ፈልግ

ብፁዕ ካርዲናል አምቦንጎ መከረም 26 በተካሄደው የሲኖዶስ መግለጫ ላይ ጋዜጠኞችን ሲያነጋግሩ ብፁዕ ካርዲናል አምቦንጎ መከረም 26 በተካሄደው የሲኖዶስ መግለጫ ላይ ጋዜጠኞችን ሲያነጋግሩ 

ብፁዕ ካርዲናል አምቦንጎ ሲኖዶሳዊነት የቤተ ክርስቲያንን አዲስ መንገድ የሚያሳይ ነው አሉ።

በሲኖዶሱ ጠቅላላ ጉባኤ ማጠቃለያ ላይ የኮንጎው ካርዲናል ፍሪዶሊን አምቦንጎ ለቫቲካን ዜና እንደተናገሩት ሲኖዶሳዊነት “የቤተክርስቲያንን አዲስ መንገድ የሚያሳይ ነው” ካሉ በኋላ ይህም የካቶሊክ እምነት እሴት የሆኑትን አስፈላጊ ነገሮች ችላ ሳንል መንፈስ ቅዱስን እና እርስ በርሳችን ማዳመጥ አስፈላጊ መሆኑን ያሳያል ብለዋል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

በ16ኛው የጳጳሳት ሲኖዶስ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ የመጀመሪያ ጉባኤ ማጠቃለያ ላይ የኪንሻሳው ብፁዕ ካርዲናል በሲኖዶሱ ሂደት መደሰታቸውን ገልጸዋል። የአፍሪካ እና ማዳጋስካር ጳጳሳት ጉባኤዎች ሲምፖዚየም (SECAM) ሊቀ መንበር የሆኑት ብፁዕ ካርዲናል ፍሪዶሊን አምቦንጎ ቤሱንጉ ከቫቲካን ዜና ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፥ ስለ መጨረሻው ማጠቃለያ ዘገባ፣ ስለ አፍሪካ ቤተ ክርስቲያን ተሳትፎ እና ስለ ወደፊቷ ቤተክርስቲያን ሲኖዶሳዊ ጉባኤ ትርጉም ማብራሪያ ሰጥተዋል። እንደሚከተለው ቀርቧል፦

ጥያቄ፡- በዚህ ሲኖዶስ መጨረሻ ላይ ያለዎትን ልምድ እንዴት ይገልጹታል?

መልስ፦ በዚህ ሲኖዶስ መጨረሻ ላይ ይህን ልዩ ልምድ እንድወስድ የፈቀደልኝን ጌታ ከሁሉ በፊት ማመስገን እፈልጋለሁ፥ እኔ የሲኖዶስ ጉባኤ ላይ ስሳተፍ ይህ አራተኛው ነው፥ ነገር ግን ይህ ሲኖዶስ ለእኔ ልዩ ነበር ማለት እችላለሁ።

ጥያቄ፦ በምን መልኩ ልዩ ነበር?

መልስ፦ በመጀመሪያ ደረጃ በአወቃቀሩ ልዩ ነበር። የጳጳሳት ሲኖዶስ ይባል እንጂ ተሳታፊዎቹ ግን ጳጳሳት ብቻ አልነበርንም። ምእመናን፣ ሴቶች፣ ወጣቶች፣ ከእህት አብያተ ክርስቲያናት የተውጣጡ ልዑካን ነበሩ፥ ይህም ያልተለመደ ድባብን ፈጥሯል። ሌላው እውነታ ደግሞ ከወትሮው በእጥፍ በዝተናል። ስለዚህ በአዲሱ የሲኖዶስ አዳራሽ ከመሰብሰብ ይልቅ ስብሰባችንን በጳውሎስ ስድስተኛ አዳራሽ አድርገናል።
ነገር ግን ይህን ሲኖዶስ በይበልጥ የሚገልጸው ነገር በውይይቱ ወቅት የተጠቀመበት ዘዴ ነው፥ በመንፈስ ቅዱስ የተመራ የውይይት ዘዴ ነበር፥ ስብሰባዎች፣ በጸሎት ወቅት የነበሩ የሃሳብ ልውውጦች፣ የማሰላሰያ ጊዜያት፣ እና ፀጥታው፥ ይህ ሁሉ ከዚህ በፊት ሆኖ የማያውቅ ነው። እርስ በርሳችንን በጸጥታ ውስጥ ሆነን ስንደማመጥ በእውነትም መንፈስ ቅዱስን መስማት የምንችልበት ሁኔታ ውስጥ ያስገባናል።

ጥያቄ፡- በዚህ ሲኖዶስ ጉባኤ ላይ በንቃት ተሳትፌያለው ይላሉ? ይህ ሲኖዶስ ለቤተ ክርስቲያን ምን አዲስ ነገር ያመጣል ወይም ወደ ቤተ ክርስቲያኒቷ ሕይወት ምን ሊያመጣ ይችላል?

መልስ፦ በእኔ እይታ ይህ ሲኖዶስ ለቤተክርስቲያናችን አዳዲስ አመለካከቶችን ይዞ ይመጣል እላለሁ። ሲኖዶስ ስሙ ራሱ እንደሚያመለክተው ሲኖዶሳዊነት ነው። ይህ ማለት አንድ ነገር በጊዜ ሂደት መለወጥ እንዳለበት ቤተክርስቲያን ተረድታለች። በሲኖዶስ ላይ ያለው ሲኖዶሳዊነት እርስ በእርስ መፈላለግ ነው፥ ዛሬ መንፈስ ቅዱስን ማዳመጥ የተለየ ቤተ ክርስቲያን ለመሆን ይረዳል፥ ይህም አንድን ቤተ ክርስቲያንን ቤተክርስቲያን የሚያደርገው ዋና ነገር ነው። በሌላ አነጋገር እጅ ለእጅ ተያይዘን በመንፈስ ቅዱስ እየተመራን ልዩ የሆነች ቤተ ክርስቲያን እንድንሆን፣ ማንንም ወደ ጎን የማትተው ነገር ግን የሚነሱትን ዋና ዋና ሃዋሪያዊ ተግዳሮቶችን የምትፈታ ቤተ ክርስቲያን የምንሆንበትን መንገድ መፈለግ ነው። እርስ በርስ የምትሰማማ እና መንፈስ ቅዱስን የምታዳምጥ ቤተክርስቲያን መሆን አለባት።

ይህ አይነቱ ሲኖዶስ ወደ ግለሰባዊ ለውጥ የሚያመራ ቢሆንም እንደ ቤተ ክርስቲያን በኅብረት መለወጡ የማይቀር ነው። ይህ ሲኖዶስ የቤተክርስቲያንን አሠራር እና ህልውናን በእጅጉ ይለውጣል።

ጥያቄ፦ እርስዎ ወደ ድህረ-ሲኖዶስ ምክረ ሃሳብ ለመድረስ የመጀመሪያው ደረጃ የሆነውን የአጠቃላይ ሪፖርት አርቃቂዎች ውስጥ አንዱ ነዎት። ለዚህ ሰነድ ምን ዓይነት ዋጋ እና አስፈላጊነት መሰጠት አለበት ይላሉ? ይህ ሰነድ እስከሚቀጥለው ጥቅምት 2017 ዓ.ም. ላይ እስከሚካሄደው የሲኖዶስ ጉባኤ ድረስ ብቻ የሚቆይ ነው?

መልስ፦ አሁን የሚወጣው የማጠቃለያ ሪፖርት ሁለት የታቀዱ ተቀባዮች አሉት። የመጀመርያው በሮም፣ ቫቲካን ለአንድ ወር ያህል ቆይተን ስንወያይ ሲከታተሉን የነበሩ የእግዚአብሔር ቤተሰብ ናቸው። እኛ ያደረግነውን፣ የተነጋገርነውን፣ አንድ ወር የፈጀው ስብሰባ ውጤት ምን እንደሆነ የማወቅ መብት አላቸው። በዚህ የውይይት ወቅት የሆነውን ለሰዎች ለማሳወቅ ጥንቃቄ አድርገናል።

ሁለተኛው ተቀባይ ግን በሲኖዶሱ የመጀመሪያ ስብሰባ ላይ የተሳተፍነው እኛ ነን። ይህ ሰነድ ከአሁን ጀምሮ እስከ ጥቅምት 2017 ዓ.ም. ድረስ ያለውን ጊዜ እንድናልፍ እና ለሁለተኛው የሲኖዶስ ክፍለ ጊዜ እንድንዘጋጅ ይረዳናል። በመሆኑም ይህ ሰነድ የሽግግር ሰነድ ነው።ቀጥሎ ሁለተኛው ጉባኤ ስላለ ይህ የሲኖዶሱ የመጨረሻ ሰነድ አይደለም። ነገር ግን በዚህ የሽግግር ጊዜ ውስጥ እንድንኖር የሚረዳን የሽግግር ሰነድ ነው፥ የሆነውን ሁሉ ለእግዚአብሔርን ሕዝብ በተሻለ ሁኔታ ለማሳወቅ፣ እንዲሁም ለሁለተኛው ክፍለ ጊዜ ስንመለስ ውይይቶቹን የሚያበለጽጉ አዳዲስ ነጥቦችን ይዘን እንመጣለን ብለን ተስፋ በማድረግ ነው።

ጥያቄ፡- ሲኖዶሱ የታቀዱትን ጥያቄዎች በሙሉ ያነሳ ይመስሎታል ወይስ ያልተነሱ ጥያቄዎች ነበሩ?

መልስ፦ በዚህ ነጥብ ላይ አንድ ነገር ግልጽ ማድረግ እፈልጋለሁ፥ ይህ ሲኖዶስ ዓላማ ነበረው፡ የዘንድሮው ሲኖዶሱ ስለ ሲኖዶሳዊነት ነው፥ ልክ እንደ ከዚህ ቀደም በወጣቶች፣ በቤተሰብ ወዘተ ሲኖዶስ ሲደረግ እንደነበረው ማለት ነው። ይህ ሲኖዶስ በእግዚአብሔር ፊት በጸሎት ማንጸባረቅ፣ መንፈስ ቅዱስን መስማት፣ ወንድሞቻችንን እና እህቶቻችንን መስማት፣ አዲሱን የቤተ ክርስቲያንን መንገድ ለማሰላሰል፣ የምትሰማ ቤተ ክርስቲያን፣ ማንንም ችላ ብላ የማትተወው ቤተ ክርስቲያን እና የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስብከት ዋና ጭብጥ የሆነውን ወደ እግዚአብሔር መንግሥት የምትመራ ቤተክርስቲያን እንድትሆን የሚያግዝ ጉባኤ ነበር።

ስለዚህ ወደዚህ ሲኖዶስ ስንመጣ ዓላማው አንዱን ወይም ሌላውን ችግር ለመፍታት አልነበረም። የሲኖዶሱ ዋና ዓላማ፣ አንድ ላይ አዲስ ቤተ ክርስቲያን እንዴት እንደምንሆን፣ እና በመንገዶቻችን፣ በአሠራር መዋቅሮቻችን፣ በትብብር መዋቅሮቻችን ውስጥ የቤተ ክርስቲያንን አዲስ መንገድ እንዴት ማግኘት እንደምንችል ለመወያየት ነው።

ለሁሉም ክፍት የሆነች ግን ለካቶሊክ እምነት አስፈላጊ የሆነውን ነገር የማትጥል ቤተክርስቲያን መሆንን እንዴት እንማራለን? የሚለውን በጥንቃቄ መመለስ አለብን። ስለዚህ፣ የቤተክርስቲያናችን የሆነውን አዲሱን መንገዳችንን ስለማሰላሰል ነው የተሰበሰብነው። እያንዳንዱ ተሳታፊ የሚመለከተው ጉዳይ ስለሆነው ስለ ሃዋሪያዊ ሥራ ተግዳሮቶች ተናግሯል። በተጨማሪም ብዙ ጥያቄዎችን ተወያይተናል፣ ነገር ግን እነዚህ ጥያቄዎች የአስተሳሰባችን ማዕከል አልነበሩም። ለዛም ነው በማጠቃለያ ሰነዱ ውስጥ ጥያቄዎቹን በሦስት ክፍሎች ያዋቀርናቸው፥ በመጀመሪያ፣ ለእያንዳንዱ የሃዋሪያዊ ሥራ ተግዳሮቶች በአዳራሹ ውስጥ ከተነሱት ተያያዥ ነጥቦች ጋር እናያለን። ከዚያም በጥልቀት መታየት ያለባቸው ነጥቦች ደግሞ ይኖራሉ፥ ይህም ማለት ሲኖዶሱ አሁንም ሁለተኛው ጉባኤ ስላለ ጉዳዩን ክፍት አድርጎ ተወው ማለት ነው። ሦስተኛው ክፍል በሲኖዶሳዊ ጎዳና ላይ እንድንራመድ የሚረዱን አንዳንድ ፕሮፖዛሎችን ይዟል። ለእያንዳንዱ የተነሳ ሃሳብ ጉዳዩ ተያያዥነት አለው ወይ የሚሉ ለሁሉም ክፍት የሆኑ ጥያቄዎች ይነሳሉ፣ ከዛም ምን መደረግ እንዳለበት እና ሊሆኑ የሚችሉ ሀሳቦች ላይ ውይይት ይደረጋሉ።

ጥያቄ፦ ሲኖዶሱ ከዓለም አቀፉ ቤተክርስቲያን የተውጣጡ ተሳታፊዎችን አሳትፏል። እነዚህ ተሳታፊዎች የራሳቸውን አስተዋፅዖ አድርገዋል። በእርስዎ አስተያየት የአፍሪካ ቤተክርስቲያን ያበረከተችው አስተዋፅኦ ምን ነበር?

መልስ፦ ‘በአፍሪካ ውስጥ ያለን የቤተክርስቲያን ድምጽ አልሰማንም’ በማለት ጋዜጠኞች መጠየቅ በሚፈልጉት መንገድ ሳይሆን በአፍሪካ ያለው ቤተክርስቲያን ትልቅ አስተዋፅዖ አድርጓል። ወደዚህ ሲኖዶስ የመጣነው የይገባኛል ጥያቄ መንፈስ ይዘን አይደለም፣ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ መጀመሪያ ላይ በአጽንኦት እንደተናገሩት የፓርላማ መንፈስ ይዘን አይደለም የመጣነው። እኛ አፍሪካን ለመወከል ወደ አንድ ጉባኤ የመጣን የአፍሪካ ፓርላማ አባላት አይደለንም። እኛ የዓለም አቀፋዊት ቤተክርስቲያን ልጆች ነን፥ ነገር ግን አንዳንድ ጊዜ ለእኛ ልዩ የሆኑ የሃዋሪያዊ ሥራ ተግዳሮቶች ወይም ፈተናዎች ከሌላው አከባቢ በተለየ ሁኔታ አፍሪካ ላይ ያጋጥሙናል፥ እነዚህን ፈተናዎች ናቸው ወደ እዚህ ያመጣናቸው።

በሲኖዶሱ ወቅት ከእነዚህ ተግዳሮቶች መካከል አንዳንዶቹን በተለይም በወገኖቻችን ላይ እየደረሰ ያለውን መከራ ለማንሳት ሞክረናል። የአፍሪካ አህጉር ብዙ ደስተኛ ያልሆኑ እና ድሆች ያሉበት ቦታ ነው፥ በመሆኑም ወጣቶች በዚህ ሁኔታ ውስጥ መኖር ስለማይቻላቸው ያላቸው አማራጭ አከባቢውን ለቀው መውጣት ብቻ ነው። በተጨማሪም የአየር ንብረት ለውጥ ፈተና አለ። አፍሪካ ለአየር ንብረት ብክለት ምንም አስተዋጽኦ ሳታረግ በውጤቱ እጅግ እየተሰቃየች ያለች አህጉር ናት። በየሀገራችን የመልካም አስተዳደር እጦት ፈተና፣ በመፈንቅለ መንግስት፣ የግል ብልፅግናቸውን ብቻ የሚያስቡ የፖለቲካ መሪዎች ወዘተ የምትሰቃይ አህጉር ናት። ስለዚህ እነዚህን ስጋቶች ከሌላ አህጉር ለሚመጡ ወንድሞችና እህቶች ለማካፈል ሞክረናል፣ በሲኖዶሳዊነት መንፈስ ይህች አህጉር ካለባት ሰቆቃ እንድትወጣ የሚረዳንን መንገድ በጋራ መፈለግ እንችላለን።

ስለዚህ የአፍሪካ ድምጽ በእርግጠኝነት በሲኖዶስ አዳራሽ ተሰምቷል ማለት እንችላለን። ከአፍሪካ የመጣነው ከስልሳ ሰው በላይ የልዑካን ቡድን ነበርን፥ የተቻለንን ተናግረናል፣ ኃላፊነታችንንም ተወጥተናል። ነገር ግን ይህን ያደረግነው ራሳችንን ከሌሎች ለመለየት በማሰብ እንዳልሆነ ደግሜ መናገር እፈልጋለሁ። ምንም እንኳ የአፍሪካዊያን ጉዳይ ብቻ ቢሆኑም ከአንድ በላይ ሚስት ስለማግባት ልምድንም አንስተናል። ሌሎች አፍሪካን ብቻ የሚመለከቱ ጉዳዮችን በሲኖዶሳዊነት መንፈስ ጭምር አንስተን ነበር።

ጥያቄ፡- የአፍሪካ ቤተክርስቲያን ከዚህ ሲኖዶስ ምን ትጠብቃለች? የአፍሪካን ድምፅ ወደ እዚህ አምጥተዋልና በምላሹ በአከባቢ ደረጃ፣ በልዩ አብያተ ክርስቲያናት፣ በአፍሪካ ማህበረሰብ ውስጥ፣ አፍሪካውያን ምን ይጠብቃሉ?

መልስ፦ በመጀመሪያ ደረጃ ሲኖዶሱ ገና ያላለቀ መሆኑን መገንዘብ አለብን። አሁን የመጀመሪያውን ምዕራፍ ነው እየጨረስን ያለነው። ለዚህ ነው በዚህኛው ምዕራፍ የወጣውን ሰነድ የሽግግር ሰነድ ነው ያልነው። በሚቀጥለው ዓመት በጥቅምት ወር ለሁለተኛው ክፍለ ጊዜ እንመለሳለን። በዚያን ጊዜ ነው ጳጳሱ ከሲኖዶሱ በኋላ የውሳኔ ሐሳብ የሚያወጡት። ብጹዕነታቸው መጨረሻ ላይ የሚያወጡት ሰነድ ስልጣን ያለው ይሆናል። እስከዚያው ግን ወደ ሀገሮቻችን እና ወደ ቤተክርስቲያኖቻችን እንደተመለስን በዚህ ሲኖዶስ ውስጥ የተሳተፉት ሁሉ እራሳቸውን እንደ ሚሲዮናውያን እንዲቆጥሩ፣ ጉዳዩን እንዲዘግቡ፣ አብረን አንድ ወር ሙሉ ከወንድሞቻችን እና እህቶቻችን ጋር የቆየንበትን የዚህን የኅብረት፣ የወንድማማችነት ሲኖዶሳዊ ልምድ እንዲያካፍሉ እናበረታታለን። ስለዚህ እኔ ወደ ኪንሻሳ ስመለስ በመጀመሪያ ደርጃ ከሲኖዶሱ ያገኘናቸውን ልምዶች ሪፖርት አደርጋለሁ፥ ከዛም ሌሎች እንዲመጡ እና ከእኛ ጋር ተመሳሳይ ተሞክሮ እንዲኖራቸው ለማሳመን እሞክራለሁ። ይሄን ትልቅ ደስታ፣ እንደ ወንድሞች እና እህቶች፣ እንደ አንድ ቤተሰብ አባላት፣ ትልቅ የእግዚአብሔር ልጆች ቤተሰብ የመኖር ደስታ እንዲካፈሉ እጋብዛለሁ። ስለዚህ እኛ በምላሹ ለሰዎች የምናካፍለው በመጀመሪያ የራሳችን ልምድ ነው፥ በመቀጠልም የአጠቃላይ ሪፖርቱን ይዘት እናካፍላለን።

ጥያቄ፦ ለሰዎች ይህን የሲኖዶስ ውጤት መልሶ የማሳወቅ ዘዴን አስበው ያውቃሉ ወይንስ በጽሁፎች ብቻ ይከናወናል? ለዚህ አሠራር ሌሎች ማዕቀፎች ይኖሩ ይሆን?

መልስ፦ መልሶ የማሳወቅ ዘዴን አስበንበታል፥ ምክንያቱም እንደምታዩት በዚህ ሲኖዶስ ውስጥ በአፍሪካ ያሉ ሁሉም ሃገረ ስብከቶች አልተወከሉም። ለምሳሌ አርባ ስምንት ሃገረ ስብከት ላላት ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ሦስት ጳጳሳት ብቻ ነበርን የተወከልነው። ስለዚህም በመጀመሪያ እኔ የኪንሻሳ ሊቀ ጳጳስ እንደመሆኔ መልሶ የማሳወቁ ሂደት በሀገረ ስብከቴ ደረጃ ይሆናል።

ቀጣዩ ደረጃ በአገር አቀፍ ደረጃ ነው። እንደ የኮንጎ የጳጳሳት ጉባኤ (CENCO) ማዕቀፍ ውስጥ ሆነን ተገናኝተን ስለ አጠቃላይ ሪፖርቱ እንወያያለን። በዛውም በሮም ውስጥ ካሉ ወንድሞቻችን ጋር በነበረን ጊዜ ስላሳለፍነው የሲኖዶሳዊነት ልምዳችንን እናካፍላለን። ከዚህ ስብሰባ በኋላ የኮንጎ ጳጳሳት ጉባኤ በኮንጎ ለሚገኙ ቤተ ክርስቲያናት በሙሉ ሰነዱ እንዲደርሳቸው አንዳንድ መመሪያዎችን ይሰጣል ብዬ አምናለሁ። እንዲሁም በዚህ ሰነድ ውስጥ ያሉትን ነጥቦች ተግባራዊ ለማድረግ የተሻለ ግንዛቤ እና መመሪያ ይሰጣል።

ከሀገር አቀፍ ደረጃ በተጨማሪ አህጉራዊ ደረጃም አለ። በሚቀጥለው ዓመት ከፋሲካ በኋላ ባለው ሦስተኛው ሳምንት ማለትም በሚያዝያ ወር በዚህ ሲኖዶስ ውስጥ ከተሳተፉት ሁሉ እና ከአዳዲስ አባላት ጋር አህጉራዊ ስብሰባ ለማድረግ አቅደናል። ምናልባትም ብፁዕ አባታችን አዳዲስ አባላትን ለመጨመር ከፈለጉ ሁሉንም እንጋብዛቸዋለን፥ በዚህም አንፃር በአህጉር ደረጃ ልምዳችንን፣ ተስፋችንን እና እቅዶቻችንን በሚቀጥለው ዓመት እዚሁ ሮም ውስጥ በሚካሄደው የሁለተኛው ምእራፍ ጉባኤ ላይ ማካፈል እንችላለን።

ጥያቄ፦ ቀረ የሚሉት የመጨረሻ ሀሳቦች አሉ?

መልስ፦ በዚህ ጉባኤ ተሳትፌ ልምድ በማግኘቴ ረክቻለሁ። እናም ይህን ልምድ ካገኘሁ በኋላ ወደ ሀገረ ስብከቴ የምመለሰው በደስታ እና በምስጋና ተሞልቼ ነው፥ ይህ ለእኔ አዲስ ተሞክሮ ነው፥ በአንድነት የምትጓዝ፣ ሁሉንም ወንድ እና ሴት ልጆቿን የምትንከባከብ ቤተክርስትያን፣ እርስ በእርስ የምትደማመጥ ቤተክርስትያን፣ ከሁሉ በላይ በዋነኝነት መንፈስ ቅዱስን የምታዳምጥ ቤተክርስቲያንን ተሞክሮ ነው ያገኘሁት።
 

31 October 2023, 14:27