ፈልግ

አባ ኢብራሂም ፋልታስ አባ ኢብራሂም ፋልታስ 

አባ ፋልታስ 'ር.ሊ.ጳ. ፍራንቺስኮስ በቅድስት ሀገር የተኩስአቁም ጥሪ ያቀረቡ ብቸኛው መሪ ናቸው'አሉ

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ እሁድ ዕለት በሥም ጠቅሰው ያነሷቸው በእየሩሳሌም የቅድስት ሀገር ጠባቂ ቤተክርስቲያን ካህን የሆኑት አባ ኢብራሂም ፋልታስ የጋዛን ሕዝብ ፍላጎት ማንም ምንም ባላለበት ወቅት በእስራኤል እና በሐማስ መካከል እየተደረገ ላለው ጦርነት የተኩስ አቁም ጥሪ በማቅረባቸው ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳትን አመስግነዋል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

   “የተኩስ አቁም ስምምነት ይደረግ ፥ እኛም እንደ አባ ኢብራሂም የተኩስ አቁም ይደረግ እንላለን” ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ እሁድ ዕለት በተደረገው የመልአከ እግዚያብሄር ጸሎት ሥነ ስርዓት ወቅት የቅድስት ሀገር ጠባቂ ቤተክርስቲያን ካህንን በቀጥታ በመጥቀስ በመካከለኛው ምስራቅ የተኩስ አቁም ጥሪውን እንዲቀላቀሉ ከመላው ዓለም የተውጣጡ ምእመናንን ጋብዘዋል።

የግብፅ ተወላጅ የሆኑት የፍራንቺስካዊያን መነኩሴ አባ ኢብራሂም ፋልታስ በርዕሰ ሊቃነ ጳጳሱ በመወሳታቸው ደስታ እንደተሰማቸውተናግረዋል። ካህኑ ለቫቲካን ዜና እንዳብራሩት በርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ስለተጠቀሱ ብቻ ሳይሆን “በዚህ ዓለም ውስጥ ካሉት ኃያላን ሰዎች መካከል ቅዱስ አባታችን ብቻ ናቸው ‘የተኩስ አቁም’ የሚለውን ቃል የተጠቀሙበት እና ጦርነት ለሁሉም ወገን ሽንፈት እንደሆነ የገለፁት። እነዚህን ጥሪዎች ያቀረቡት ጳጳሱ ብቻ ናቸው” ብለዋል።

'ማንም አይሰማም'

አባ ፋልታስ በቅርቡ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ብዙ ጊዜ እንደገለፁት አዘውትረው የሚከታተሉት ‘በእሱ ምስል’ (A Sua Immagine) በተባለ የጣሊያን የቴሌቪዥን ፕሮግራም ላይ ቀርበው ነበር። ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ቤተክርስቲያኒቷ ስላስተላለፈችው መልዕክት መደነቃቸውን በቴሌቭዥን መስኮት ሆነው በዓለም ዙሪያ ባካፈሉት ንግግር ገልፀዋል ። ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ በንግግራቸው አራት ጊዜ “የተኩስ አቁም ስምምነት ይደረግ” ብለዋል።

አባ ኢብራሂም ኢየሩሳሌም ከሚገኘው ቤተክርስቲያናቸው ሆነው ሲናገሩ “ቅዱስ አባታችንን ማመስገን እፈልጋለሁ” ብለዋል ሌሎች “ምድራችን ላይ የሚገኙ ኃያላን ሰዎች” ይህንን ጩኸት መስማት አለመፈለጋቸውን በማየታቸው ደግሞ ምስጋናቸውን መራር ያደርገዋል። ይሄን ሲገልፁም “ማንም ሰው ይሄን ጩኸት አልሰማም፤ ቤት የሌላቸው፣ ያለ ምግብ፣ ያለ መብራት፣ ያለ ውሃ፣ ያለ ምንም ነገር እየኖሩ ያሉ የእነዚህን የጋዛ ሰዎች ፍላጎት የሚሰማ የለም” ብለዋል አባ ፋልታስ።

በጋዛ የሞቱ፣ የተጎዱ እና የወደሙ ቤቶች

“በጦርነቱ የተገደሉ ህጻናት፣ ሴቶች፣ አካል ጉዳተኞች አሉ። በ24 ቀናት ውስጥ ከ10,000 በላይ ሰዎች ተገድለዋል። በጋዛ ከተማ በፈረሱት ቤቶች ሥር በጣም ብዙ ህጻናት፣ ብዙ ሴቶች አሉ፥ እነዚህ ሰዎች እንዴት መረዳት እንዳለባቸው ማንም አያውቅም። ለመኖር እጅግ አስፈላጊ የሆኑትን ነገሮች ጨምሮ በጋዛ ውስጥ የሁሉም ነገር እጥረት አለ፥ ከ20,000 በላይ የሆኑ የቆሰሉ ሰዎች ህክምና ማግኘት ስለማይችሉ የመዳን ተስፋቸው የተመናመነ ነው። ይሄ ሁሉ እየሆነ ግን የተኩስ አቁም ጥሪ እየጠየቁ ያሉት ቅዱስ አባታችን ብቻ ናቸው፥ እርሳቸው ብቻ፥ ጥሪያቸውን እንደሚሰሟቸው ተስፋ አደርጋለሁ!” ብለዋል አባ ኢብራሂም።

በ ‘ሆሊ ፋሚሊ’ ደብር ውስጥ ያሉ ወደ 700 የሚጠጉ ሰዎች

ይህ በእንዲህ እንዳለ በጋዛ ሰርጥ የእስራኤል የምድር ጦር ጥቃት እየተጠናከረ በመጣበት እና ሰብአዊ ሁኔታው እየተባባሰ በሄደበት በዚህ ጊዜ የአንዳንድ ነዋሪዎች የኢንተርኔት ግንኙነት ወደ ነበረበት መመለሱን መረጃዎች ያመለክታሉ። በመሆኑም አባ ኢብራሂም ፋልታስ በጋዛ ቅዱስ ቤተሰብ ደብር ውስጥ ተጠልለው የሚገኙትን ወንድሞቻቸውን እና እህቶቻቸውን ለማግኘት እድሉን ተጠቅመውበታል። ይህንንም አስመልክተው “አዎ የኢንተርኔት ግንኙነቱ ተመልሷል ሆኖም ግን ይቆራረጣል፥ የተረጋጋ አይደለም” ሲሉ አስረድተዋል። በማከልም “እዛ ካሉት ገዳማዊያን መካከል ከሲስተር ነቢላ ሳሌህ፣ ከሆሊ ሮዛሪ ደናግላን እና ከአባ ዮሴፍ ጋር ለመነጋገር የምችለውን ሁሉ አድርጌያለሁ” ብለዋል።

“እነዚህ ገዳማዊያን ጋዛ ውስጥ በጠና ከታመሙት ሰዎች ጋር ነው ያሉት። ወደ 700 የሚጠጉ ሰዎች ደብራቸው ውስጥ ተጠልለዋል፥ እነዚህ ሰዎች የሚተኙትም፣ የሚበሉትም፣ የሚኖሩትም እዚያው ነው” በማለት ገልፀዋል።

'ገሃነም ሆኖባቸዋል' 

“እስኪ አስቡት 700 የሚሆኑ ሰዎች በአንድ ቤተክርስቲያን ውስጥ፣ ያውም መላው ጋዛ በእስራኤል ጦር ተከቦ ባለበት!” በማለት አባ ፋልታስ በግርምት ተናግረዋል። “ያለ ምግብ፣ ያለ መብራት፣ ያለ ውሃ፣ ያለ መድሃኒት፣ ምንም ነገር ሳይኖር በጋዛ ውስጥ ሁለት ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎች እየኖሩ ይገኛሉ፥ እዚያ ያለው ነገር በጣም አሰቃቂ ሁኔታ ነው፥ ግን ማን ይሰማቸዋል? እነዚህን ነገሮች ማን ያያቸዋል?” በማለትም ጠይቀዋል።

ፍራንችስካዊያኑ ካህን ባለፈው ጥቅምት 17, 2016 ዓ.ም. ቅዳሜ ዕለት በጎዳናዎች ላይ የተደረጉትን ሰልፎች በማስታወስ፥ "በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች 'ይህ የሲኦል ኑሮ' እንዲያበቃ መሪዎቻቸው የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲያደርጉ ጠይቀዋል። በእርግጥም ገሃነም ነው! የጋዛ ሰዎች በገሃነም ውስጥ እየኖሩ ነው፥ እኛም በመላው ቅድስት ሀገር የምንኖር ሰዎች እጅግ በጣም አስቸጋሪ ጊዜ እያሳለፍን እንገኛለን፥ ለሁሉም ሰው የገሃነም ያክል ነው” በማለት ሃሳባቸውን አጠቃለዋል።
 

30 October 2023, 14:22