ፈልግ

ሲስተር ጆሴፊና አልቡከሪክ በሽልማት ሥነ ስርዓቱ ላይ ሲስተር ጆሴፊና አልቡከሪክ በሽልማት ሥነ ስርዓቱ ላይ 

ታታሪዋ የካቶሊክ መነኩሴ በፊልም ሥራ ወደ ወጣቶች እየቀረቡ እንደሆነ ተነገረ።

በህንድ ምዕራብ ሙምባይ የሚኖሩት ሲስተር ጆሴፊና አልቡከርኪ የተባሉ የካቶሊክ መነኩሴ ለፊልም ስራ እና ለትምህርት በነበራቸው ፍቅር እና በፊልም ኢንደስትሪ ውስጥ የራሳቸውን አሻራ ለማስቀመጥ ብሎም ወጣቶችን በአንድነት ለማሰባሰብ በሁለት ቀናት ውስጥ በተንቀሳቃሽ ስልክ ብቻ የተቀረጸ በእምነት የተሞላ የ7 ደቂቃ ልብ ወለድ ፊልማቸውን እንዲሰሩ አስችሏቸዋል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

በምእራብ ህንድ ሙምባይ ከተማ የሚኖሩት ሲስተር ጆሴፊና አልቡከርኪ የተባሉ ካቶሊካዊት መነኩሴ በዘመኑ ወጣቶች ላይ ያነጣጠረ የሲኒማ ስራ በመስራት ወደ ፊልም ኢንደስትሪ ለመግባት ተነሳሽነቱን ወስደዋል።

ይህ ድንቅ ስራቸው በተንቀሳቃሽ ስልክ የተሰራ አጭር ፥ ግን ኃይለኛ መልዕክት ያለው የሰባት ደቂቃ ልብወለድ ፊልም በሁለት ቀናት ውስጥ ብቻ ተጠናቋል።
ሲስተር ጆሴፊና የኢየሱስ እና የማርያም ጉባኤ ማህበር አባል ሲሆኑ ፥ በአሁኑ ጊዜ በባይኩላ ግዛት ሙምባይ ከተማ በሚገኘው የቅዱስ አግነስ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የሚያስተምሩ አልፎ ተርፎም የትምህርት ቤቱ ርዕሰ መምህርም ናቸው። አስተማሪ ከመሆን በተጨማሪ ለፊልም ስራ ከፍተኛ ፍቅር የነበራቸው ሲስተሯ የመጻፍ ችሎታ ባይኖራቸውም ፥ ነገር ግን በሲኒማቶግራፊ ሙያ ውስጥ ጥሩ የሚባል ደረጃ ላይ ነበሩ። የኮቪድ-19 ወቅት ለፊልም ስራ እና አርትዖት የሚያስፈልጉ አንዳንድ ክህሎቶችን እንዲማሩ እድል ሰጥቷቸዋል።

ሲስተር ጆሴፊና በአሬይ ጫካ ውስጥ የሚኖሩትን የአከባቢው ተወላጅ ጎሳዎችን ሲጎበኙ በአኗኗራቸው ተማርከው ነበር። ይህ ጉብኝታቸው "በባንያን ዛፍ ስር፡ ራስን የማግኘት መንገድ" በሚል ርዕስ ዘጋቢ ፊልሙን እንዲቀርጹ አነሳሳቸው። ፊልሙ የገንዘብ ምቾትን ትቶ ሙምባይ በሚገኘው የአሬይ ጫካ ውስጥ በመኖር ፥ ሰዎች ለመብታቸው በመቆም እውነተኛ ጥሪያቸውን እንዲያገኙ የሚያስተምረውን የአንድ ኢንጅነር ህይወት ይተርካል።

ሲስተር ጆሴፊና በአሬይ ጫካ ውስጥ ስለሚኖሩ ጎሳዎች የሚያሳይ ዘጋቢ ፊልም በመስራት በሲኒማቶግራፊ ችሎታቸው አድናቆት እና ከበሬታን አግኝተዋል።
"በገዳማዊ ህይወቴ የወጣቶች አገልግሎት ሀላፊ እንደመሆኔ መጠን ፥ ወጣቶቻችን አብዛኛውን ጊዜያቸውን በማህበራዊ ድረ-ገጾች ላይ እንደሚያውሉ ተመልክቻለሁ። ስለዚህ እነሱን ማግኘት የምችለው በሚዲያ እና በዲጂታል ጥናቶች እራሴን በማጠናከር ብቻ ነው ብዬ አምን ነበር። ይሄንንም ለማድረግ ፕሮፌሽናል የፊልም ሥራ ኮርሶችን መውሰድ ያስፈልግ ነበር” ሲሉ ሲስተር ጆሴፊና ከቫቲካን ዜና ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅት የት/ቤቱ ርዕሰ መምህር በመሆን ከማገልገል በተጨማሪ በሙምባይ ከተማ ባንድራ አውራጃ በሚገኘው የቅዱስ ጳውሎስ ኮሙኒኬሽን ማዕከል የፕሮፌሽናል ፊልም ስራ ኮርስ መከታተል ጀምረዋል። በፕሮፌሽናል ፊልም ስራ ውስጥ የኮርሱ አካል ሆነው በልጆች ህይወት ላይ ፊልም ለመስራት እንደተነሳሱም ተናግረዋል።
ሲስተር ጆሴፊና “D for Dumbo” የተሰኘውን ዘጋቢ ፊልም የሰሩት ውስን በሆነ የገንዘብ በጀት በማሮል አንኸሪ ግዛት ፡ ሙምባይ ከተማ በሚገኘው በወንጌላዊ ቅዱስ ዮሐንስ ትምህርት ቤት ውስጥ ነው።

ዘጋቢ ፊልሙም ሳም የተባለ የአራተኛ ክፍል ተማሪ እንደ ክፍል ጓደኞቹ በፍጥነት የሂሳብ ሰንጠረዦችን መቁጠር ባለመቻሉ የክፍል ጓደኞቹ ሲሳለቁበት በሚገልጽ ትረካ የሚጀምር ሲሆን ፥ ነገር ግን ‘ደደብ’ ተብሎ የተጠራው ልጅ ፥ ሌላ አስተማሪ ለተማሪዎቹ ሌላ የፈጠራ ስራ እንዲሰሩ ሲመድባቸው ፥ የክፍሉ ተማሪዎችን በተሻለ ሁኔታ ሲበልጣቸው ይታያል።

ፊልሙ ባንድራ ፣ ሙምባይ ከሚገኘው የቅዱስ ጳውሎስ ተቋም ምርጡን ሽልማት ያገኘ ሲሆን ፥ ሲስተር ጆሴፊና ሽልማቱንም የተቀበሉት ከታዋቂው የቦሊውድ ተዋናይ ናሲሩዲን ሻህ እጅ ነው። ፊልሙ በአሁኑ ጊዜ ኦንላይን በሚካሄደው ‘ALP ኢንተርናሽናል ፊልም ፌስቲቫል’ ላይ እንዲሳተፍም ታጭቷል። እንደ ሲስተር ጆሴፊና ገለጻ ፊልሙ የተሰራው በውስን ሃብት ሲሆን ፥ የርዕሱም መልዕክት “በተወሰነ ደረጃ ለሁሉም ሰው እንደሚያስተጋባ” ገልፀው ፥ “ናሲሩዲን ሻህ ስሜን ከሌሎቹ ለይቶ ሲያወጣ እና ከዋናው ገፀ ባህሪ መለየቱን ሲናገር ለእኔ በጣም አስገርሞኝ ነበር” ብለዋል።

ስለ ሽልማቱም ሲናገሩ “ለፊልም ስራ እና ለትምህርት ያለኝን ፍቅር በማቀናጀት ብዙ ተመልካቾችን ማግኘት እንደምችል እና እምነት እንዳለኝ እውቅና እና ማረጋገጫ ሆኖኛል” ብለው ገልፀዋል።
ሲስተር ጆሴፊና በመጨረሻም “ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በወቅቱ ምሳሌዎችን ሲጠቀም የነበረው በዘመኑ ከነበሩት ሰዎች ጋር ለመግባባት ነው። ዛሬ ባለው ሁኔታም ፥ ፊልሞች የእግዚአብሔርን ቃል ለዓለም ለማዳረስ በጣም ውጤታማ ከሆኑ መንገዶች አንዱ እንደሆነ አምናለሁ” ብለዋል።

‘የሺህ ኪሎ ሜትሮች ጉዞ የሚጀምረው በአንድ እርምጃ ነው’ ሲል የቻይናዊያን አባባል ይነግረናል ፥ እናም በፊልሙ ዓለም ውስጥ ትንሽም ቢሆን የመጀመሪያ የሆነውን ሥራቸውን ሲሰሩ ይህ አባባል በሲስተር ጆሴፊና ታሪክ ውስጥ እጅግ በጣም እውነት ሆኖ እናገኘዋለን።
 

07 September 2023, 15:57