ፈልግ

ብጹዕ ካርዲናል ብርሃነየሱስ ሊቀጳጳሳት ዘካቶሊካውያን፣ የኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ጳጳሳት ጉባኤ ፕረዚዳንት እና የኢትዮጵያ ካቶሊክ ዩኒቨርሲቲ ቻንስለር  (ፋይል) ብጹዕ ካርዲናል ብርሃነየሱስ ሊቀጳጳሳት ዘካቶሊካውያን፣ የኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ጳጳሳት ጉባኤ ፕረዚዳንት እና የኢትዮጵያ ካቶሊክ ዩኒቨርሲቲ ቻንስለር (ፋይል) 

ብጹዕ ካርዲናል አቡነ ብርሃነኢየሱስ ሊቀ ጳጳሳት ዘካቶሊካዊያን በጳጉሜ ቀናት ጾም ጸሎት እንዲደረግ ጥሪ አቀረቡ

የኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ጳጳሳት ጉባኤ ፕረዚዳንት እና የኢትዮጵያ ካቶሊክ ዩኒቨርሲቲ ቻንስለር የሆኑት ብጹዕ ካርዲናል ብርሃነኢየሱስ ሀገራችን ኢትዮጵያን እያጋጠሟት ያሉትን ተግዳሮቶች በድል እንድትወጣ እያንዳንዱ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ምዕመን እያገባደድነው ባለው የ 2015 ዓ.ም. የመጨረሻዎቹ የጳጉሜ ቀናትን በጾም ፣ በጸሎት እና በንስሃ እንዲያሳልፍ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል ፥ እንደሚከተለው እናቀርባለን።

የእግዚአብሔር ሰላምና ጸጋ ከሁላችን ጋር ይሁን! 

የያዝነውን 2015 ዓ.ም. እያገባደድን በምንገኝበት በዚህ ወቅት የመጨረሻዎቹን ቀናት ያለፈውን ዓመት ወደኋላ የምንቃኝበት፣ ራሳችንን በንሥሓ የምንመለከትበት፣ ከእግዚአብሔር ጋር ያለንን ግንኙነት በጥልቀት የምንመረምርበት ሲሆን ለምንቀበለው ዓመት ደግሞ ካለፈው ድክመታችን፣ ስህተታችን፣ ጥፋቶቻችን ተምረን፣ ሕይወታችንን በአዲስ መልክ ከእግዚአብሔር ጋር በበለጠ በማቆራኘት ለመጀመር የምናቅድበት የጥሞና ጊዜ እንዲሆን ያስፈልጋል፡፡ 

የጳጉሜ ወርን በጸሎት እንደናሳልፍ በተለይም ስለአገራችን ሰላም አብዝተን እንድንጸልይ በዚህ አጋጣሚ ጥሪ ለማስተላለፍ እንወዳለን፡፡ የዚህ ጥሪ ዋነኛ ዓላማው አገራችን ከሁከት፣ ከመፈናቀል፣ ከመገዳደልና ከመገፋፋት አዙሪት ትወጣ ዘንድ ሁላችንም በጾምና በጸሎት ስድስቱን የጳጉሜ ቀናት ለእግዚአብሔር እንድንሰጥ በማሰብ ነው፡፡ 

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ዓለም የመጣው የሰውን ልጅ ሁሉ ለማዳን ነው፡፡ ራሱን አዋርዶ በበረት ተወልዶ፣ ሐዋርያው ጳውሎስ እንደሚል ራሱን ስለእኛ ሲል ርግማን አድርጎ የመስቀል ሞት እስከመሞት ራሱን የሰጠው ሃይማኖት፣ ዘር፣ ቀለም፣ ጾታ ሳይለይ መላውን የሰው ዘር ለማዳን ነው፡፡ በዚህ የማዳን ሥራ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሰውን ልጅ ከራሱና ከእግዚአብሔር ጋር አስታረቀ፡፡ ይህ የማስታረቅ አገልገሎቱ እርስበርሳችን በመታረቅና በመተሳሰር የሚቀጥል ነው፡፡ 

በተለይ ደግሞ አሁን አገራችን ከምትገኝበት ፈታኝ ሁኔታ አንጻር እያንዳንዱ ምእመን ሆነ ማንኛውም ዜጋ ራሱን መጠየቅ ያለበት “እኔ ለራሴ ሰላም እንዲኖረኝ ምን ማድረግ አለብኝ? ቤተሰቤ ሰላም እንዲሆን ምን ማድረግ አለብኝ? አካባቢዬ ሰላም እንዲሰፍን ምን ማድረግ አለብኝ? አገሬ የሰላም ምድር እንድትሆን ምን ማድረግ አለብኝ? እንዴት ማሰብ አለብኝ? እንዴት መመላለስ አለብኝ? ከባልንጀራዬ፣ ከጎረቤቴ፣ ከሥራ ባልደረባዬ፣ በተለያየ መስክ ከማገኛቸው፣ ሌላ ቋንቋ፣ ሌላ ሃይማኖት፣ ሌላ ባሕል፣ ሌላ ወግ ካላቸው ወገኖች ሁሉ ጋር ምን ዓይነት መስተጋብር ሊኖረኝ ይገባል? የምከታተላቸውና የማጋራቸው የመረጃ ምንጮች ምን ዓይነት መሆን አለባቸው? ከተፈጥሮ ጋር ምን ዓይነት ግንኙነት ሊኖረኝ ይገባል? ከፈጣሪዬ ጋር ያለኝ ግንኙነትስ ምን መምሰል አለበት?” እነዚህ እና በርካታ ራሳችንን የምንመረምርባቸውን፣ የምንፈትሽባቸውን ጥየቄዎች በማንሣት ወደ አዲሱ ዓመት በምናደርገው ጉዞ ማሰላሰል ይጠበቅብናል፡፡ 

አገራችን ባለችበት በዚህ አስቸጋሪ ወቅት በአንድ በኩል በዓለምአቀፍ ደረጃ የጦርነት ነጋሪት በሚጎሰምበት ሁኔታ ምክንያት ከፍተኛ ሰብአዊ ቀውስ ላይ እንገኛለን፡፡ በሌላ በኩል በተለያዩ የአገራችን ክፍሎች ያለው የግጭትና የመጠላለፍ ፣ ንጹሐን ዜጎች በግፍ በአሰቃቂ ሁኔታ እየተገደሉ፣ እየተፈናቀሉ፣ እየተገፉና ስብእናን በሚያጎድፍ መልኩ እንዲኖሩ በሚደረጉበት ሁኔታ የአንዲት ኢትዮጵያ ልጆች የሆኑ ወንድማማቾች/እኅትማማቾች የሚተላለቁበትና ቂም ቁርሾ ወደሚይዙበት ደረጃ እየሄደ ነው፡፡ 

ስለሆነም የንጉሥ ዳዊት ትንቢታዊ ዝማሬ “ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች።” (መዝ 68፥31) የሚለውን መሠረት አድርገን ወደ ፈጣሪአችን በተሰበረ ልብ ንሥሐ ገብተን ልንጮኽ የሚገባን ነገ ሳይሆን ዛሬ፣ ከዛሬም አሁን ነው። ይህንን የጳጉሜ ወር በፍጹም መጸጸት ለራሳችን እና ለወገኖቻችን ሁሉ ንሥሓ በመግባት የሁላችንም ልብ ለይቅርታ እንዲዘጋጅ በንሥሓ ውስጣችንን ልናጥብ ይገባል፡፡ እግዚአብሔር ይቅር እንዲለንም አጥብቅን ልንማልድ ይገባል፡፡ ንሥሐ የምንገባው ለራሳችን ብቻ 

ሳይሆን ለሕዝባችን፣ ጦር አንሥተው ሰላማዊ ሰዎችን ለሚያፈናቅሉትም ጭምር ነው፤ በየቦታው ግፍን ለሚፈጽሙትም ነው፤ በደላቸው በግልጽ ለሚታየውም ለማይታየውም ነው፡፡ 

እግዚአብሔር ዛሬ ለሁላችንም ጥያቄ ያቀርባል፡፡ ይህንንም በሐዋርያው ያዕቆብ ቃል ያሰማናል፣ “በእናንተ መካከል ያለው ጦርነትና ጠብ ከየት የመጣ ነው?” በማለት ራሳችንን እንድጠይቅ ይጋብዘናል። ወዲያውም ራሱ መልሱን ይነግረናል፣ “በሰውነታችሁ ውስጥ ከሚዋጋው ከሥጋዊ ምኞታችሁ አይደለምን? የምትፈልጉትን ነገር ማግኘት ሲያቅታችሁ ሰውን ትገድላላችሁ፤ በብርቱ ተመኝታችሁ ማግኘት ሲያቅታችሁ ትጣላላችሁ፤ ትጋደላላችሁ።” (ያዕ 4፡1-2) 

ይህንን ቃል ስናስብ ባልንጀራህን እንደራስህ ውደድ የሚለውን ትእዛዝ ወደ ጎን ማደረጋችን እንደሆነ እንረዳለን፡፡ በጦርነት አሸናፊ የሚሆን ወገን የለም፡፡ በጦርነት ማሸነፍ ልብን አያስገዛም፤ ይልቁንም ቂምና ቁርሾን ወልዶ ቀን ጠብቆ በድጋሚ ወደመቆራቆስ ነው የሚወስደው፡፡ የእግዚአብሔርም ቃል እንደሚያስተምረን፤ “ሰይፍ የሚያነሡ ሁሉ በሰይፍ ይጠፋሉና ሰይፍህን ወደ ስፍራው መልስ፡፡” (ማቴ 26፡52) 

የሰላም ንጉሥ ክርስቶስ ሰላም እንዲሰጠን ሁሉም ወገኖች የጦረ መሣርያዎቻቸውን በማምረቻ መሣርያ እንዲለውጡ ጥሪአችንን እናስተላልፋለን፡፡ ነቢዩ ኢሳይያስ በትንቢቱ እንደሚለው “ሰይፋቸውንም ማረሻ ጦራቸውንም ማጭድ ለማድረግ ይቀጠቅጣሉ ሕዝብም በሕዝብ ላይ ሰይፍ አያነሣም፥ ሰልፍም ከእንግዲህ ወዲህ አይማሩም።” (ኢሳ 2፡4) ይህንንም በማድረግ ሕዝባችን የሰላም አየር እንዲተነፍስ እንዲያደርጉ እንደቤተክርስቲያን ልንማልድ ይገባናል፡፡ በቀጥታ በጦር ሜዳ ባይሆኑም በያሉበት ጦርነትን የሚገፋፉትም ልቦናቸውን የሰላሙ ንጉሥ እንዲነካ እንማልዳልን፡፡ 

ስለሆነም በመጪዎቹ ቀናት ይህንን በማሰብ በየቁምስናው እና በየገዳማቱ በየዕለቱ የመቁጠርያ ጸሎት በማድረስ፣ የሕማም ምሥጢር ላይ በማስተንተን በተለይም የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ሥቃይ ከሕዝባችን ሥቃይ ጋር በማቆራኘት ከዐርብ ስቅለት ተሻግረን ወደ ትንሣኤ እሑድ መሻገር እንድንችል በማስተንተን፣ ለንሥሓ ጊዜ በመውሰድ እና የቅዱስ ቁርባን ቡራኬ በማድረግ እንድናሳልፍ ይሁን፡፡ 

እግዚአብህር ምድራችንን ይባርክ!!!

ብጹዕ ካርዲናል አቡነ ብርሃነኢየሱስ ሊቀ ጳጳሳት ዘካቶሊካዊያን፣

የኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ጳጳሳት ጉባኤ ፕረዚዳንትና

የኢትዮጵያ ካቶሊክ ዩኒቨርሲቲ ቻንስለር

 

 የእዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ 

 

 

 

07 September 2023, 09:26