ፈልግ

የምሪዝ ሪጄቺ ፖርታል ድረ-ገጽ ተባባሪዎች የምሪዝ ሪጄቺ ፖርታል ድረ-ገጽ ተባባሪዎች 

የክሮሺያ ካቴኪስቶች ጥራት ባለው የዲጂታል ይዘት ወንጌልን እየሰበኩ ነው ተባለ።

በስፕሊት-ማካርስካ ሃገረ ስብከት ሃዋሪያዊ ጽህፈት ቤት የሚደገፈው በክሮኤሺያ የሚገኙ የሀይማኖት ትምህርት መምህራን ቡድን ከማስተማሪያ ክፍሎቻቸው በተጨማሪ ካሉ ሰዎች ጋር ለመቀራረብ በመፈለግ የበፊቱን የማስተማሪያ የአሰራር ስልት እየቀየሩ ነው።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

በብዙ የዓለም ክፍሎች ያሉ ተማሪዎች የኦን ላይን ቴክኖሎጂ ባመጣላቸው ዕድል ሕይወታቸውን እና ትምህርታቸውን በማሻሻል ላይ ይገኛሉ። እነዚህ ተማሪዎች ይሄንን የሚያረጉት ለጊዜ ማሳለፊያ ብቻ ሳይሆን የመረጃ ምንጮችን ለመፈለግ እና ለመማር በተለያዩ ድህረ ገፆች ላይ ቆይታ ያደርጋሉ። ጥያቄው በድንገት የሚነሳው እንደ ሃይማኖት፣ ጓደኝነት እና የአኗኗር ዘይቤ ባሉ ርዕሶች ላይ የመረጃ ምንጫቸው ማን ነው? ስለ ሕይወትስ ትርጉም መልስ የሚሰጣቸው ማን ነው? የሚለው ጉዳይ ነው።
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ በ 2012 ዓ.ም. በተከበረው የዓለም የመገናኛ ብዙኃን ቀን ላይ ባስተላለፉት መልዕክታቸው ላይ እንዳስታውሱት ፥ የዲጂታል ዓለም “ከሰው ልጅ የዕለት ተዕለት ኑሮው የማይለይ ነው” ብለዋል። የሰው ልጅ እውቀትን የሚያከማችበት፣ መረጃ የሚያሰራጭበት እና ግንኙነቶችን የሚያዳብርበትን መንገድ እየቀየረ ነው። በዚህም ምክንያት በክሮሺያ የሚገኙ የሃይማኖት አስተማሪዎችም ለዚህ ጥሪ ምላሽ በመስጠት በዲጂታሉ ሰፊ ጎዳና ላይ እየተጓዙ ይገኛሉ።
እነዚህ መምህራን ለበርካታ ወራት በፈቃዳቸው የተከፈተውን ‘ምሪዝ ሪጄቺ’ (Mreze Riječi) የተሰኘውን የዌብ ፖርታል ፕሮጀክት በመተግበር ላይ የሚገኙት በስፕሊት-ማካርስካ ሃገረ ስብከት ሃዋሪያዊ ጽሕፈት ቤት ድጋፍ ነው።
ግባቸው ተማሪዎችን ብቻ ሳይሆን በዲጂታሉ ዓለም ላይ ያሉትን ሁሉ ፥ ስለ ቤተክርስቲያን አስተምህሮ እና በሌሎችም ርዕሰ ጉዳዮችን ከክርስቲያናዊ እይታ የበለጠ መማር እና መረዳት የሚፈልጉትን ማበረታታት እና ማስተማር ነው።

ደፋር እርምጃዎች ወደ አዳዲስ መስኮች

የፖርታል ድረገፅ ፕሮጄክትን ከጀመሩት የሃይማኖት መምህራን አንዱ የሆኑት ዶ/ር ኔናድ ፓላክ ስለ ኢንሼቲቩ ግቦች ለቫቲካን ኒውስ እንደተናገሩት “የሃይማኖት አስተማሪዎች እንደመሆናችን መጠን የዚህ አብዮት አካል መሆን እና በድፍረት ወደ አዲስ መስኮች መግባት እንፈልጋለን” ብለዋል።
የሃይማኖት መምህራኑ ተልእኮ ሥራ በዋነኛነት ከመማሪያ ክፍሎች ጋር የተያያዘ ቢሆንም ፥ የኢንሼቲቩ አባላት ይህን ምስል ለመቀየር ወስነዋል። አንዴ የተማሪዎቻቸው ልማዶች እንደተለወጠ ካዩ በኋላ ኦንላይን የመገኘትን ጥቅሞችን ማሳለፍ አልፈለጉም ነበር። ይህንንም ሲያስረዱ “ተማሪዎቻችን የቀኑን አንድ ሶስተኛ የሚሆነውን ጊዜያቸውን ስልካቸው ላይ እንደሚያሳልፉ እናውቃለን። በእነዚህ ሂደቶች ላይ ከእነሱ ጋር በመገኘት ፥ ጥራት ያለው ይዘት ልናቀርብላቸው እና በመጨረሻም በህብረት ህያው ከሆነው ከጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጋር እንዲገናኙ ልንመራቸው እንፈልጋለን” ብለዋል ዶ/ር ፓላክ።
ይህ የፖርታል ድረገፅ ከመስከረም ወር መጀመሪያ ጀምሮ ሁሉም በጎ ፈቃደኛ የሆኑ ከ30 በላይ ገዳማዊያን እና ምእመናን ተባባሪዎችን ይዟል። ከእነዚህም አንዳንዶቹ ተጨማሪ ትምህርት ማለትም እንደ ሳይኮቴራፒ ወይም በተለያዩ የትምህርት ዘርፎች የዶክትሬት ዲግሪ ያላቸው የሀይማኖት አስተማሪዎች ናቸው።
እንዲሁም በማህበራዊ ፣ በህክምና እና ሌሎች ሙያዎች ላይ የተሰማሩትን ከካሪታስ የመጡ እና በየሙያ ዘርፎቻቸው ውስጥ የስልጠና ይዘትን አዘጋጅተው የማስተማር ፍላጎት ያላቸውን ሌሎች ባለሙያዎችን ያካተተ ነው።

እንደ ማህበረሰብ መስበክ

ድረ ገፁ ከቤተክርስቲያን ዜና እስከ ተለያዩ አምዶች በተግባራዊ የህይወት ጉዳዮች ላይ ምክሮችን የያዘ ሰፊ ይዘትን ያቀርባል። እንዲሁም ቡድኑ በድምፅ የተዘጋጁ መሰናዶዎችን እና የወንጌል አስተንትኖዎችን እንዲሁም በየሳምንቱ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁራን የእሁድ የወንጌል ምንባባትን የሚያብራሩበትን ቪዲዮዎችን ያዘጋጃል።
“የድረገፁ ተልእኮ ክርስቲያናዊ እሴቶችን ቀላል እና ተግባራዊ በሆነ መንገድ ማስተላለፍ ነው። በተጨማሪም ስኬታማ፣ መልካም የሆነ እና ጥራት ያለው ህይወት ለመምራት ማስቻልም ነው። ለዚያም ነው ወንጌልን የይዘቱ ዋና ትኩረት አድርገን እንድንሰራ አስፈላጊ የሆነው” በማለት የስፕሊት-ማካርስካ ሃገረ ስብከት ሃዋሪያዊ ስራ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ የሆኑት ፕሮፌሰር ጃድራንካ ጋርማዝ አብራርተዋል።
የኦንላይን መንፈሳዊ ትምህርት ፍሬዎች ድረ ገፁ ወይም ፖርታሉ ከተከፈተ ከጥቂት ወራት በኋላ ነው የሚታዩት። ፕሮፌሰር ጋርማዝ ከቫቲካን ዜና ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ አጽንኦት ሰጥተው እንደገለጹት በመጀመሪያ ደረጃ ፍሬዎቹ “በሃይማኖት መምህራኑ እና ቀደም ብለው በተመሰረቱ የሥራ ባልደረቦቻቸው መካከል ያለውን ታላቅ ማህበረሰብን” ያካትታል ብለዋል።
ይህ የኦን ላይን ትስስር የቫቲካን የኮሙኒኬሽን ጽ/ቤት (የቫቲካን ዜና መስራች ድርጅት) ሃዋሪያዊ አስተንትኖ ከሆነው እና “በሙሉአት ወደ መገኘት ጉዞ” በሚል ካዘጋጀው ሰነድ ጋር ይስማማል። ሰነዱ ቤተክርስቲያን እንደ ግለሰብ ሳይሆን እንደ ማህበረሰብ በኦንላይን እንድትሰራ ያሳስባል።
እንደ ሰነዱ ዋና ነጥብ ከሆነ ‘እንደ ግለሰብ ተፅእኖ ፈጣሪዎች’ ሳይሆን መንቀሳቀስ ያለብን ፥ ‘በኅብረት እንደሚሰሩ ሸማኔዎች’ በመሆን ተስጥኦዋችንን እና ችሎታችንን በማቀናጀት እውቀትን እና ስጦታችንን ማካፈል እንደሚገባ ያብራራል።

ክርስትናን ጥራት ባለው ይዘት ማስፋፋት

ፕሮፌሰር ጋርማዝ ጥራት ባለው ይዘት ላይ በማተኮር ወንጌልን በጋራ ማሰራጨት አስፈላጊ መሆኑን ይስማማሉ።
“የሃይማኖት መምህራንን ችሎታ ለማሳደግ እና በዲጂታል ዓለም ላይ የዲጂታል አሻራቸውን እንዲተዉ እናስተምራለን። አላማችን ክርስቲያናዊ አኗኗርን በጥራት ለማሳየት እንዲችሉ አቅማቸውን ማጎልበት ነው” ብለዋል።
የዌብ ፖርታል ቡድን አባላቱ በፕሮጀክቱ ላይ በሚሰሩበት ጊዜ ሌሎች በማስተማር ላይ የሚገኙትን ብዙ ያልታወቁ የተሰጥኦ ባለቤቶችን አግኝተዋል። ይህ ‘የዲጂታል ቃላት ትምህርት ቤቱ’ የተቋቋመው በድምጽ ስርጭት (ፖድካስት) ላይ ፍላጎት ያላቸውን ፥ እንዲሁም ‘የጽሑፍ እና የንግግር ቃላት ትምህርት ቤት’ ውስጥ ለማስተማር ነው።
በክሮሺያ ያለው የሃዋሪያዊ ቡድን ሥራ የክርስቲያን ማህበረሰቡ ለፈጠራ ጠንካራ መሠረት በመጣል እና አዳዲስ መንገዶችን በመክፈት የምሥራቹን ቃል በዲጂታሉ ዓለም ለማሰራጨት እንዴት እንደሚሠራ ያሳያል ተብሏል።
 

14 September 2023, 14:28