ፈልግ

የእስራኤል የአየር ጥቃትን ተከትሎ በሰሜናዊ የጋዛ ሰርጥ የታየ ጭስ የእስራኤል የአየር ጥቃትን ተከትሎ በሰሜናዊ የጋዛ ሰርጥ የታየ ጭስ  

በዩ. ኪንግደም የሚገኙ ጳጳሳትና የክርስቲያን ድርጅቶች በጋዛ የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረግ ጠየቁ

የእንግሊዝ እና የዌልስ የካቶሊክ ጳጳሳት ጉባኤ የዩናይትድ ኪንግደም መንግስት በጋዛ የሰብአዊ ተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረግ እና ሁሉም ታጋቾች በአስቸኳይ እንዲፈቱ የሚደረጉትን ጥረቶችን እንዲያሳድግ በማሳሰብ መግለጫ አውጥቷል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

የእንግሊዝ እና የዌልስ ጳጳሳት የዓለም አቀፉ ጥሪ በሆነው “በቅድስቲቱ ምድር ፍትህ እና ሰላም ይስፈን፣ የህዝቡም ስቃይ ይቁም” በሚለው ላይ የራሳቸውን ድምፅ አክለው አሰምተዋል።

የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረግ እና ታጋቾች ነጻ እንዲወጡ ዲፕሎማሲያዊ ጥረት እንዲደረግ የቀረበ ጥሪ

ጥቅምት 26 ቀን 2016 ዓ.ም. በተለቀቀው መግለጫ፣ የእንግሊዝ እና የዌልስ የካቶሊክ ጳጳሳት ጉባኤ የዓለም አቀፍ ጉዳዮች መምሪያ ኃላፊ የሆኑት ሊቀ ጳጳስ ዲላን ላንግ እና የቅድስት ሃገር ማስተባበሪያ ሃላፊ የሆኑት ሊቀ ጳጳስ ኒኮላስ ሁድሰን፥ የብሪታንያ መንግሥት የእስራኤል-ሃማስ ጦርነት እንዲቆም እና የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደርግ፣ ሁሉም ታጋቾች በአስቸኳይ እንዲፈቱ እንዲሁም ሰብአዊ እርዳታን በማመቻቸት በጣም አስፈላጊ የሆኑ የምግብ፣ የውሃ፣ የነዳጅ እና የህክምና አቅርቦቶች ወደ ጋዛ በሰላም እንዲደርሱ ዲፕሎማሲያዊ ጥረት እንዲያደርግ አሳስበዋል።

በጋዛ ካሉ ወንድሞች እና እህቶች ጋር መቀራረብ

ጳጳሳቱ “በቅድስት ሀገር ዙሪያ ካሉ ወንድሞች እና እህቶች በተለይም በጋዛ የቅዱስ ቤተሰብ አጥቢያ ቤተክርስቲያን ተጠልለው ካሉ እንዲሁም ዌስት ባንክ ከሚገኙት ወንድሞች እና እህቶች” ጋር ያላቸውን ቀጣይነት ያለው ቅርርብ ገልጸዋል ። በእንግሊዝ እና በዌልስ የሚገኙ የካቶሊክ ማህበረሰቦች በቅድስት ሀገር በተለይም ለታገቱት፣ ለተገደሉት፣ ጉዳት ለደረሰባቸው እና ለቤተሰቦቻቸው ጸሎት እንዲያደርግ ጠይቀዋል። በተጨማሪም “በመንግሥት ሥልጣን ላይ ያሉት በሰላምና በፍትሕ መንገድ የሚመራቸውን ጥበብ እንዲያገኙ” እንጸልያለን ብለዋል።

ለቅድስት ሀገር ሰላም የክርስቲያን ድርጅቶች ተነሳሽነት

የእንግሊዝ እና የዌልስ የካቶሊክ ጳጳሳት ጉባኤ መግለጫ ባለፈው ሳምንት በእንግሊዝ እና ዌልስ ውስጥ የሚገኙ ካቶሊክ ቤተክርስቲያናት ኦፊሴላዊ የእርዳታ ኤጀንሲ የሆነው ‘ካፎድ’፣ የክርስቲያን በጎ አድራጊ ድርጅቶች እና ሌሎች ድርጅቶች አንድ ላይ በመሆን 300,000 ፊርማዎችን በማሰባሰብ ለውጭ ጉዳይ ቢሮ ያቀረቡትን የተኩስ አቁም ስምምነት አቤቱታ ተከትሎ ነው።

የኢንግላንድ እና የዌልስ ፓክስ ክሪስቲ ንቅናቄዎች (ፓክስ ክርስቲ ዓለም አቀፍ የካቶሊክ የሰላም ንቅናቄ ነው) በበኩላቸው በቅድስት ሀገር ሰላም እንዲሰፍን ዘመቻ እያደረጉ ነው። ይህ የካቶሊክ ንቅናቄ በየምሽቱ ሻማ በማብራት እና ጦርነቱ እንዲያበቃ መጸለይን እንዲሁም በክልሉ ላሉ ሁሉ ፍትህ እንዲመጣ በየትምህርት ቤቶች፣ በየአጥቢያዎቹ ባሉ ማህበረሰቦች ውስጥ የሰላም ጥሪዎችን ማደራጀት፣ የጸሎት ካርዶችን ማደል እንዲሁም ለፓርላማ አባላት የሰላም መልዕክቶችን መላክ እና ሌሎች ተነሳሽነቶች ጨምሮ በርካታ ድርጊቶችን እያከናወነ ይገኛል።

በዌስት ባንክ፣ በጋዛ፣ በእስራኤል እና በዮርዳኖስ ላሉ የክርስቲያን ማህበረሰብ በጸሎት እና በተግባራዊ ፕሮጄክቶች ድጋፍ የሚያደርገው እና በዩናይት ኪንግደም የተመሰረተው የቅድስት ምድር ወዳጅ ድርጅት በኢየሩሳሌም የሚገኙትን የካቶሊክ ቤተክርስቲያ የላቲን ሥርዓት ተከታይ ፓትርያርክን እየደገፈ ይገኛል። ፓትርያርክ ፒየርባቲስታ ፒዛባላ ለሀገረ ስብከታቸው፣ በጋዛ ለሚገኙ ሰዎች እና በቅድስት ሀገር እየተካሄደ ያለው ጦርነት ባስከተለውን መዘዝ ምክንያት ለሚሰቃዩ ሰዎች ሁሉ እርዳታ እንዲደረግላቸው ተማጽነዋል።
 

09 November 2023, 13:58