ፈልግ

የቅዱስ ቪንሴንት ደ ፖል የቸርነት ሥራ እህቶች የቅዱስ ቪንሴንት ደ ፖል የቸርነት ሥራ እህቶች  

የፍቅር ሥራ ማኅበር እህቶች በሰለሞን ደሴቶች የተቸገሩትን በማገልገል ላይ እንደሚገኙ ተገለጸ

የቅዱስ ቪንሴንት ደ ፖል የፍቅር ሥራ እህቶች ማኅበር በሰለሞን ደሴቶች በሚፈጽሙት ተልዕኮ ድሆችን እና በማኅበረሰቡ የተገለሉትን በማገልገል ላይ እንደሚገኙ እና የአካባቢው ወጣት ሴቶች ለተጋበዙት የምንኩስና ሕይወት ምላሽ እየሰጡ መሆናቸው ታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ከክሮኤሺያ የመጡት የቅዱስ ቪንሴንት ደ ፖል የፍቅር ሥራ ማኅበር እህቶች ላለፉት 12 ዓመታት በሰሎሞን ደሴቶች የሚሲዮናዊነት አገልግሎት ሲያበረክቱ ቆይተዋል። በማላይታ ደሴት በሚገኝ ቡማ ሀገረ ስብከት ውስጥ የሚኖሩ የፍቅር ሥራ ማኅበር እህቶች መብራት በሌለበት እና ከዋና ከተማው ጋር በአደገኛ መንገድ በተገናኘ አካባቢ የሚኖሩ ናቸው። የአካባቢው ነዋሪዎች የዘንባባ ፍሬ በመሸጥ እና ዓሣ በማጥመድ ኑሯቸውን የሚመሩ ሲሆን፣ የቅዱስ ቪንሴንት ማኅበር እህቶችም የሕክምና መድኃኒቶችን በማቅረብ፣ ትምህርት ቤት በመክፈት እና የክርስትና እምነትን በማስተማር ይረዷቸዋል።

ዓመታት እየተቆጠሩ በሄዱ ቁጥር የሚስዮናዊነት ሥራቸው ፍሬ ማፍራቱ ይበልጥ ግልጽ እየሆነ መጥቷል። በሰለሞን ደሴቶች ውስጥ የምትገኝ ቤተ ክርስቲያን በተለይ በወጣቶች ዘንድ እያደገች መሆኗ ይታያል። የፍቅር ሥራ ማኅበር እህቶችም ቁጥራቸው በየጊዜው እያደገ የመጣውን የቅዱስ ቪንሴንት የማርያም ወጣቶች ማኅበር መሥርተዋል። የፍቅር ሥራ እህቶቹ ይህን ሲያስረዱ፥ የአካባቢው ወጣቶች ስለ እምነታቸው የበለጠ ለማወቅ እና በቤተ ክርስቲያናቸው ውስጥ ንቁ ተሳትፎ ለማድረግ ጉጉት እንዳላቸው ገልጸዋል።

የቅዱስ ቪንሴንት የፍቅር ሥራ ማኅበር እህቶች ሴቶችን በተለይም ባል የሌላቸው እናቶችን ለመርዳት በሉዊስ ደ ማሪላክ ማዕከል የልብስ ስፌት፣ ማንበብና መጻፍን እያስተማሩ ይገኛል። ለሴቶች እና ሕጻናት ልዩ ትኩረት በመስጠት ኢኮኖሚያዊ ችግር ያለባቸው ሰዎች እንዴት እራሳቸውን መቻል እንደሚችሉ ማስተማርም ይፈልጋሉ። የፍቅር ሥራ ማኅበር እህቶች ከራሳቸው ድጋፍ በመስጠት፥ ያለውን ችግር ለማስወገድ ቅድሚያ ከሚሰጡባቸው ጉዳዮች መካከል ትምህርት አንዱ ነው። ወላጆቻቸው የትምህርት ቤት ክፍያን መክፈል ባለመቻላቸው ብዙ ልጆች ትምህርታቸውን መከታተል ይሳናቸዋል።

እህት ቬሮኒካ ከቅዱስ ቪንሴንት የማርያም ወጣቶች ማኅበር አባላት ጋር
እህት ቬሮኒካ ከቅዱስ ቪንሴንት የማርያም ወጣቶች ማኅበር አባላት ጋር

ከመላው ዓለም የመጡ በጎ ፈቃደኞች እና ለጋሾች

እህት ቬሮኒካ ኢባሪች በሰለሞን ደሴቶች ከሚገኙት ክሮኤሽያውያን ሚስዮናዊ እህቶች መካከል አንዷ ናቸው። እህት ቬሮኒካ ከቫቲካን የዜና አገልግሎት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፥ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ለጋስ ሰዎች ተልዕኳቸውን ሳያቋርጡ እንዲቀጥሉ ለማድረግ እንዴት እንደሚረዱ ገልጸዋል። ከአውስትራሊያ የመጡ ክሮኤሽያዊ በጎ ፈቃደኞች፥ የፍቅር ሥራ እህቶች አገልግሎታቸውን የሚያቀርቡበት እና ትምህርታዊ ፕሮግራሞችን የሚያካሂዱባቸውን ቤቶች ሠርተው አበርክተዋል። ለጋሾቹ ለትምህርት ቤት ክፍያ እና ለተቸገሩ ሰዎች የመድኃኒት እና የአልባሳት አስተዋፅኦ ያደርጋሉ። በአካባቢው የወባ በሽታ በተደጋጋሚ እንደሚከሰት የገለጹት እህት ቬሮኒካ፥ ቢያንስ ሕጻናትን እና እርጉዝ ሴቶችን ለመርዳት ቢሞክሩም ነገር ግን በሽታውን ለመከላከል በክሊኒካቸው የወባ መከላከያ መድኃኒት እንደሌለ ይናገራሉ።

የቸርነት ሥራ ማኅበር እህቶች በሰለሞን ደሴቶች ውስጥ
የቸርነት ሥራ ማኅበር እህቶች በሰለሞን ደሴቶች ውስጥ

ቤተ ክርስቲያን በሰለሞን ደሴቶች ውስጥ በማደግ ላይ ትገኛለች

በዓለም ካርታ ላይ እምብዛም በማይታዩ አንዳንዶች የሰለሞን ደሴቶች ውስጥ የክርስትና እምነት ዛሬ እየተስፋፋ ይገኛል። በሰለሞን ደሴቶች ውስጥ ከቡማ ማኅበረሰብ የተገኙ ሁለት እህቶች የመጨረሻ መሃላቸውን ሲፈጽሙ፥ አንድ ጀማሪ እና ሁለት እጩዎች ያሉ ሲሆን፥ የፍቅር ሥራ ማኅበር እህቶችን ከደሴቶቹ ለማፍራት በተደረገው ጥረት በርካታ የአካባቢው ወጣት ሴቶች የክሮኤሺያ እህቶችን በመቀላቀል ላይ ይገኛሉ።

“እግዚአብሔርን ወደ ሕዝባቸው ማቅረብ እንፈልጋለን” ያሉት እህት ቬሮኒካ፥ ወደ ድሆች ዘንድ በመቅረብ ከከተማ ይልቅ አስተማማኝ በሆነ ገጠራማው አካባቢዎች የቅርብ ተስፋ ሆነው እንደሚኖሩ በማስረዳት፥ ብዙ ጊዜ ለሕዝቡ የሚፈያስፈልገውን ነገር ማቅረብ ባይችሉም ወደ እህቶች በመምጣት እገዛ መጠየቅ እንድሚችሉ እና ቢያንስ በማኅበሩ ተስፋ በማድረግ እነዚያ የፍቅር ሥራ ማኅበር እህቶችን የሚቀላቀሉ ወጣት ልጃገረዶች ችግሮችን እንደሚገነዘቡት አምናለሁ ብለዋል።

የቅዱስ ቪንሴንት ደ ፖል ዓመታዊ ክብረ በዓል

ቤተ ክርስቲያን የቅዱስ ቪንሴንት ደ ፖል ዓመታዊ ክብረ በዓል በየዓመቱ መስከረም 16 የምታከብር ቢሆንም፥ በሰሎሞን ደሴቶች ውስጥ የሚገኙ የቅዱስ ቪንሴንት የማርያም ወጣቶች ማኅበር አባላት ከቅዱስ ቪንሴንት ደ ፖል ማኅበር አባላት ጋር በመሆን መስከረም ወር በሙሉ የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት በማቅረብ ጸበል ጸዲቅ እንደሚቀምሱ እህት ቬሮኒካ አብራርተው፥ መስዋዕተ ቅዳሴውን ለሚካፈል እያንዳንዱ ሰው ዳቦን እንደሚያካፍሉ፥ ይህን በማድረግ ሕይወታቸውን በመካፈል የአንድ ትልቅ ቤተሰብ አባል መሆናቸውን የሚያሳዩበት ምሳሌያዊ መንገድ መሆኑን በመናገር፣ ይህም ቅዱስ ቪንሴንት ዲ ፖል ያስተማራቸው እና ለሁሉም ሰው የሚሆን ቦታ እንዳለ የሚገልጹበት መንገድ እንደሆነ አስረድተዋል።

የቸርነት ሥራ ማኅበር እህቶች በሰለሞን ደሴቶች ውስጥ
የቸርነት ሥራ ማኅበር እህቶች በሰለሞን ደሴቶች ውስጥ

የሕይወትን የሚቀይር ተሞክሮ

እህት ቬሮኒካ በሰለሞን ደሴቶች ተልዕኮአቸው ወቅት ሕይወታቸው እንደተለወጠ እና ለደስታ ያላቸው እሳቤም እንደተለወጠ ተናግረው፥ የደሴቶቹ ነዋሪዎችም ባላቸው ነገር እና በሕይወታቸው አመስጋኞች በመሆናቸው የሰለሞን ደሴቶች ደስተኞች እንደሚባሉ ተናግረዋል። እህት ቬሮኒካ አክለውም ነዋሪዎቹ ይህ ትልቅ ስጦታ መሆኑን እንደሚያቁ ተናግረው፥ ለነገ ሳይጨነቁ ለዛሬ ባላቸው ነገር እግዚአብሔርን እያመሰገኑ እንደሚኖሩ ገልጸው፥ የፍቅር ሥራ ማኅበር እህቶችም ያላቸውን በኅብረት ከሌሎች ጋር በመካፈል እውነተኛ ደስታን እንደሚያገኙ አስረድተዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ግንቦት ወር 2023 ዓ. ም. በተካሄደው የሚስዮናዊ ተቋማት ጉባኤ ላይ ባደረጉት ንግግር፥ የተልዕኮ ሥራ ለክርስትና እምነት አስፈላጊ እንደሆነ ተናግረው፥ ተልዕኮ ለክርስቲያናዊ ሕይወት እስትንፋስ እንደሆነ፥ ያለ ተልዕኮ ክርስቲያናዊ ሕይወት እንደሚታመም እና እንደሚጠወልግ በማስረዳት፥ ሚስዮናውያን አገልግሎታቸውን እያበረክቱ በድፍረት ወደ ፊት እንዲራመዱ አደራ ብለዋል።

 

21 September 2023, 17:08