ፈልግ

በደቡባዊ ጋዛ ሰርጥ የአየር ጥቃትን ተከትሎ የፍለጋ ስራዎች በደቡባዊ ጋዛ ሰርጥ የአየር ጥቃትን ተከትሎ የፍለጋ ስራዎች  (ANSA)

የጋዛ ህፃናት በላኩት ቪዲዮ ስለ ሰላም በመጸለይ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስን አመስግነዋል

በጋዛ የሚገኘው የሆሊ ፋሚሊ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሰበካ ልጆች ጦርነቱ እንዲያበቃ አባታችንን እና ሰላምታ ለማርያም ጸሎት እየጸለዩ ባለበት ሠዓት የቦምብ ፍንዳታ ድምፅ ከበስተጀርባ የሚሰማ ቪዲዮ ቀርፀው ልከዋል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

በጋዛ የሚገኘው የቅዱስ ቤተሰብ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሰበካ ምእመናን ጦርነቱ እንዲያበቃ እና ለሁሉም ሰላም እንዲወርድ አጥብቀው እየጸለዩ ይገኛሉ። ይህ ጥቅምት 17, 2016 ዓ.ም. ዕለተ ቅዳሜ የተቀረፀው ቪዲዮ ከበስተጀርባው ቦንብ ሲፈነዳ ይሰማል። እንደሚታወቀው የቁምስናው ግቢ ለብዙዎች መጠለያ ፈላጊዎች የማረፊያ ቦታ ሆኖ እያገለገለ ይገኛል። ይህንን በማስመልከት በአሁኑ ጊዜ ቤተልሔም ከተማ ያሉት እና ጋዛ መድረስ ያልቻሉት የደብሩ ካህን የሆኑት አባ ገብርኤል ሮማኔሊ “እግዚአብሔር ይመስገን ሁሉም ሰው ደህና ነው” ብለዋል። አሁን ላይ ረዳት የሰበካ ካህን በሆኑት አባ ዩሱፍ አሳድ በኩል መረጃ እየደረሳቸው እንደሆነም ተናግረዋል።

የቦምብ ድምፅ

በጋዛ ውስጥ አንዳንድ የበይነ መረብ ግንኙነት መቆራረጥ ጋር እየታገሉ መረጃ በሚልኩ ሰዎች እንደተረጋገጠው ነዋሪዎች አሁንም ድረስ ለሰው ልጅ እጅግ አስፈላጊ የሆኑት እንደ ምግብ፣ መድሃኒት እና ንጹህ ውሃ እንዲሁም የስልክ እና የበይነ መረብ አገልግሎቶች እንደሌሉ ተነግሯል። በተመሳሳይ መልኩ፥ በቁምስናው ውስጥ የተጠለሉት ህፃናት ብዙ ጭንቀት እና መከራ ቢያጋጥማቸውም ስላላቸው ተስፋ እየመሰከሩ መሆናቸውንም አባ ገብርኤል ተናግረዋል።

ህጻናቱ ለርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ እና ስለ ሰላም ለሚጸልዩት ሁሉ ይሄንን ቪዲዮ ቀርፀው ልከዋል። ይህ የሁለት ደቂቃ ቪዲዮ በተለያዩ የእድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ልጆች የመስቀል ምልክት እያደረጉ አባታችን ሆይን፣ ጸጋ የሞላሽንን እና ‘በጥበቃሽ ሥር’ የተሰኘውን ጸሎት ሲፀልዩ ያሳያል።

ጥቅምት 16, 2016 ዓ.ም. ዕለተ ዓርብ ስለተደረገው ለዓለማችን ሰላም የጸሎት፣ የጾም እና የንስሐ ቀንን በማስመልከት ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳትን በማመስገን ጸልየውላቸዋል። ቪድዮው የሚያልቀው ለሁሉም የመዝጊያ ሰላምታ በመስጠት ሲሆን፥ ከበስተጀርባው ደግሞ የቦምብ ፍንዳታ በግልጽ ይሰማ ነበር።
 

30 October 2023, 15:52