ፈልግ

በደቡባዊ ኢጣሊያን ከምትገኘው ከላምፔዱዛ ደሴት ወደ ሌላ ቦታ ለመሸጋገር የሚጠባበቁ ስደተኞች በደቡባዊ ኢጣሊያን ከምትገኘው ከላምፔዱዛ ደሴት ወደ ሌላ ቦታ ለመሸጋገር የሚጠባበቁ ስደተኞች  (ANSA)

የኢጣሊያኑ ካሪታስ የዓለም የስደተኞች ቀን ሲከበር ተጨማሪ ህጋዊ መንገዶች እንዲከፈቱ ጠየቀ

ቤተክርስቲያን 109ኛውን የዓለም የስደተኞች እና የፍልሰተኞች ቀን ስታከብር የካሪታስ ኢጣሊያን ሃላፊ የሆኑት ኦሊቪዬሮ ፎርቲ ፡ የጉልበት ብዝበዛን በማስቆም ስደተኞች የተሻለ ህይወት እንዲጀምሩ ለመርዳት እንዲቻል ተጨማሪ የሰብአዊነት መተላለፊያዎችን መክፈት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

የዓለም የስደተኞች እና የፍልሰተኞች ቀንን አስመልክቶ በካሪታስ ኢጣሊያን የፍልሰት ፖሊሲዎች እና ዓለም አቀፍ ጥበቃ ኃላፊ የሆኑት ኦሊቪዬሮ ፎርቲ ወደ አውሮፓ የሚጎርፉትን ስደተኞች ሰብዓዊ በሆነ መንገድ ለማስተናገድ የሚቻልባቸውን ስለተለያዩ አማራጮች እና ተግዳሮቶች ከቫቲካን ዜና ጋር ቆይታ አድርገዋል።
በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ስደተኞች በደቡብ ኢጣሊያ የባህር ዳርቻዎች ሲደርሱ ካሪታስ ኢጣሊያ ስደተኞችን እና ፍልሰተኞችን በማስተናገድ እና ተቀብሎ በማቆየት ላይ ብቻ ሳይሆን በአውሮፓ ተቋማትም ተቀባይነት እንዲያገኙ ድጋፍ እያደረገ እንደሆነ ሃላፊው ገልፀዋል። “ለዚህ ትልቅ የስደት ፈተና መፍትሄው ይሄ ነው ብሎ ወጥ የሆነ ነገር መናገር በጣም ከባድ ነው። ነገር ግን የመፍትሄው የመጀመሪያው እርምጃ ብዙ ህጋዊ መንገዶችን መክፈት ነው ልንል እንችላለን” ያሉት አቶ ፎርቲ ፥ የኢኮኖሚ ስደተኞች እና ፍልሰተኞቹ ደህንነታቸው ወደ ተጠበቁ አገሮች እንዲደርሱ እድል የመስጠቱን አስፈላጊነት አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።

የአውሮፓ አገሮች መተባበር አለባቸው

‘በስደት መስመር ላይ ያሉ ሀገራት ይህንን ችግር ለመፍታት አስተዋፅዖ ማድረግ ይችላሉ ፥ ነገር ግን ይህን ማድረግ የሚችሉት በጋራ ከሰሩ ብቻ ነው’ ሲሉ አቶ ፎርቲ ያስረዳሉ። በማከልም “እድሎች አሉን ፥ ለእነዚህ ሁሉ ሰዎች ዕድል ለመስጠት የሚያስችል ሀብቶች አለን። ችግሩ የአውሮፓ አገሮች መተባበር አለመፈለጋቸው ነው። አውሮፓ በስደት ጉዳዮች ላይ ያላት አቋም ግልጽ አይደለም” ብለዋል።

የጉልበት ብዝበዛን መዋጋት

ከስደት ጋር ተያይዘው ከሚመጡት ዋነኛ ችግሮች አንዱ ስደተኞች በአሰሪዎች የሚበዘበዙበት ጉዳይ ነው። ብዙውን ጊዜ ስደተኞች በግብርናው ዘርፍ ወይም በሌሎች የብሔራዊ ኢኮኖሚ ዘርፎች ተሰማርተው የጉልበት ብዝበዛ ይደርስባቸዋል። አቶ ፎርቲ ስለዚህ ጉዳይ ሲያብራሩ “በጣሊያን ውስጥ ያለው የጉልበት ብዝበዛን ጨምሮ በተለያዩ በርካታ የአውሮፓ ሃገሮች ውስጥ ያለው የጉልበት ብዝበዛ በእውነቱ ትልቅ ችግር ነው” ብለዋል።
ስደተኞች በመጀመሪያ ደረጃ ወደ አውሮፓ የሚሰዳዱት በአገራቸው ውስጥ የመሥራት ዕድል ባለማግኘታቸው ስለሆነ በአውሮፓ ያለውን የሥራ ገበያ ውስጥም ቢሆን ጥሩ እድሎችን ለማቅረብ ውጤታማ መንገዶችን ማመቻቸት እንደሚያስፈልግ አስምረውበታል። አቶ ፎርቲ “አንዳንድ ጊዜ ስደተኞቹ ሁለት ጊዜ ሲበዘበዙ ማየት በጣም የሚያስደንቅ ነው ፥ በመጀመሪያ በትውልድ አገራቸው ፥ ከዛም አንዳንድ ጊዜ በመተላለፊያ ሀገራት ፥ በመጨረሻም በመዳረሻ ሀገራት ውስጥ ብዝበዛ ይደርስባቸዋል” በማለት አብራርተዋል።
ካሪታስ ኢጣሊያን በጣሊያን ውስጥ የሚገኙትን የስደተኞችን የኑሮ ሁኔታ ለማሻሻል ታልሞ በ 2008 ዓ.ም. የተመሰረተውን ‘ፕሬሲዲዮ’ የተባለውን ፕሮጀክት አሁንም በተጠናከረ ሁኔታ ቀጥሎበታል።
የጣሊያኑ ካሪታስ ከሌሎች ድርጅቶች ጋር በመተባበር በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ለሚኖሩ በሺዎች ለሚቆጠሩ ስደተኞች የህግ፣ የህክምና እና ማህበራዊ ድጋፍ ይሰጣል። ለዚህ ፕሮጀክት ምስጋና ይግባውና ሥራ ማግኘት እና እንደ ሰራተኛ መብታቸውን ማስጠበቅ ችለዋል።

የ2023ቱ የዓለም የስደተኞች እና የፍልሰተኞች ቀን

109ኛው የዓለም የስደተኞች እና የፍልሰተኞች ቀን እሁድ መስከረም 13 ቀን 2016 ዓ.ም. ተከብሮ ዉሏል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስስ የዘንድሮውን የዓለም የስደተኞች ቀን በማስመልከት ባስተላለፉት መልእክት “ለመሰደድ ወይም ለመቆየት የመምረጥ ነፃነት” በሚል መሪ ቃል ሁሉም አገሮችና ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ማንም ሰው ያለመሰደድ መብቱ እንዲከበር እና በገዛ አገሩ በሰላም እና በክብር እንዲኖር የጋራ ጥረት እንዲደረግ አሳስበዋል። ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ለእያንዳንዱ ስደተኛ ክብር ከፍተኛ አክብሮት እንዲያሳዩ እና ደህንነቱ የተጠበቀ እና መደበኛ ወይም ህጋዊ የፍልሰት መንገዶችን እንዲያሰፋ ጥሪ አቅርበዋል። ብጹእነታቸው ሁሉም ሰው በጋራ ተጠቃሚነት ላይ እኩል ድርሻ እንዲኖረው ፣ መሰረታዊ መብቶቹ እንዲከበሩ እና ከአጠቃላይ ልማቱ ተጠቃሚ እንዲሆን ሁሉም ሰው ጥረት እንዲያደርግ አሳስበዋል።
 

25 September 2023, 12:58