ፈልግ

2023.09.05 Santa Madre Teresa di Calcutta

በኢትዮጵያ የሚገኘው የቅድስት እማሆይ ተሬዛ ማህበር 50ኛ ዓመቱን አከበረ!

በኢትዮጵያ የሚገኘው የቅድስት እማሆይ ተሬዛ የፍቅር ሥራ ልኡካን ማህበር 50ኛ ዓመቱን አከበረ በደማቅ ሥነ ስርዓት አከበረ። በቅድስት እማሆይ ተሬዛ በ1966 ዓ.ም. አዲስ አበባ ላይ በተለምዶ ስድስት ኪሎ ተብሎ በሚጠራው አከባቢ የተቋቋመው የፍቅር ሥራ ልኡካን ማህበር ‘ሚሽነሪስ ኦፍ ቻሪቲ’ የሰላም ንግስት ቤት የሚባለው በጎ አድራጊ ድርጅት 50ኛ ዓመት የምስረታ በዓል የወርቅ ኢዩቤልዩውን ዛሬ ዕለተ ሐሙስ ህዳር 13/2016 ዓ.ም. በደማቅ ሥነ ስርዓት አክብሯል።

አዘጋጅ እና አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ አዲስ አበባ

ቅድስት እማሆይ ተሬዛ ነሐሴ 26/1910 ዓ.ም. (እ.አ.አ.) ስኮፕጄ ተብላ በምትጠራ መንደር በሜቄዶንያ ግዛት የተወለዱ ሲሆን፥ ከሶስት ወንድሞችና እኅቶች እሳቸው የቤቱ መጨረሻ ልጅ ነበሩ።

ቤተሰባቸው ከአልቤኒያ የሚመዘዘው እማሆይ ተሬዛ በአስራ ሁለት ዓመታቸው ግድም ከአምላክ ጥሪ እንደደረሳቸው እና የአምላካቸውንም መልእክት ለማስተላለፍ ሚሽነሪ መሆን እንዳለባቸው እንዳመኑ ይነገራል። አስራ ስምንት ዓመት ሲሞላቸው ስኮፕጄ የነበረውን የቤተሰባቸውን ቤት በመልቀቅ ህንድ ውስጥ ከሚገኝ የአይሪሽ ካቶሊክ እህትማማች ሚሽነሪዎች ጋር ተቀላቀሉ። የተወሰነ ትምህርት አየርላንድ ውስጥ ከወሰዱ በኋላ እ.አ.አ. በግንቦት 24 1931 ዓ.ም የእማሆይነት ዘመናቸውን ጀመሩ።

ሚሽነሪስ ኦፍ ቻሪቲ በቅድስት እማሆይ ተሬዛ እ.አ.አ. በ1950 ዓ.ም. በህንድ ካልካታ የተመሰረተ ሲሆን ከጊዜያት በኋላ በተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች አገልግሎትን በማስፋት በ140 ሃገራት ላይ ቅርንጫፎቹን ከፍቶ ዘርፈ ብዙ ሥራ እየሰራ ይገኛል።

ቅድስት እማሆይ ተሬዛ ከዛሬ 50 ዓመት በፊት ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት ያቋቋሙት የሚሽነሪስ ኦፍ ቻሪቲ ዛሬ ላይ ደርሶ 50ኛ ዓመት የምስጋና በዓሉን በተለያዩ ሥነ ስርዓቶች አክብሯል።

በሥነ ስርዓቱም ላይ ብጹዕ ካርዲናል አቡነ ብርሃነኢየሱስ ሊቀ ጳጳሳት ዘካቶሊካዊያን የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዚዳንት፣ የቫቲካን ኤምባሲ ዋና ጸሃፊ፣ ክቡር ሼህ ዶ/ር ሃጂ ኢብራሂም ቱፋ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት፣ ክቡር አምባሳደር ምስጋኑ አረጋ የውጭ ጉዳዮች ምንስትር ዴኤታ፣ ከተለያዩ ሃገራት ኤምባሲዎች የመጡ ተወካዮች፣ የተለያዩ ሃገረ ስብከቶች ጳጳሳት፣ ካህናት እና ደናግል፣ ምእመናን፣ እንዲሁም የተለያዩ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

ብጹዕ ካርዲናል አቡነ ብርሃነኢየሱስ ሥነ ስርዓቱን በጸሎት ያስጀመሩ ሲሆን፥ ብዙ የተቸገሩ ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን በዚህ ቦታ ከዛሬ 50 ዓመት ጀምሮ የተራቡት፣ የተጠሙት፣ የታረዙት እና የታሰሩት ሁሉ በቅድስት እማሆይ ተሬዛ አማካይነት እንዲጎበኙ ስላደረገ አምላካችንን ማመስገን አለብን ብለዋል።

 የኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ጠቅላይ ጽ/ቤት ዋና ጸሃፊ የሆኑት ክቡር አባ ተሾመ ፍቅሬ (ዶ/ር) መድረኩን በመምራት የተለያዩ መልዕክቶችን ያስተላለፉ ሲሆን፥ ቅድስት እማሆይ ተሬዛ በህይወት እያሉ እጅግ አብልጠው የሚወዱት እና ለአገልግሎታቸው መነሻ የሆነውን የወንጌል ክፍል ማለትም የማቴዎስ ወንጌል 25፥ 31 ለታዳሚያን አንበበዋል። ክቡር አባ ተሾመ ቅድስት እማሆይ ተሬዛ የሰው ልጅ ትልቁ ድህነት የቁስ፣ የመራብ፣ የመታረዝ ድህነት ሳይሆን፥ ትልቁ የሰው ልጅ ድህነት የመገፋት፣ ፍቅርን የማጣት እና የመናቅ ድህነት ነው ይሉ እንደነበር በማስታውስ፥ እኛም በህይወት ዘመናችን የሳቸውን ፈለግ ተከትለን ለሰው ልጅ በአጠቃላይ ፍቅርን ማሳየት መለማመድ እንደሚገባን አስገንዝበዋል።

ሚሽነሪስ ኦፍ ቻሪቲ በአሁኑ ሰዓት በኢትዮጵያ በሚገኙ ሁሉም ክልሎች ላይ 18 ቅርንጫፎችን በመክፈት በጣም የተጎዱ እና መጠጊያ የሌላቸውን አቅመ ደካሞችን እንዲሁም ህሙማንን በመንከባከብ ዘርፈ ብዙ ሥራዎችን በመስራት ላይ እንደሚገኝ ተነግሯል።

የበዓሉ ታዳሚዎች የቅዱስ ፍራንቺስኮን የሠላም ጸሎትን በመጸለይ የአዳራሹ መርሃ ግብር የተጠናቀቀ ሲሆን፥ በሚሽነሪስ ኦፍ ቻሪቲ እህቶች ብሄር እና ሃይማኖት ሳይለይ ልዩ እንክብካቤ የሚደረግላቸው ከተለያዩ የሃገሪቱ ክፍል የመጡ ህሙማን ተኝተው የሚታከሙበትን የገዳሙ የህክምና ማዕከል በእንግዶች ተጎብኝቷል። በመጨረሻም በገዳሙ የተዘጋጀውን የቅድስት እማሆይ ተሬዛን የህይወት ታሪክ የሚዳስስ የፎቶ አውደ ርዕይ ጉብኝት ከተደረገ በኋላ በበዓሉ ላይ ለተገኙት እንግዶች የተዘጋጀውን የምሳ ግብዣ በመካፈል መርሃግብሩ ተጠናቋል።

ቅድስት እማሆይ ተሬዛ ከዚህ ዓለም ድካም ካረፉ ከሁለት ዓመት ባነሰ ጊዜ ውስጥ ሕይወታቸው እንዲጠና ብለው ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ሁለተኛ በጠየቁት መሠረት አስፈላጊው ሂደት ከተጠናቀቀ በኋላ ጥቅምት 6 ቀን 1996 ዓ. ም. የእማሆይ ተሬዛ ብጽዕና ይፋ ሆነ። በዕለቱም ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ዮሐንስ ጳውሎስ ሁለተኛ ባሰሙት ንግግር “እማሆይ ተሬዛ የመጨረሻ ደሃ በሆኑት ሰዎች መካከል በመገኘት እነርሱን በማፍቀር፣ እገዛቸውንም ለማቅረብ ታጥቀው መነሳታቸው በግል ዘወትር ይሰማኝ ነበር፣ በተለያዩ አካባቢዎች የሚከሰቱ አመጾችና ጦርነቶች ለድሆች የሚያቀርቡትን አገልግሎት ሊያደናቅፍ አልቻሉም፣ የመረጡት የሕይወት አቅጣጫ ከሁሉ አንሰው መገኘትን ብቻ ሳይሆን የድሆች አገልጋይ ሆኖ መገኘትንም ጭምር ነበር፣ ለእርሳቸው ትልቅ መሆን ማለት ሌሎችን ለመርዳት ስትነሳ የምትችለውን ሁሉ በምንም ሳትለካውና ሳትቆጥር አሳልፎ መስጠት ነበር፣ ሕይወታቸውም ቆራጥነት የታከለበት የወንጌል ምስክርነት ነበር” ማለታቸው ይታወሳል። 

 

24 November 2023, 10:45