ፈልግ

የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ በመጪው የጳጉሜ ቀናት የሁሉም ሃይማኖት ተከታዮች የጸሎት እና የንስሃ ጊዜ እንዲያሳልፉ ጥሪ አቀረበ። የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ በመጪው የጳጉሜ ቀናት የሁሉም ሃይማኖት ተከታዮች የጸሎት እና የንስሃ ጊዜ እንዲያሳልፉ ጥሪ አቀረበ። 

የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ በመጪው የጳጉሜ ቀናት የሁሉም ሃይማኖት ተከታዮች የጸሎት እና የንስሃ ጊዜ እንዲያሳልፉ ጥሪ አቀረበ።

የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ዛሬ ነሃሴ 30 ቀን 2015 ዓ.ም. በተቋሙ ዋና ጽ/ቤት ለመገናኛ ብዙሃን በሰጠው የጋራ መግለጫ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ የሁሉም ሃይማኖት ተቋማት ለምዕመናኖቻቸው ከነገ ጀምሮ በሚገባው የጳጉሜ ቀናት ብሄራዊ የጸሎት እና የንስሃ መርሃ ግብር እንዲዘጋጅ ጥሪውን አስተላልፏል።

አዘጋጅ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

የጋራ መግለጫው የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ የበላይ ጠባቂ አባቶች አዲሱን ዓመት በማስመልከት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት በማስተላለፍ የጀመረ ሲሆን ፥ በመቀጠልም በተቋሙ የተዘጋጀውን ከጳጉሜ 3 እስከ 5/2015 ዓ.ም. ድረስ የሚቆየውን ብሄራዊ የጸሎት እና የንስሃ መርሃ ግብር በኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ መዘጋጀቱን ይፋ አድርጓል። ይህ ብሄራዊ የጸሎት እና የንስሃ መርሃ ግብር ‘ጥላቻ የራቀበት ፣ የፍቅር ብሩህ ተስፋ የሚታይበት 2016 ዓ.ም.ን በንስሃ እና በይቅርታ እንቀበል’ የሚል መርህ እንደሚኖረው ተገልጿል። በዚህ መሰረት የምንዘጋጅበት የንስሃ እና የጸሎት መርሃ ግብር እንደ መነሻነት የዓለም ታሪክን ወደ ኋላ ስንዳስስ በሰው ልጆች ታሪክ ዉስጥ የእርስ በእርስ ግጭት ፣ ጦርነት እና ሁከት በዬትኛውም የዓለም ክፍል እንደሚከሰት አጽንኦት የሰጠው መግለጫው ፥ ዛሬም ያሉ እውነታቸው እንደሚያሳዩት ከግጭት ነጻ የሆነ ሃገርም ሆነ ህብረተሰብ እንደሌለ ታሪክም ምስክር ነው ተብሏል። ዓለማችን የብዙ ዘመናት የጦርነት ግጭት መድረክ እንደነበረች የብዙ ታሪክ ድርሳናት መዝግበው አኑረውልናል ብሏል።  ሌላኛው የዓለማችን ገጽታ ደግሞ የትውልድ እልቂት እና ክብር የሰው ልጅ ጥፋት ፣ የንብረት መውደም ፣ የህዝብ መፈናቀል ቂም በቀልን ማትረፍ እንጂ ጦርነት የችግር መፍትሄ አለመሆኑን ይገልፅልናል’ ተብሏል።

መግለጫው በመቀጠል ‘ሩቅ ሳንሄድ ከቅርብ ጎረቤቶቻችን እንደምንረዳው የጦርነት ትርፍ የሃገር መፍረስ ፣ የቅርሶች መውደም ፣ ስደት ፣ ረሃብ እና ሃገር አልባነት መሆኑ ይታወቃል’ ካለ በኋላ ከዚህ አንፃር እኛም ከሌሎች ተምረን በጥንቃቄ እና በጥበብ ችግሮቻችንን መያዝ ካልቻልን ከሌሎች የተለየን ህዝቦች እንዳልሆንን እንገነዘባል ፥ ስለዚህ ቆም ብሎ ማሰብ ፣ ያለፈውን ዘመን በይቅርታ ዘግቶ የወደፊቱን ማየት ፥ ዕርቅ እና ንስሃ የጊዜው አስፈላጊ ጥያቄ መሆናቸውን ለመጠቆም እንወዳለን’ ብሏል።

ያለፈውን የታሪካችንን ቁስል እና ስብራት ማከም የምንችለው ደግሞ የይቅርታ እና የምህረት ልብ ሲኖረን ብቻ እንድሆነ እና በየሁሉም የሃይማኖት ተቋማት ዉስጥ ንስሃ ትልቅ ቦታ ስላለው ፥ ንስሃ ያለ ጠባሳ ስለሚያክም ፣ ያለቅሬታ የሚፈውስ ጥበብ በመሆኑ ይህንን ጥሪ አድርገናል ብለዋል።

ስለዚህ በዚህ የጸሎት መርሃ ግብር ላይ ትልቁ ወደ አደባባይ እንድንወጣ ፣ ህዝባችንን እንድንጠይቅ ከሚያስገድዱን ጉዳዮች በሃገራችን ለዘመናት የተጠራቀመ ግፍ እና በደል እንዲሁም የቂም በቀል ስሜት ስላለ ዛሬ ለትውልድ የሚተላለፍ በደል እየተፈጸመ ስለሆነ ፥ ባለፉት ዘመናት የእምነት አባቶቻችንን ስላዋረድን ፣ ስለገደልን ፣ ለመከራ እና ለስደት ስለዳረግን ፣ የሃይማኖት ተቋማትን እና የማምለኪያ ስፍራዎቻችንን ስላፈራረስን እና ስላቃጠልን ፣ ምእመናንን ስላፈናቀልን ፣ በመከባበር ፋንታ ስለተናናቅን ፣ በመመራረቅ ፋንታ ስለተረጋገምን ፣ ፈጣሪን በአደባባይ ስለካድን ፣ ፍትህ ስላዛባን ፣ በአጠቃላይ በደለኞች ስለሆንን በፈጣሪ ፊት በንስሃ መውደቅ ያስፈልገናል” በማለት ስለመርሃ ግብሩ አስፈላጊነት በአጽንኦት ተገልጿል። ይህ የጸሎት መርሃ ግብር ሶስት አበይት ዓላማዎች እንዳሉት የተነገረ ሲሆን ፥ እነዚህም ንስሃ ፣ ይቅርታ እና ዕርቅ እንደሆኑ እና የጸሎቱም መርሃ ግብር የሚከናወነው እንደየ ቤተ እምነቱ አስተምርሆ እና ሥርዓት መሆኑም ተነግሯል።

በዚህም መሰረት ጳጉሜ 3 2015 ዓ.ም. ዓርብ ዕለት በመላው የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ስር ባሉ መስጊዶች አጠቃላይ የጸሎት (ዱአ) ሥነ ስርዓት እና በዚሁ ዙሪያ ትምህርት የሚሰጥ ይሆናል።

ጳጉሜ 4 2015 ዓ.ም. ቅዳሜ ዕለት በመላው የሰባተኛ ቀን አድቬንቲስት ቤተ ክርስቲያን ሁሉ እንደ ቤተ እምነቱ ሥነ ስርዓት የጸሎት እና የትምህርት መርሃ ግብር እንዲካሄድ ፡

ጳጉሜ 5 2015 ዓ.ም. እሁድ ዕለት በሁሉም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ፣ የኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ፣ የኢትዮጵያ ወንጌላዊያን አብያተ ክርስቲያናት ህብረት ፣ የኢትዮጵያ ወንጌላዊት መካነ ኢየሱስ ቤተ ክርስቲያን እንዲሁም የኢትዮጵያ ቃለ ህይወት ቤተ ክርቲያን እንደየ እምነቶቻቸው ሁሉም የሃይማኖቱ ተከታይ የንስሃ እና የይቅርታ እንዲሁም በዚህ ዙሪያ ትምህርት የሚሰጥበት መርሃ ግብር እንዲኖር የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ የበላይ ጠባቂ አባቶች እና የሥራ አስፈፃሚ ቦርድ አባላት ይህ መመሪያ እንዲሰጥ ወስኗል።

ዕለተ እሁድ ፥ ጳጉሜ 5 2015 ዓ.ም. ከሰዓት በኋላ 7 ሰዓት ላይ በወዳጅነት ፓርክ የተለያዩ የመንግስት ባለስልጣናት እና ከሰባቱ የሃይማኖት ተቋማት ውጪ የሆኑ ቤተ እምነቶች በሚሳተፉበት አጠቃላይ የመርሃ ግብሩ የማጠቃለያ የጸሎት እና የተለያዩ ሥነ ስርዓቶች እንደሚካሄዱም ተገልጿል።

 ተቋሙን የሚወክሉ ሁሉም የሃይማኖት አባቶች በተገኙበት መግለጫውን ያስተላለፈው የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ፥ ሃገራችን እየገጠሟት ያሉትን የተለያዩ ተግዳሮቶችን በድል አሸንፈን እንድንወጣ ሁሉም በየሃይማኖቱ አምላክ የምህረት እጁን እንዲዘረጋልን ወደ ፈጣሪው እንዲማጸን ጥሪ አስተላልፈዋል።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሃፊ የሆኑት ብጹዕ ዶክተር አቡነ ጴጥሮስ “ጌታ አምላካችን ሆይ ምህረት ካንተ ዘንድ ካልሆነ በስተቀር ከዬትም ስለማይገኝ ምህረትህን አውርድልን” ብለው የመክፈቻ ንግግር እና ጸሎት ያደረጉ ሲሆን ፥ በመጪው የጳጉሜ ቀናት እያንዳንዱ የሃይማኖቱ ተከታይ ባለበት ሆኖ በተደረገው ጥሪ መሰረት የጸሎት እና የንስሃ ጊዜ እንዲያደርግ አደራ ብለዋል። ብጹዕ አቡነ ጴጥሮስ በማከልም “ለሚቀጥሉት ስድስት ቀናት ልባችንን ልናፈስ በየቤተ እምነታችን ካንተ ጋር ልንገናኝ ፣ ይቅርታ ልንጠይቅ ተዘጋጅተናልና ጸሎታችንን ፣ እንባችንን ፣ ምህላችንን እንድትቀበለን ፍቃድህ ይሁንልን” ካሉ በኋላ ለሁሉም አማኞች ባስተላለፉት መልዕክት ፥ “በዚህ ሰዓት የምናስተላልፈው መልዕክት ሁሉ በእያንዳንዱ ቤተ እምነት አማኝ ልብ ዉስጥ ተቀምጦ ለንስሃ የሚዘጋጅ እንድታደርግልን ፍቃድህ ይሁን” ብለው ጸሎታቸውን አድርሰዋል።

የኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተክርስቲያንን እና ብጹእ ካርዲናል አቡነ ብርሃነኢየሱስ ሊቀ ጳጳሳት ዘካቶሊካዊያንን በመወከል በዝግጅቱ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት በኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ጠቅላይ ጽ/ቤት የትምህርት ክፍል ሃላፊ የሆኑት ክቡር አባ ዳኒኤል ሃሶ እንደተናገሩት ‘ሠላም እንኳን ለሰው ልጅ ይቅርና ለእንስሣትም ጭምር ምን ያክል አስፈላጊ እንደሆነ’ በመግለፅ ፥ የሰው ልጅ ገና ከጅምሩ የእግዚያብሄርን ትዕዛዝ በመተላለፉ ከእግዚያብሄር ጋር የነበረው ጥሩ ግንኙነት እና ሠላም እንዲሁም ከራሱ ጋር እና ከሌሎች ጋር የነበረው ሰላም እንደጠፋው ካብራሩ በኋላ ይህንንም ሠላሙን ለመመለስ ያስችለው ዘንድ ወደ አምላክ መጸለይ እና ንስሃ መግባት ግዴታ ስለሆነ በሃገር ውስጥም ሆነ ከሃገር ዉጪ ያሉ ሁሉም የካቶሊክ እምነት ተከታይ በተደረገው ጥሪ መሰረት ጳጉሜ 5/2015 ዓ.ም. ለሃገራች ሠላም በተሰበረ ልብ ከመደበኛው የቤተክርስቲያኒቷ የጸሎት እና የቅዳሴ መርሃ ግብር በተጨማሪ በመቁጠሪያ ጸሎት እና የንስሃ ጊዜ እንዲያሳልፍ እንዲሁም ከሰዓት በኋላ በወዳጅነት ፓርክ ከሁሉም የሃይማኖት ተቋማት ጋር በሚደረገው የጸሎት ሥነ ስርዓት ላይ እንዲካፈል ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።  

ሙስሊሙን ማህበረሰብ ወክለው ሼህ ሃጂ ኢብራሂም ቱፋ ንግግር ያደረጉ ሲሆን ፥ ሼሁ ለሙስሊሙ ህብረተሰብ ባስተላለፉት መልዕክት ጳጉሜ 3 2015 ዓ.ም. ዕለተ ዓርብ ላይ ሁሉም ሙስሊም ህብረተሰብ የጁምአ ጸሎት ላይ ተገኝቶ ይህን ልዩ የጸሎት እና የንስሃ ጊዜ እንዲያሳልፍ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።   

06 September 2023, 13:56