ፈልግ

በጋዛ ከተማ የእስራኤል የአየር ጥቃትን ተከትሎ የተራቆተው ጎዳና ላይ የወዳደቀ ፍርስራሽ በጋዛ ከተማ የእስራኤል የአየር ጥቃትን ተከትሎ የተራቆተው ጎዳና ላይ የወዳደቀ ፍርስራሽ  (ANSA)

በጋዛ የሚኖር ወጣት ካቶሊካዊ ቤቱ በጥቃቱ ቢወድምበትም ስለ ሰላም ብዬ እጸልያለሁ አለ

የጋዛ ነዋሪ የሆነው የ18 ዓመቱ የካቶሊክ ምእመን ሱሃይል አቦዳውድ የቤተሰቦቹ ቤት በእስራኤል የአየር ጥቃት ከወደመ በኋላ ቤተክርስቲያን እውነተኛ የመኖሪያ ሥፍራው እንደሆነ ተናግሯል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

ጥቅምት 12, 2016 ዓ.ም. ሰኞ እለት ሱሃይል አቦዳውድ በጋዛ በምትገኘው ቅዱስ ቤተሰብ ካቶሊካዊት ቤተክርስትያን (ሆሊ ፋሚሊ) ሰበካ ውስጥ ተጠልሎ በነበረበት ወቅት ለቅድስት ሀገር ሠላም እንዲወርድ የጸሎት መልእክት ጽፎ ነበር። ይህን የሰላም መልዕክት ከፃፈ ከሁለት ቀናት በኋላ ጥቅምት 14, 2016 ዓ.ም. ረቡዕ ዕለት በእስራኤል የአየር ጥቃት መኖሪያ ቤቱ መውደሙ ተዘግቧል።

ከሌሎች 700 ሰዎች ጋር በተጠለለበት ደብር ሥርዓተ ቅዳሴ ለመካፈል ከመግባቱ በፊት ነበር መኖሪያ ቤቱ ላይ ጥቃት እንደተፈፀመ መልእክት የደረሰው።

መንፈሳዊ ቤት

አቦዳውድ ለቫቲካን ዜና እና ለሌላኛው የዜና ድርጅት ለሆነው ኦዘርቫቶሬ ሮማኖ በሰጠው ማስታወሻ ላይ በቤተሰባቸው መኖሪያ ቤት ላይ በደረሰው ውድመት ያለውን የግል አስተያየት ገልጿል። በማስታወሻው ላይም “መጀመሪያ ላይ በጣም ከማዘኔ ምክንያት ተስፋ ቆርጬ ነበር። ከዚያ በኋላ ግን ሕይወታችን ከማንኛውም ነገር የበለጠ አስፈላጊ እንደሆነ ተገነዘብኩ” ሲል ጽፏል። “ተጀምሮ በነበረው ሥርዓተ ቅዳሴ ላይ አጥብቄ ወደ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጸለይኩ፥ የደረሰብኝን ጭንቀት ለመቋቋም እንድችል የበለጠ ጥንካሬ እና እምነት እንዲሰጠኝ ጠየቅሁት” ብሏል።

አቦዳውድ ምድራዊ መኖሪያውን ካጣ በኋላ እውነተኛ ቤቱን እና ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ያለውን ግንኙነት ፈጽሞ እንደማያጣ ተገነዝቧል። ይህንንም በማስመልከት “ሁሉም ነገር ቢኖርህም ቅድስት ቤተ ክርስቲያን የመጀመሪያና የመጨረሻ ቤቴ እንደሆነች አስባለሁ እናም አምናለሁ” ብሏል። በማከልም “ምድራዊ ቤቴ ከተደመሰሰ በኋላ ቤተክርስቲያን እውነተኛው ቤቴ ሆኗል” በማለት ገልጿል።

ስለ ሰላም እና ፍትህ መጸለይ

ወጣት አቦዳውድ እና በሆሊ ፋሚሊ ቤተ ክርስቲያን የተጠለሉ ፍልስጤማውያን ብዙ ጊዜያቸውን በጸሎት ያሳልፋሉ፣ አብዛኛውን ቀናት በቀን ሁለት ጊዜ የቅዳሴ ሥነስርዓት ላይ በመገኘት እና የቅድስት ድንግል ማርያም ጥበቃ እንዳይለያቸው አዘውትረው በትጋት እየጸለዩ ይገኛሉ።  “እምነት ከጦርነት የበለጠ ጠንካራ ነው” በማለት እሱና በደብሩ ስር ተጠልለው የሚገኙ ሌሎች ነዋሪዎች “በቅድስት ሀገራችን ሰላምና ፍትህ እንዲሰጠን አምላክን እየለመን ነው” ብሏል።

የእሱ ደብር ካህን የሆኑት አባ ገብርኤል ሮማኔሊ እንደተናገሩት የቁምስናቸው ምዕመናን በሙሉ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ለዓለማችን ሰላም እንዲወርድ ጥቅምት 16, 2016 ዓ.ም. ዕለተ ዓርብ የጾም እና የንስሐ ቀን እንዲሆን ባስተላለፉት የጸሎት ጥሪ መሰረት እንደሚሳተፉ ገልጸዋል።

ወጣት አቦዳውድ መልዕክቱን ሲያጠቃልል “ተስፋ እና ቁርጠኝነት ከማንኛውም ጦርነት የበለጠ ጠንካራ ነው” በማለት ያለውን ጽኑ እምነት ገልጿል።

በመጨረሻም “አሁንም በህይወት እስካለን ድረስ እግዚአብሔር ስላደረገልን ነገር ሁሉ መጸለይ፣ መጾም እና ማመስገናችንን እንቀጥላለን” ብሏል።
 

27 October 2023, 12:51