ፈልግ

በሞዛምቢክ የቴቴ ሀገረ ስብከት ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ዲያማንቲኖ ጉአፖ አንቱነስ በሞዛምቢክ የቴቴ ሀገረ ስብከት ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ዲያማንቲኖ ጉአፖ አንቱነስ  

በሞዛምቢክ ሁለት የእግዚአብሔር አገልጋዮች የብጽዕና ቅድመ ዝግጅት በሂደት ላይ እንደሚገኝ ተገለጸ

ሞዛምቢክ ውስጥ በተካሄደው የእርስ በርስ ጦርነት ሕይወታቸውን ለሰላም ሲሉ የተሰው የሁለት ኢየሱሳዊ ካህናት የብጽዕና አዋጅ ቅድመ ዝግጅት በሂደት ላይ እንደሚገኝ ተገለጸ። እስካሁን በሀገረ ስብከት ደረጃ ሲካሄድ የቆየው ጥናቱ በቅርብ ጊዜ ሲጠናቀር ማኅደሩ ወደ ሮም እንደሚላክ ታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በሞዛምቢክ ቴቴ ሀገረ ስብከት ውስጥ ከሚገኙ የተለያዩ ቁምስናዎች የተውጣጡ በመቶዎች የሚቆጠሩ ካቶሊክ ምዕመናን በግፍ የተገደሉ ሁለት ኢየሱሳዊ ካህናትን ለማስታወስ ነሐሴ 6/2015 ዓ. ም. በቀረበው የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ተካፋይ ሆነዋል። ዕለቱ በሀገረ ስብከት ምዕራፍ ሲካሄድ የቆየው የብጽዕና አዋጅ ቅድመ ጥናት ማጠቃለያ ቀን እንደ ሆነም ታውቋል።

የአቡነ ዲያማንቲኖ ንግግር

የቴቴ ሀገረ ስብከት ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ዲያማንቲኖ ጉአፖ አንቱነስ በስብከታቸው፥ “ሁለቱ የእግዚአብሔር አገልጋዮች የሕዝባቸውን ስቃይ የተካፈሉ፥ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ ሰላምና እርቅን የሻቱ፥ ሰብዓዊና መንፈሳዊ ባህሪያቸውን ለእግዚአብሔር እና ለሰው ልጆች አገልግሎት የሰጡ ልዩ ሐዋርያዊ አገልጋዮች ነበሩ” በማለት ያመሰገኗቸው ሲሆን፥ የጳጳሱ ንግግር ካኅናቱን በጸሎት ለማስታወስ በመጡ ምእመናን ልብ ውስጥ በጥልቅ ማስተጋባቱ ተነግሯል።

የብጽዕና ጥናት ሂደት

የሁለት ካኅናት የቅድመ ብጽዕና ጥናት ሂደት እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ኅዳር 20/2021 ዓ. ም. የተጀመረ ሲሆን፥ በቴቴ ሀገረ ስብከት ጳጳስ የተሰየመው ኮሚሽኑ ሰፊ ምርመራ ማካሄዱ ታውቋል። እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ከጥር 2022 እስከ ሰኔ 2023 ድረስ ኮሚሽኑ አባ ዮዋዎ ደ ዴኡስ ካምቴዳዛን እና አባ ሲልቪዮ አልቬስ ሞሬራን በሕይወት ዘመናቸው በቅርብ የሚያውቋቸውን ሰዎች በማቅረብ ጥንቃቄ የተመላበት ቃለ መጠይቅ አድርጓል። ምስክሮቹ በእነዚህ ሁለት የእግዚአብሔር አገልጋዮች ሕይወት፣ ሰማዕትነት እና መልካም ስም ላይ ጠቃሚ ግንዛቤዎችን የሰጡ ሲሆን፥ የተሰበሰቡት ምስክርነቶች ከመዝገብ ቤት ሰነዶች ጋር 1,500 ገፆች ባሉት ጠቅላላ መዝበብ ውስጥ መሰብሰባቸው ታውቋል።

የብጽዕና ሂደቱ ቀጣዩ ተግባር መዝገቡን አሽጎ በሞዛምቢክ ለሚገኘው የቅድስት መንበር ሐዋርያዊ እንደራሴ ተወካይ ለሆኑት ብጹዕ አቡነ ፖል አንቶኒ መላክ ሲሆን አቡነ አንቶኒም መዝገቡን ለተጨማሪ ምርመራ በቫቲካን ወደሚገኝ የቅድስና ጉዳዮችን የሚከታተል ጽሕፈት ቤት እንደሚያስተላልፉት ይጠበቃል።

የሰማዕታቱ ታሪክ

የእነዚህ የሁለት ኢየሱሳውያን ካኅናት ልብ የሚነካ ታሪክ የሚጀምረው፥ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በጥቅምት 30/1985 ዓ. ም. በሞዛምቢክ ቻፖቴራ የሚስዮን ቤታቸው አቅራቢያ ካጋጠማቸው አሳዛኝ ታሪክ ሲሆን፣ ሞዛምቢካዊው ካኅን አባ ዮዋዎ ዴ ዴኡስ በቴቴ ግዛት አንጎኒያ በምትባል መንደር እንደ ጎርጎሮሳውያኑ መጋቢት 8/1930 ተወለዱ። እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ1948 ዓ. ም. ወደ ኢየሱሳውያን ማኅበር ዘርዓ ክኅነት ገብተው እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ1953 ዓ. ም. ብራጋ በምትባል የፖርቱጋ ከተማ የምንኩስና መሃላ በመፈጸም፥ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ነሐሴ 15/1964 ዓ. ም. የክኅነት ማዕረግ ተቀበሉ። ለወገኖቻቸው ወንጌልን ለመመስከር ባላቸው ጥልቅ ምኞት በሞዛምቢክ የተለያዩ አካባቢ እነርሱም የምሣላዲዚ፣ የፎንቴ ቦአ እና የሳተምዋ ማኅበረሰቦችን ጨምሮ የተለያዩ አካባቢዎች ሰዎች ባሕል፣ ቋንቋ እና መንፈሳዊነት በሙሉ ልብ ተቀብለው ሐዋርያዊ ተልዕኮአቸውን ፈጽመዋል። ቀጥሎም እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ 1983 ዓ. ም.  ወደ ቻፖቴራ ተዛወረው በሊፊዚ እና ቻብዋሎ ሚሲዮኖች በእረኝነት አገልግለዋል።

እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ሚያዝያ 16/1941 ዓ. ም. በሪዮ ሜኦ ቪላ ዳ ፌይራ በተባለ የፖርቹጋል ግዛት የተወለዱት አባ ሲልቪዮ አልቬስ ሞሬራ፥ እንደ ጎርጎሮሳውያን በ 1952 ዓ. ም. ወደ ኢየሱሳውያን ማኅበር ዘርዓ ክኅነት በመግባት እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ 1959 የምንኩስና መሃላቸውን ፈጽመዋል።  ከ1968 እስከ 1972 በሊዝበን ካቶሊክ ዩኒቨርሲቲ የነገረ መለኮት ጥናት ካደረጉ በኋላ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በሐምሌ 30/1972 ዓ. ም. በፖርቱጋል ኮቪላ የክኅነት ማዕረግ ተቀብለዋል። ሚስዮናዊ አገልግሎታቸውን በቴቴ ሀገረ ስብከት ውስጥ የጀመሩ ሲሆን፥ መጀመሪያ በዞቡዬ የዘርዓ ክኅነት ትምህርት ቤት በኋላም በማቱንዶ ቁምስና አገልግለዋል።እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ 1981 ዓ. ም. ወደ ማፑቶ ተዛወረው፥ በዋነኝነት በማቶላ ውስጥ በአምፓሮ ቁምስና ውስጥ አገልግለዋል። እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በመስከረም ወር 1984 ዓ. ም. ወደ ቴቴ ሀገረ ስብከት ተመልሰው ሃላፊነትን ተቀብለው በሳተምዋ፣ በፎንቴ ቦአ ሚስዮን እና በመጨረሻም በቻፖቴራ ሊፊዚ ሚስዮን አገልግለዋል።

አባ ሲልቪዮ በደፋር እና አስደሳች መንፈሳቸው፥ ለሚስዮናዊነት ባላቸው ፍቅር እና በችግሮች እና በአደጋዎች ውስጥ ደስታን በማግኘት ይታወቁ ነበር። በሚያሳዝን ሁኔታ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በጥቅምት 30/1985 ዓ. ም. እርሳቸው እና አባ ዮዋዎ ዴ ዴኡስ ካምቴዳዛ በሞዛምቢክ ሕዝብ እና በካቶሊክ ማኅበረሰቦች ላይ በደረሰው ረጅም እና ደም አፋሳሽ የእርስ በርስ ጦርነት ሰለባ ሆነዋል።

 

07 September 2023, 17:12