋል።

ቶሎም ይሁን ዘግይቶ ጦርነቱ እንደሚያበቃ የተናገሩት ብፁዕ ካርዲናል ፒየርባቲስታ፥ መዘዙ በጣም አስከፊ እንደሚሆን ተናግረው፥ በተለይ ሁለት የሚያስጨንቋቸው ጉዳዮች እንዳሉ፥ የመጀመርያው ሁለቱም ወገኖች አንዱ ሌላውን ለማጥፋት ከመሞከር ባለፈ ስልታዊ ራዕይ የሌላቸው መሆኑ እና ግጭቱ ከተቀሰቀሰበት ጊዜ አንስቶ ሁለቱም ሕዝቦች በከባድ እልቂት እራሳቸውን ስሜት ውስጥ በማስገባት መራራቃቸው እንደሆነ አስረድተዋል። እስራኤል ለዓመታት ያህል ኢኮኖሚያዊ ዕድገትን ያሳየች አገር እና የምዕራቡ ዓለም አኗኗር ግጭቱን ወደ ዳራ እንዲገፋ ያደረገ መሆኑን ግምት ውስጥ ማስገባት እንደሚያስፈልግ እና በተለይ እጅግ ትንሽ አገር በሆነች እስራኤል ውስጥ የ1,400 ሰዎች ሞት እጅግ ብዙ መሆኑን ማሰብ ያስፈልጋል ብለዋል።

 

08 November 2023, 14:39