ፈልግ

የብጹዕ ካርዲናል ማቴዎ ዙፒ የፋይል ፎቶ (2019) የብጹዕ ካርዲናል ማቴዎ ዙፒ የፋይል ፎቶ (2019)  (Francesco Pierantoni)

ብፁዕ ካርዲናል ዙፒ በዩክሬን የሚደረገው የሰላም ጥረት ጫና ስር መውደቅ ዬለበትም አሉ

ካርዲናል ማትዮ ዙፒ በዩክሬን 'ጥበብ የተሞላበት ሰላም' አስፈላጊነትን አጉልተው በመግለጽ ፥ በዩክሬን ሰላምን የመፈለግ ተልዕኮ አካል የሆነውን ወደ ቤጂንግ ስለሚያደርጉት ጉዞ ከጋዜጠኞች ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ ሰጥተዋል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

የጣሊያን ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዝዳንት ብፁዕ ካርዲናል ማትዮ ማሪያ ዙፒ በዩክሬን እየተካሄደ ስላለው ጦርነት በበርሊን ከተካሄደው ዓለም አቀፍ ስብሰባ ላይ አንስተው ንግግር አድርገዋል።
ከጳጉሜ 5 - መስከረም 1 2016 ዓ.ም. ድረስ “የሰላም ድፍረት” በሚል መሪ ቃል የተካሄደው ስብሰባ በጀርመን ዋና ከተማ ከሚገኙት የካቶሊክ እና ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ጋር በመተባበር በቅዱስ ኤጊዲዮ ማህበረሰብ አስተናጋጅነት ተካሂዷል። ዝግጅቱ ከ40 የተለያዩ ሀገራት የተውጣጡ የባህል እና የፖለቲካ መሪዎችን ጨምሮ የዓለም ታላላቅ ሃይማኖቶች መሪዎችን ያሰባሰበ ሲሆን ፥ እ.አ.አ. በ1986 በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ መሪነት በአሲሲ የተካሄደው የሃይማኖቶች የጋራ የሰላም ጸሎት ትሩፋት ነው።

የሰላም ተልዕኮ እና የቻይና ጉብኝት

ለጋዜጠኞች ጥያቄ ምላሽ የሰጡት የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት የዩክሬን ልዩ የሰላም መልዕክተኛ የሆኑት ብፁዕ ካርዲናል ዙፒ በዩክሬን ውስጥ ላለው ጦርነት መፍትሄ መፈለግ እንደሚያስፈልግ ጠቁመው ፥ አጥቂውን ከተጠቂው መለየት አስፈላጊ መሆኑንም አመላክተዋል።
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ስለሰጧቸው የሰላም ተልዕኮ እና በዚህም ምክንያት ወደ ዩክሬን፣ ሩሲያ እና አሜሪካ ስላደረጉት ጉዞም አብራርተዋል።
ካርዲናል ዙፒ በቅርብ ጊዜ ውስጥ ይጓዛሉ ተብሎ በሚጠበቀው እንደ ቻይና ያሉ ቁልፍ ሃገራትን በማሳተፍ ፍትሃዊ እና አስተማማኝ ሰላም ላይ መስራት አስፈላጊ መሆኑን አሳስበዋል።
ዩክሬናውያን የራሳቸውን የሰላም መንገድ በመወሰን ረገድ የሚያደርጉትን ሚና በማጉላት ያለነሱ ተሳትፎ እውነተኛ ሰላም ማምጣት እንደማይቻል በድጋሚ ተናግረዋል። ሰላም የሁሉንም ሰው ጥረት የሚጠይቅ ቢሆንም "በፍፁም በማንም ሰው ጫና ስር ሊወድቅ የሚችል ነገር አይደለም ፤ ሁሉም ሰው ዋስትና የሚያገኝበት ፣ ቁርጠኝነት እና ጥረት የሚፈልግ በዩክሬናውያን የተመረጠ ሰላም መሆን አለበት" ብለዋል።

ለዩክሬን የሚደረግ ጳጳሳዊ ድጋፍ

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ በሴንት ፒተርስበርግ ለወጣት ሩሲያውያን ያደረጉትን ንግግር ተከትሎ በቅርቡ ከኪየቭ ጋር የተፈጠረውን ውጥረት በተመለከተ ብፁዕ ካርዲናል ዙፒ እነዚህ ጉዳዮች እንደሚፈቱ ያላቸውን እምነት ገልጸው ፥ በመከራ ጊዜ ቤተ ክርስቲያን እና ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ለዩክሬን ያላቸውን ድጋፍ አጉልተው አሳይተዋል።
የሰላም ጎዳናዎች ራሳቸው አንዳንድ ጊዜ “ያልተጠበቁ እንደሚሆኑ እና ወደ አንድ አቅጣጫ ለመጓዝ የሁሉም ቁርጠኝነት እና ተሳትፎ እንዲሁም ስለ ሰላም ሲባል ብርቱ ትብብር እንደሚያስፈልግ” ለማስረዳት ብፁዕ ካርዲናሉ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስን ‘ጥበብ የተሞላበት ሰላም’ እንዲሰፍን ያላቸውን ፍላጎት አስተጋብተዋል።

“ሰላም ቶሎ መምጣት አለበት”

ካርዲናል ዙፒ ስለ ዲፕሎማሲው ስራ መዘግየት ለተሰነዘረው ትችት ምላሽ ሲሰጡ ፥ እርምጃ ስለመውሰድ እና ለውጥ ለማምጣት መሞከር አስፈላጊ መሆኑን አንስተው ተከራክረዋል።
“ምንም ካላደረግክ ትወድቃለህ ፥ ስለዚህ የሆነ ነገር አርግ” ካሉ በኋላ “ሁልጊዜ መሞከር የተሻለ ነው” በማለትም አክለዋል።
እንደ እውነቱ ከሆነ በጦርነት ምክንያት የሚደርሰውን ስቃይ ስንጋፈጥ ሰላም ብዙውን ጊዜ ዘግይቶ ነው የሚመጣው ፥ ነገር ግን ቶሎ መምጣት አለበት ብለዋል።
ብፁዕ ካርዲናል ዙፒ በማጠቃለያቸው ክፍልፍል፣ ዓመፅ እና ኢፍትሃዊነት ያፈረሱትን መልሶ ለመገንባት በትዕግስት መስራት እንዳለብን እና የተቀናጀ ጥረት እንዲደረግ ጥሪ አቅርበዋል።
“ጊዜው እንዲሰክን እና ጊዜን እንዴት መቆጣጠር እንደሚገባን ለማወቅ ትዕግስት ያስፈልጋል ፥ ሁልጊዜ ሰላም መምጣት አለበት ፥ በተቻለ ፍጥነት በአስቸኳይ መምጣት አለበት” በማለት አስታውሰዋል።
 

14 September 2023, 17:15