ፈልግ

የሲኖዶስ ጉባኤን የሚካፈሉ የዓለም አቀፍ የገዳማውያት የበላይ አለቆች ኅብረት ተወካዮች  የሲኖዶስ ጉባኤን የሚካፈሉ የዓለም አቀፍ የገዳማውያት የበላይ አለቆች ኅብረት ተወካዮች  

ገዳማውያት እህቶች በሲኖዶስ ጉባኤ እንዲሳተፉ በመጋበዛቸው የተሰማቸውን ደስታ ገለጹ

የዓለም አቀፍ የገዳማውያት የበላይ አለቆች ኅብረት ፕሬዝደንት እህት ሜሪ ባሮን፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ገዳማውያት የቤተ ክርስቲያን የጋራ ጉዞ በሆነው የአንድነት፣ የተሳትፎ እና የተልዕኮ ሲኖዶሳዊ ጉባኤ ላይ እንዲሳተፉ ባቀረቡት ግብዣ ገዳማውያቱ የደስታ ምላሽ መስጠታቸውን ገለጹ።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ 16ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ በሮም ከመስከረም 23 እስከ ጥቅምት 18/ 2016 ዓ. ም. ድረስ የሚካሄድ ሲሆን፥ በጉባኤው ላይ ዓለም አቀፍ የገዳማውያት የበላይ አለቆች ኅብረትን በመወከል አምስት ገዳማውያት እንደሚካፈሉ የኅብረቱ ፕሬዝደንት እህት ሜሪ ባሮን ተናግረው፥ ዕድሉን በማግኘታቸው የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል።

ለርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የቀረበ ምስጋና

የኅብረቱ ፕሬዝደንት እህት ሜሪ ባሮን ሐሙስ መስከረም 17/2016 ዓ. ም. እንደገለጹት፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ2014 ዓ. ም. ቤተሰብን አስመልክቶ በተካሄደው የሲኖዶስ ጉባኤ ላይ የዓለም አቀፍ የገዳማውያት የበላይ አለቆች ኅብረት በመጋበዛቸው አድናቆታቸውን ገልጸዋል። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የኅብረቱ አባላት በእያንዳንዱ ቀጣይ ሲኖዶስ እንደ አድማጭ መሳተፋቸውን እህት ሜሪ ተናግረው፥ በዚህ ዓመት በሚካሄደው 16ኛ  መደበኛ ጠቅላላ የሲኖዶስ ጉባኤ ላይ እንዲገኝ ኅብረቱ በመጋበዙ ምስጋናቸውን አቅርበዋል። የኅብረቱ ተወካይ እህቶች ለመጀመሪያ ጊዜ በሲኖዶስ ሂደት ውስጥ በሙሉ አባልነት እንደሚሳተፉ፥ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር በሚደረጉ ውይይቶችም በመሳተፍ በጉባኤው ሠነድ ውስጥ ለሚካተቱ አስተያየቶች ድምጻቸውን እንደሚሰጡ ተናግረዋል። እህት ሜሪ ባሮን አክለውም፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ገዳማውያት በ16ኛው መደበኛ ጠቅላላ የሲኖዶስ ጉባኤ ላይ እንዲሳተፉ ያቀረቡትን ጥሪ ተቀብለው፥ የቤተ ክርስቲያን የጋራ በሆነው የአንድነት፣ የተሳትፎ እና የተልዕኮ ጉዞ ላይ እንዲሳተፉ ላቀረቡት ጥሪ የደስታ ምላሽ እንደሚሰጡ አጽንኦት ሰጥተዋል።

አምስቱ የጉባኤው ተሳታፊዎች

በሮም በሚካሄደው 16ኛው የሲኖዶስ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ አምስት የዓለም አቀፍ የገዳማውያት የበላይ አለቆች ኅብረት ተወካዮች እንዲሳተፉ ጥሪ ቀርቧል። ከመስከረም 23 እስከ ጥቅምት 18/ 2016 ዓ. ም. ድረስ በሚካሄደው የሲኖዶስ ጉባኤ ኅብረቱን ወክለው የሚሳተፉት፥ የኅብረቱ ፕሬዝዳንት እህት መሪ ባሮን፣ የኅብረቱ ዋና ጸሐፊ እህት ፓትሪሲያ ማሪ፣ የኅብረቱ ሥራ አስፈፃሚዎች እህት ኤልሳቤጥ ሜሪ ዴቪስ፣ እህት ኤሊሴ ኢዜሪማና፣ እና እህት ማርያ ኒርማሊኒ መሆናቸው ታውቋል።

የኅብረቱ ፕሬዝደንት እህት መሪ ባሮን፣ ኅብረታቸው በሲኖዶስ ጉባኤ ውስጥ ያለው ተሳትፎ ትንቢታዊ ድምጽ እንደሚሆን ያላቸውን ተስፋ ገልጸው፥ ኅብረታቸው ዛሬ በዓለም ውስጥ እየተከሰቱ ስላሉ በርካታ ነገሮች የዓይን ምስክር እንደሆነ ተናግረዋል። ጉባኤውን እንዲካፈሉ በመመረጣቸው ምክንያት የተሰማቸውን ደስታ የገለጹት እህት ማርያ ኒርማሊኒ ያስደነገጣቸው፥ “ከሁሉም ሕዝቦቹ ጋር በሚያደርጉት ጉዞ እንዲሳተፉ የቀረበልኝ ግብዣ እንደሆነ ተናግረዋል።

ገዳማውያቱ የሚያበረክቱት ልዩ አስተዋፅኦ

የዓለም አቀፍ የገዳማውያት የበላይ አለቆች ኅብረት ፕሬዝደንት እህት ሜሪ ባሮን፥ የገዳማውያት ሕይወት ከማኅበረሰብ የሕይወት ልምድ ጋር ቤተ ክርስቲያን ሲኖዶሳዊ ለውጥ ለማካሄድ እንደሚረዳ ያላቸውን እምነት ተናግረዋል። እህት ሜሪ ባሮን በገለጻቸው፥ “የምንኩስና ሕይወታቸው በሲኖዶሳዊት ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የተለያዩ የወንዶች እና የሴቶች ማኅበራት በደስታ የሚተባበሩበትን፣ እርስ በርስ በመደማመጥ፣ የእግዚአብሔርን ፈቃድ በመሻት፣ በሦስተኛው ሺህ ዓመት እግዚአብሔር የሚጠብቃትን ቤተ ክርስቲያን በአንድነት ለመገንባት እንደቆመ አስቀድሞ ማሳየቱን ገልጸዋል።

"እኛም የዘመናችን የምንኩስና ሕይወት ተከታዮች እንደ መሆናችን መጠን፥ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ከሚገኙ ሌሎች ሰዎች የምንማረው ብዙ ነገር አለን” ያሉት እህት ሜሪ ባሮን፥ በምንኩስና ሕይወታቸው ውስጥ ሲኖዶሳዊነትን በማሳደግ የመለወጥን፣ የመሻሻል እና የማዳበርን መንገድ እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል። እህት ሜሪ ባሮን በማከልም፥ የሲኖዶሱ አካል እንዲሆኑ በቀረበላቸው ግብዣ መሠረት፥ ልምዶቻቸውን ለማካፈል እና በኅብረት እንዲያልሙ እና ሲኖዶሳዊት ቤተ ክርስቲያን እውን ትሆን ዘንድ በመጋበዛቸው፥ ጉባኤውን የሚሳተፉት በልበ ሙሉነት፣ በትህትና እና ኃላፊነት በተሞላበት ሁኔታ እንደሆነ አስረድተዋል።

የዓለም አቀፍ የገዳማውያት የበላይ አለቆች ኅብረት ፕሬዝደንት እህት ሜሪ ባሮን ንግግራቸውን ሲያጠቃልሉ፥ “የደረሳቸውን የሲኖዶሳዊ ሂደት ምላሾች መሠረት በማድረግ፣ በሂደቱ ወቅት ከገዳማውያን አቻቸው ጋር በመተባበር የበኩላቸውን አስተዋፅዖ ማበርከታቸውን ገልጸው፥ በዚህ የብዙ ሰዎችን ሕይወት የሚነካ አስፈላጊ የቤተ ክርስቲያን ሕይወት ገጽታን መወከል እንደሚችሉ ገልጸዋል።

ዓለም አቀፍ የገዳማውያት የበላይ አለቆች ኅብረት አጭር ታሪክ

ዓለም አቀፉ የገዳማውያት የበላይ አለቆች ኅብረት እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ1965 ዓ. ም. በሁለተኛው የቫቲካን ጉባኤ አነሳሽነት በሕገ ቀኖና የተመሠረተ ሲሆን፥ ተልዕኮው በገዳማውያት ሐዋርያዊ ሕይወት መካከል የቅርብ ትብብርን ለመፍጠር ያለመ ነው። በአሁኑ ወቅት ጊዜ ዓለም አቀፉ የበላይ አለቆች ኅብረት በ1903 የበላይ አለቆች የተዋቀረ እና በዓለማችን ውስጥ በ 36 ክልሎች ውስጥ የሚገኝ ኅብረት ነው።

ከ600,000 የሚበልጡ አባላትን ያቀፉት 2,000 የገዳማውያት ማኅበራት ልምዳቸውን እና እውቀታቸውን የሚለዋወጡበት፣ እርስ በርስ በመመካከር እና በመደጋገፍ ማኅበሮቻቸውን እየመሩ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ እና በአጠቃላይ በኅብረተሰቡ ውስጥ አገልግሎታቸውን እንደሚመሩ ታውቋል።

ከዓለም አቀፍ አባልነት ጋር ኅብረቱ ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች የመጡ ገዳማውያት እርስ በርሳቸው እንዲገናኙ እና በኅብረት ሆነው ዓለም አቀፋዊ ማኅበረሰብን ለመመሥረት እርስ በርስ የሚገናኙበትን ድልድይ ለመገንባት እና አውታረ መረቦችን ለማዳበር ዓላማ ያለው እንደሆነ ታውቋል።

 

30 September 2023, 17:07