ፈልግ

በኢንዶኔዥያ ተነስቶ የነበረው የሰደድ እሳት በኢንዶኔዥያ ተነስቶ የነበረው የሰደድ እሳት  (AFP or licensors)

ብጹዕ አቡነ አርኖልድ፥ ለፍጥረታቱ እግዚአብሔርን ማመስገን ጥብቅ ጥሪ መሆኑን ገለጹ

የእንግሊዝ እና የዌልስ ብጹዓን ጳጳሳት፥ የአካባቢ ጉዳዮች በማስመልከት ይፋ የሚሆነው የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ “ውዳሴ ለእግዚአብሔር” የሚለው ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን፥ ወቅታዊ የአየር ንብረት ለውጥ ቀውስን እና የአካባቢ ችግሮችን ለመፍታት የሚያግዝ ተጨማሪ አስቸኳይ ጥሪ መሆኑን ብጹዕ አቡነ አርኖልድ ገለጹ።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የአሲሲው ቅዱስ ፍራንችስኮስ ዓመታዊ የፍጥረት ወቅት በሚጠናቀቅበት ማለትም መስከረም 23/2016 ዓ. ም. በሚከበርበት ወቅት ይፋ የሚሆነው “ውዳሴ ለእግዚአብሔር” የሚለው የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ አዲሱ ሠነድ፥ የጋራ መኖሪያ ምድራችንን እንድንንከባከብ በማለት የጻፉት የመጀመሪያው ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን ተከታታይ ክፍል መሆኑ ታውቋል።

የእንግሊዝ እና የዌልስ ብጹ ዓን ጳጳሳት ጉባኤ የአካባቢ ጉዳዮች ተጠሪ የሆኑት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ጆን አርኖልድ እንደተናገሩት፥ የአካባቢ ጥበቃ እና የአየር ንብረት ለውጥ አደጋን በማስመልከት እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ2015 ዓ. ም. ይፋ የሆነው የመጀመሪያው “ውዳሴ ላንተ ይሁን” ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን  አስደናቂ  ሠነድ እንደሆነ ገልጸው፥ የዚህ ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን ተከታታይ ክፍል ወቅታዊ የአየር ንብረት ለውጥ ቀውስን እና የአካባቢ ችግሮችን ለመፍታት የሚያግዝ ተጨማሪ አስቸኳይ ጥሪ መሆኑን በጳጳሳቱ ጉባኤ ድረ ገጽ ላይ በታተመ የቪዲዮ ቃለ መጠይቅ አብራርተዋል።

በስምንት ዓመታት ውስጥ ዓላማዎቹ አልተሳኩም

ከስምንት ዓመታት በኋላ እና እንዲሁም የአየር ንብረት ለውጥ ቀውስን እና የአካባቢ ችግሮችን ለመፍታት በርካታ ስብሰባዎች ከተካሄዱ በኋላ የተስማሙባቸው ግቦች ሳይሳኩ መቆየታቸውን እና ጉዳቱ እየቀነሰ አለመሆኑን፥ እንዲያውም በአንዳንድ መንገዶች ጉዳቱ እየጨመረ መሆኑን አቡነ አርኖልድ ተናግረዋል። የአየር ንብረት ለውጥን በማስመልከት የአካባቢ ጥበቃ ባለሙያዎች አንዳንድ ትንበያዎችን ቀለል ባለ መልኩ መግለጻቸውን ተናግረው፥ ባለሙያዎች ከሚያስቡት በላይ አሁን ጉዳቱ በፍጥነት እየጨመሩ መምጣቱን አስረድተዋል።

የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ አዲሱ ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን ጠንካራ እና አስቸኳይ ማስጠንቀቂያ እንደሚሰጥ የተናገሩት ብጹዕ አቡነ አርኖልድ፥ አዲሱ ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳኑ ሁላችንም በአስቸኳይ  የበኩላችንን ድርሻ እንድንወጣ ያሳስባል ብለዋል።

“ድርሻችንን የምንወጣባቸው ብዙ ምክንያቶች አሉን” ያሉት ብጹዕ አቡነ አርኖልድ፥ እያንዳንዱ አህጉር በጉዳቱ የተጠቃ መሆኑን ገልጸው፥ ድርቅ እና ወቅቱን ያልጠበቀ የአየር ሁኔታ አገራቸው ውስጥ በሰብሎች ጉዳት ማስከተሉን ገልጸዋል።

ከሰው ሠራሽ የአየር ንብረት ለውጥ በማስመልከት የቀረቡ ሳይንሳዊ ማስረጃዎችን መካድ አይቻልም

በአየር ንብረት ለውጥ እና በሰዎች እንቅስቃሴ መካከል ባለው ግንኙነት ተጠራጣሪ አመለካከት ያላቸውን ሰዎች በተመለከተ፣ አካባቢውን በትክክል የሚያውቁ ሰዎች ያቀረቡትን ማስረጃ መካድ እንደማይቻል ተናግረው፥ “በግልጽ ወደ ጉዳት እየሄድን ነው” በማለት አቡነ አርኖልድ ተናግረዋል።

እኛ የፍጥረት ተንከባካቢዎች ነን

የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስን መልዕክት በመድገም የተናገሩት አቡነ አርኖልድ፥ ቀውሱን ለመቅረፍ ሁላችንም የበኩላችንን ሚና መጫወት አለብን ብለው፥ የኤሌክትሪክ እና የውኃ ፍጆታን ለመቆጠብ የምንወስዳቸው እርምጃዎች ተራ ሊመስሉ እንደሚችሉ ገልጸው፥ እነዚህን ነገሮች በግል ስናያቸው ትንሽ ቢሆኑም ነገር ግን አንድ ላይ ብናከናውናቸው ትልቅ ለውጥ ሊያመጡ እንደሚችሉ ተናግረዋል።

እኛ ማየት ያለብን የሥርዓት ለውጥ እና የቅሪተ አካል ነዳጆችን መጠቀም ማብቃት እንደሚገባ ገልጸው፥ የቅሪተ አካል ነዳጅ በዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ለውጥ ውስጥ አደገኛ ንጥረ ነገር እንደሆነ አስረድተው፥ያለ ቅሪተ አካል ነዳጅ መኖርን መማር አለብን ብለዋል።

ክርስቲያናዊ ግዴታ.

ከክርስቲያናዊ ዕይታ አንጻር ተፈጥሮን እና አካባቢን አንድ ላይ ካልተመለከቱ አስፈላጊ የሆኑ ትእዛዛትን በቁም ነገር መመልከት እንደማይቻል ብጹዕ አቡነ አርኖልድ ተናግረው፥ ባልንጀራችን በእውነት የምንወድ ከሆነ ዓለምን መንከባከብ አለብን ብለዋል። በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት ብዙ ሰዎች እየተሰቃዩ መሆናቸውን ገልጸው፥ ለጥቅም ሲባል ሌሎች አገራት መዘረፋቸውን በመግለጽ ይህ ሁኔታ መለወጥ እንደሚገባ አሳስበዋል።

በዚህ አስተያየት የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያንም ለአካባቢ ጥበቃ እና ለትምህርት ዘርፍ የበለጠ መሥራት እንደምትችል ገልጸው፥ ወደ ፊት በመጓዝ ለዲሞክራሲያዊት አገራቸው ድምፅ መሆንን በማረጋገጥ እንደ አገር ፖሊሲያቸውን እና ሕይወታቸውን መለወጥ እንደሚገባ ብጹዕ አቡነ አርኖልድ በቃለ ምልልሳቸው ላይ ተናግረዋል።

 

 

 

 

04 October 2023, 15:18