ፈልግ

የመስከረም 6/2016 ዓ.ም ሰንበት ዘዮሐንስ ንባባት እና የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ የመስከረም 6/2016 ዓ.ም ሰንበት ዘዮሐንስ ንባባት እና የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ 

የመስከረም 6/2016 ዓ.ም ሰንበት ዘዮሐንስ ንባባት እና የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ

የእለቱ ንባባት

1.      1 ቆሮንጦስ 11፡17-34

2.     ያዕቆብ 2፡1-13

3.     ሐዋ. 18፡24-28

4.    ዮሐንስ 1፡15-37

የእለቱ ቅዱስ ወንጌል

ዮሐንስም፣ “ ‘ከእኔ በኋላ የሚመጣው ከእኔ በፊት ስለ ነበረ ከእኔ ይልቃል’ ብዬ የመሰከርሁለት እርሱ ነው” በማለት ጮኾ ስለ እርሱ መሰከረ። ከእርሱ ሙላት ሁላችንም በጸጋ ላይ ጸጋ ተቀብለናል፤ ሕግ በሙሴ በኩል ተሰጥቶ ነበር፤ ጸጋና እውነት ግን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል መጣ። ከቶውንም እግዚአብሔርን ያየ ማንም የለም፤ ነገር ግን በአብ ዕቅፍ ያለው አንድያ ልጁ የሆነው አምላክ እርሱ ገለጠው።

መጥምቁ ዮሐንስ ራሱ ክርስቶስ እንዳልሆነ ተናገረ

አይሁድ፣ ማንነቱን እንዲጠይቁት ካህናትንና ሌዋውያንን ከኢየሩሳሌም ወደ እርሱ ሲልኩ፣ ዮሐንስ የሰጠው ምስክርነት ይህ ነበር። ከመመስከርም ወደ ኋላ አላለም፤ “እኔ ክርስቶስ አይደለሁም፤” ብሎ በግልጽ መሰከረ። እነርሱም፣ “ታዲያ አንተ ማን ነህ? ኤልያስ ነህ?” ብለው ጠየቁት። እርሱም፣ “አይደለሁም” አለ። እነርሱም፣ “ታዲያ ነቢዩ ነህ?” አሉት። እርሱም፣ “አይደለሁም” ሲል መለሰ።

በመጨረሻም፣ “እንግዲያስ ማን ነህ? ለላኩን ሰዎች መልስ እንድንሰጥ ስለ ራስህ ምን ትላለህ?” አሉት። ዮሐንስም በነቢዩ በኢሳይያስ እንደ ተነገረው፣ “ ‘ለጌታ መንገድ አቅኑለት’ እያለ በምድረ በዳ የሚጮኽ ድምፅ እኔ ነኝ” ሲል መለሰ።

ከተላኩትም ፈሪሳውያን አንዳንዶቹ፣ “ታዲያ፣ ክርስቶስ ወይም ኤልያስ ወይም ነቢዩ ካልሆንህ፤ ለምን ታጠምቃለህ?” ብለው ጠየቁት። ዮሐንስም እንዲህ ብሎ መለሰላቸው፤ “እኔ በውሃ አጠምቃለሁ፤ እናንተ የማታውቁት ግን በመካከላችሁ ቆሟል፤ 27ከእኔ በኋላ የሚመጣው፣ የጫማውን ማሰሪያ ለመፍታት እንኳ የማልበቃ እርሱ ነው።” ይህ ሁሉ የሆነው ዮሐንስ ሲያጠምቅ በነበረበት ከዮርዳኖስ ማዶ በቢታንያ ነበር።

የእግዚአብሔር በግ

ዮሐንስ በማግስቱም፣ ኢየሱስ ወደ እርሱ ሲመጣ አይቶ እንዲህ አለ፤ “እነሆ! የዓለምን ኀጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ፤ ‘ከእኔ በኋላ የሚመጣው ከእኔ በፊት ስለ ነበር ከእኔ ይልቃል’ ያልሁት እርሱ ነው፤ እኔ ራሴ አላወቅሁትም ነበር፤ በውሃ እያጠመቅሁ የመጣሁትም እርሱ በእስራኤል ዘንድ እንዲገለጥ ነው።”

ከዚያም ዮሐንስ እንዲህ ሲል ምስክርነቱን ሰጠ፤ “መንፈስ እንደ ርግብ ከሰማይ ወርዶ በእርሱ ላይ ሲያርፍ አየሁ፤ በውሃ እንዳጠምቅ የላከኝም፣ ‘በመንፈስ ቅዱስ የሚያጠምቀው፣ መንፈስ ሲወርድና በእርሱ ላይ ሲያርፍ የምታየው እርሱ ነው’ ብሎ እስከ ነገረኝ ድረስ እኔም አላወቅሁትም ነበር፤ አይቻለሁ፣ እርሱ የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆነ እመሰክራለሁ።”

የመጀመሪያዎቹ የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት

በማግስቱም፣ ዮሐንስ ከሁለቱ ደቀ መዛሙርቱ ጋር እንደ ገና እዚያው ቦታ ነበር፤ ኢየሱስንም በዚያ ሲያልፍ አይቶ፣ “እነሆ፤ የእግዚአብሔር በግ!” አለ። ሁለቱ ደቀ መዛሙርትም ይህን ሲናገር ሰምተው ኢየሱስን ተከተሉት።

የእለቱ ቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ

የተወደዳችሁ የእግዚአብሔር ቤተሰቦች እና በጎ ፈቃድ ያላችሁ ሁሉ!

“የዐዋጅ ነጋሪ ድምፅ እንዲህ ይላል፣ የእግዚአብሔርን መንገድ፣ በምድረ በዳ አዘጋጁ፤ ለአምላካችን አውራ ጐዳና፣ በበረሓ አስተካክሉ” (ኢሳያስ 40፡3) የሚለውን የነብዩ ኢሳይያስ የትንቢት አዋጅ ሳይረዱት ቀርተው ዛሬ “አንተ ማን ነህ?” እያሉ በጥይቄ መጥመቁ ዮሐንስን ያጣድፉታል። እሱም የሚተማመንበት ቀድሞም ማንነቱን የተረዳው ምስክርነቱን እንዲህ ሲል ይሰጣል “እስኪ አንተ ማን ነህ? ነብዩ ኤልያስ ነህ?አንተ ነብይ ንህ? እሺ አንተ ማነህ? ብለው ሲጠይቁት ፣ “የጌታን መንገድ አቅኑ ብሎ በምድረ በዳ የሚጮኽው ሰው ድምፅ ነኝ” ይላቸዋል። “እንኳን ከዘመነ ሉቃስ ወደ ዘመነ ዮሐንስ በሰላም አሸጋገራችሁ ያልኳችሁ” ከላይ ያለውን ትዕንቢት ከተተነበየ ከክርስቶስ ልደት በፊት በ700 ክፍለ ዘመን አካባቢ ነበር። ከዚያም በኋላ ዮሐንስ "የእግዚአብሔርን መንገድ አቅኑ፣ ንስሃ ግቡ” እያለ መቶ በዮርዳኖስ ወንዝ ክርስቶስን አጥምቋል።

ታላቁ የክርስቶስ ምስክር ለፈሪሳውያን ምስክርነቱን ሰጠ ፣ ዛሬ እኛ በአዲስ ዓመት ወይም 2016 ዓ.ም ጀምረናል።  ያለፈው ዓመት ሐዋርያው ጳውሎስ በቆርንቶስ መልዕክቱ እንደሚያስተምረን “ሳይገባው ይህንን እንጀራ የበላ ወይም የጌታን ጽዋ የጠጣ ሁሉ የጌታ ስጋና ደም ዕዳ አለበት፣ ሰው ግን ራሱን ይፈትን” ይለናልና የጌታ ባለዕዳ እንዳንሆን ራሳችንን እንመርምር ፣ ራሳችንን መርምረን ድክመታችንን ካወቅን በአዲስ ዓመት ፣ አዲስ ተሰፋ ፣ አዲስ ነገር ፣አዲስ ሕይወት ያስፈልገናልና በያዝነው አዲስ ዓመት ምን አስበናል? ዮሐንስ ስለክርስቶስ እውነት እንደመሰከረ እኛስ እንዴት ስለአምላካችን ፣ ስለ ጌታችን ፣ መድኃኒታችን መመስከር አለብን ? በስራ ገበታችን አብረውን በሚኖሩት ጎረቤቶቻችን ፣ እንዲሁም በጓደኞቻችን መካከል ምን መምሰል (መሆን) አለብን? የቤተክርስቲያን ሕይወታችን ምን መምሰል አለበት? ይህንን ሁሉ መመርመር የሚገባን ነገር ሲሆን እነዚህ ሁሉ ነገሮች ለወደፊቱ ሕይወታችን መቃናት መሰረት ናቸው። እነዚህን ነገሮች ሁሉ በደንብ ተረድተን ከተገበርናቸው ስእተቶቻችንን መርምረን ካስተካከልናቸው በተለይም በቤተክርስቲያናችን ሕይወት ወደ ሚስጥራት ቀርበን (ንሰሃ ገብተን ፣ ቅዱሱን ስጋና ደም) ከተቀበልን ፈሬያቸው ጣፋጭ ይሆንልናል፡፡

 

በዛሬው ቅዱስ ወንጌል ንባብ ማእከል ውስጥ (ዮሐ 1፡29-37) “እነሆ የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ!” (ዮሐንስ 1፡29) የሚል የመጥምቁ ዮሐንስ መልእክት አርፍተ ነገር እናገኛለን። እርሱን ኢየሱስን የሚያመለክት በእይታ እና የእጅ ምልክት የታጀበ መልእክት ነው።

ሁኔታውን በዓይነ ሕሊና እናስብ። በዮርዳኖስ ወንዝ ዳርቻ ላይ ነን። ዮሐንስ እያጠመቀ ነው፣ ከዘጠኝ መቶ ዓመታት በፊት እስራኤላውያንን ከጣዖት አምልኮ ያነጻ የነበረውን እና እውነተኛውን በእግዚአብሔር ላይ የተመሰረት እምነት እንዲኖራቸው አድርጎ የነበረውን ታላቁን ነቢይ ኤልያስን ለብዙዎች ያሳሰበው ሰው ጥምቀትን ለመቀበል ወደ ወንዝ መጥተው በተለያየ ዕድሜ ላይ ያሉ ብዙ ሰዎች፣ ወንዶችና ሴቶች እንመለከታለን። ታላቁ ነቢይ ኤሊያስ በቃል ኪዳኑ አምላክ፣ በአብርሃም፣ በይስሐቅ እና በያዕቆብ አምላክ ላይ ወዳለው እውነተኛ እምነት መለሳቸው።

ዮሐንስ መንግሥተ ሰማያት እንደቀረበች፣ መሲሑም ራሱን ሊገልጥ ነው፣ እናም አንድ ሰው ማዘጋጀት፣ መለወጥ እና በጽድቅ መሥራት እንዳለበት ይሰብካል። ለሕዝቡም የሚጨበጥ የንስሐ መንገድን ለመስጠት በዮርዳኖስ ወንዝ ማጥመቅ ጀመረ (ማቴ. 3፡1-6)። እነዚህ ሰዎች በኃጢአታቸው በመጸጸት ንስሐ ለመግባት፣ የኃጢያት ካሳ ለመክፈል እና ሕይወታቸውን በአዲስ መልክ ለመጀመር መጡ። እርሱ ማለትም መጥመቁ ዮሐንስ ያውቃል፣ መሲሑ የጌታ የተቀደሰ፣ አሁን ቅርብ እንደሆነ ያውቃል፣ እናም እሱን የማወቅ ምልክቱ መንፈስ ቅዱስ በእርሱ ላይ እንደሚወርድ ያውቃል። በእውነት እርሱ እውነተኛውን ጥምቀት፣ የመንፈስ ቅዱስ ጥምቀትን ያመጣል (ዮሐ. 1፡33)።

እናም ጊዜው ደረሰ፡- ኢየሱስ በወንዙ ዳር፣ በሰዎች መካከል፣ እንደ ኃጢአተኛ እንደ ሁላችንም ማለት ነው ሆኖ ታየ። በ30 ዓመቱ ናዝሬት ከሚገኘው ቤቱን ለቆ በወጣ ጊዜ በመጀመሪያ ያደረገው የአደባባይ ተግባሩ ነው፤ ወደ ይሁዳ አገር ወርዶ ወደ ዮርዳኖስ ወንዝ ሄዶ በዮሐንስ እጅ ተጠመቀ። የሚሆነውን እናውቃለን መንፈስ ቅዱስ በርግብ አምሳል በኢየሱስ ላይ ወረደ እና የአብ ድምፅ የተወደደውን የአብል ልጅ ወልድ መሆኑን አውጇል  (ማቴ. 3፡16-17)። ዮሐንስ ሲጠብቀው የነበረው ምልክት ነው። እሱ ነው! ኢየሱስ መሲሕ ነው። ዮሐንስ ግራ ተጋብቷል፣ ምክንያቱም ራሱን በማይታሰብ መንገድ በመግለጥ፡ በኃጢአተኞች መካከል ከእነርሱ ጋር ተጠመቀ ወይም ይልቁንም እንደ እነርሱ ሆነ። መንፈሱ ግን ዮሐንስን አብርቶታል እና በዚህ መንገድ የእግዚአብሔር ፍትህ እንደ ተፈጸመ፣ የማዳን እቅዱ እንደሚፈጸም እንዲረዳው አድርጎታል። ኢየሱስ መሲህ፣ የእስራኤል ንጉስ ነው፣ ነገር ግን በዚህ ዓለም ኃይል ሳይሆን እንደ እግዚአብሔር በግ በመሆን ነው። የዓለምን ኃጢያት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ እርሱ ነው።

ስለዚህም ዮሐንስ እርሱን ለሕዝቡና ለደቀ መዛሙርቱ ጠቁሟል። ምክንያቱም ዮሐንስ እርሱን እንደ መንፈሳዊ መሪ የመረጡት ብዙ ደቀ መዛሙርት ነበሩትና አንዳንዶቹም የመጀመሪያዎቹ የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ሆነዋል። ስማቸውን በደንብ እናውቃቸዋለን፡- በኋላ ጴጥሮስ የተባለው ስምዖን፣ ወንድሙ እንድርያስ፣ ያዕቆብና ወንድሙ ዮሐንስ። ሁሉም እንደ ዓሣ አጥማጆች፣ ሁሉም እንደ ኢየሱስ የገሊላ ሰዎች ነበሩ።

ውድ ወንድሞች እና እህቶች፣ ለምን በዚህ ትዕይንት ላይ ለረጅም ጊዜ ትኩረት ሰጠን? ብለን ልንጠይቅ እንችል ይሆናል። ምክንያቱም ወሳኝ ነገር ነው! ተረት አይደለም። ወሳኝ ታሪካዊ እውነታ ነው! ይህ ትዕይንት ለእምነታችን ወሳኝ ነው፣ እናም ለቤተክርስቲያን ተልእኮም ወሳኝ ነው። ቤተክርስቲያን፣ በሁሉም ጊዜ፣ መጥምቁ ዮሐንስ ያደረገውን እንድታደርግ ተጠርታለች፡ ኢየሱስን ለህዝቡ ማሳየት ይኖርባታል፣ “እነሆ የዓለምን ኃጢአት የሚያጠፋ የእግዚአብሔር በግ!” በማለት ወደ እርሱ ልትጠቁም ይገባታል። እርሱ አንድ አዳኝ ነው! እርሱ በኃጢአተኞች መካከል ትሑት የሆነ ጌታ ነው፥ እርሱ ግን እርሱ ነው፤ የሚመጣ ሌላ ኃያል የለም፤ አይደለም እርሱ ነው፣ የእግዚአብሔር በግ ነው!

እኛ ካህናት በቅዳሴ ጊዜ ኅብስቱና ወይኑ ለሕዝብ ስናቀርብ የክርስቶስ ሥጋና ደም እንዲሆን ዕለት ዕለት የምንደግማቸው እነዚህን ቃላት ነው። ይህ የአምልኮ ምልክት እራሷን የማታወጅውን፣ ነገር ግን ክርስቶስን ብቻ የምታውጀውን የቤተክርስቲያንን ተልእኮ በሙሉ ይወክላል። ቤተክርስቲያን እራሷን ስታውጅ ወዮላት፣ ወዴት እንደምትሄድ አታውቅም! ቤተ ክርስቲያን ክርስቶስን ታውጃለች፣ ራሷን አታውጅም፣ ክርስቶስን ታመጣለች። ምክንያቱም ህዝቡን ከአጢያት የሚያድናቸው፣ ነጻ የሚያወጣቸው እና ወደ ተስፋይቱ ምድር የሚመራቸው   እውነተኛ ነፃነት የሚሰጣቸው እሱ እና እሱ ብቻ ነው።

አምነን መከተል እንደሚገባን በሚገባ መረዳት እንችል ዘንድ የእግዚአብሔር በግ እናት ድንግል ማርያም በአማላጅነቷ ትርዳን።

16 September 2023, 10:26