ፈልግ

ብጹዕ ካርዲናል ሎፔዝ ሮሜሮ ብጹዕ ካርዲናል ሎፔዝ ሮሜሮ 

ካርዲናል ሎፔዝ ር.ሊ.ጳ. በማርሴይ የሚያደርጉት ጉብኝት ድንበር የለሽ ሰላምን ለማበረታታት ነው አሉ

ማርሴ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ለሜዲትራኒያን ሃገራት ስብሰባዎች መምጣትን እየጠበቀች ባለችበት ወቅት ፥ የራባት ሃገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የሆኑት ብፁዕ ካርዲናል ሎፔዝ ሮሜሮ ሕዝቦችን በሰላም አንድ ለማድረግ ለሚደረገው የማኅበረ ቅዱሳን ሥራ ያላቸውን ተስፋ ገልፀዋል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

የጥንት ሮማውያን ‘ማሬ ኖስትረም’ ወይም “ባህራችን” ብለው በሚጠሩት አካባቢ የሰላም መንገዶችን ለማግኘት ሰባ የሜዲትራኒያን ሃገራት ጳጳሳት በሜዲትራኒያን ስብሰባ ላይ ለመሳተፍ በደቡብ ፈረንሳይ ከተማ ማርሴይ ደርሰዋል።
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ዛሬ እለተ አርብ ማርሴ ከመግባታቸው በፊት የሞሮኮዋ ራባት ከተማ ሊቀ ጳጳስ የሆኑት ብፁዕ ካርዲናል ክሪስቶባል ሎፔዝ ሮሜሮ በማርሴይ ቅድስት ማርያም ማጆር ካቴድራል ሐሙስ ዕለት ለጳጳሳት የመክፈቻውን ሥርዓተ ቅዳሴ መርተዋል።
ብፁዕ ካርዲናል ሎፔዝ ሮሜሮ ከቫቲካን ዜና ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ በሜዲትራኒያን ስብሰባዎች እና በርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ በሚገኙበት የቅዳሜ ዕለት ማጠቃለያ ዝግጅት ላይ ያላቸውን አስተያየት ሰጥተዋል። እንደሚከተለው ይቀርባል፤


ጥያቄ፡- እንደ የራባት ሊቀ ጳጳስነቶ እና የሰሜን አፍሪካ ጳጳሳት ጉባኤ (CERNA) ፕሬዝዳንትነቶ በማርሴይ በሚደረገው የሜዲትራኒያን ሃገራት ስብሰባ ላይ ምን አስተያየት አለዎት?

መልስ ፦ እኛ የየሰሜን አፍሪካ ጳጳሳት ጉባኤ ጳጳሳት ለምዕመናኖቻችን ከስምንት ዓመታት በፊት "የተስፋ አገልጋዮች" በሚል ርዕስ የሃዋሪያነት ደብዳቤ ሰጥተናል። እነዚህ ስብሰባዎች የተስፋ ምንጭ ሊሆኑ ይችላሉ።
በባሪ፣ በፍሎረንስ እና አሁን ደግሞ ማርሴይ ላይ የተካሄዱት ስብሰባዎች ምንም እንኳ ልዩነቶቻችን እንዳለ ቢሆኑም ሁላችንም የሜዲትራኒያን ባህር ሃገራት መሆናችንን እንድንገነዘብ ረድተውናል። ይህም የሜዲትራኒያን ባህርን የሰላም ድንበር ሳይሆን የድንበር የለሽ ሰላም መፍለቂያ እንድናደርግ ይጋብዘናል። የነዚህ ስብሰባዎች የመጀመሪያ ፍሬ ሰላምን ማስፈን እና በአንድነት ማደግ መሆን አለበት።

ጥያቄ፡- በእዚህ ስብሰባ ላይ ከተሰበሰቡ ሌሎች ጳጳሳት ጋር ምን ምን ሃሳቦችዎን ሊያጋርዋቸው አስበዋል? የእርስዎስ ዋና ጉዳይ ምንድን ነው?

መልስ፦ በመጀመሪያ አንድነታችንን ማወቅ አለብን። ከሚያለያየን ነገር ይልቅ አንድ የሚያደርገን ይበልጣል ፥ ይህ ምክንያታዊ ነው ፥ ምክንያቱም ሁላችንም ጳጳሳት ነን ፥ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አንድ የሚያደርገን አንድ አይነት እምነት ነው የምንጋራው። ከዚህ አንድነት በመነሳት በሜዲትራኒያን ባህር ሰላምና አንድነት እንዲሰፍን የበኩላችንን አስተዋፅኦ ማድረግ አለብን። በዚህ ክልል ብዙ የግጭት እና የውጥረት ክስተቶች ተፈጥረዋል ፥ እስቲ አስቡት የባልካንን፣ ክሮሺያን እና ሰርቢያን፣ ሞሮኮ እና አልጄሪያን፣ ግሪክን እና ቱርክን፣ እስራኤልን እና ፍልስጤምን ብቻ ሳይሆን የጥቁር ባህር አካል የሆኑትን በአጠቃላይ ግን የሜዲትራኒያን ክፍል የሆኑትን እነ ሶሪያ፣ ኢራቅ ወይም ዩክሬን እና ሩሲያን መጥቀስ ይቻላል። እንደ ብሔርተኛ የጋራ ጥቅም ሳይሆን ሁላችንም ለዓለም አቀፋዊ የጋራ ጥቅም የምንሠራ ወንድማማቾች መሆናችንን ልናጤነው ይገባል።
ለምን የሜዲትራኒያን ማህበረሰብን አትፈልግም? በሰሜን እና በደቡብ የባህር ዳርቻዎች መካከል ለምን የትብብር መንፈስ አይጨምርም? እንዲሁም ለምስራቅ እና መካከለኛው ምስራቅ የባህር ዳርቻዎች ድጋፍ ለምን አይጨምርም? በሜዲትራኒያን ሃገራት ስብሰባዎቻችን ውስጥ ሰላም እና አንድነት ቁልፍ ቃላት እንደሆኑ አምናለሁ።

ጥያቄ፡- ከቀን ወደ ቀን አሳሳቢ እየሆነ የመጣውን የስደት ቀውስ እንዴት ያዩታል? ይህ ከቱኒዚያ እስከ ጣሊያን፣ ከሞሮኮ እስከ ስፔን የተዘረጋ ውስብስብ ጉዳይ ነው። ቤተክርስቲያን ምን ማድረግ ትችላለች ይላሉ?

መልስ፦ በዚህ ጉዳይ ላይ ጠንክረን እየሰራን ነው። የፊታችን እሑድ የዓለም የስደተኞች እና የፍልሰተኞች ቀን ሲሆን የዘንድሮው መሪ ሃሳብ “ለመሰደድ ነፃነት ፥ ለመቆየትም ነፃነት” የሚለው ነው። መሰደድ ሰብአዊ መብት ነው ፥ ነገር ግን ከዚያ የመሰደድ መብት በፊት ሁሉም ሰው በተወለደበት እና ባደገበት አከባቢ በነፃነት የመቆየት መብት አለው።
ቤተክርስቲያኗ ከመንግሥታት እና ከሲቪል ማህበረሰብ ጋር በመተባበር ሰዎች እነዚህን መብቶች እንዲያውቁ እና እነሱን ለመጠቀም እንዲታገሉ ትረዳለች። መብት ከሰማይ አይወድቅም ፥ ልንጠይቃቸው ይገባል። የግል እና የማህበረሰብ ጥረት ውጤቶች ናቸው።
እያንዳንዱ አገር መሰደድ በራሱ ችግር ያልሆነበትን እነዚህን የስደተኛ ክስተቶች እንዴት መቋቋም እንዳለበት ማጤን አለበት። ችግሮቹ ባሃገራቱ ውስጥ ያለ ጦርነት፣ የፖለቲካ ስደት እና የኢኮኖሚ ኢፍትሃዊ ክፍፍል ናቸው። እነዚህ ሁሉ ምክንያቶች ወደ ስደት ያመራሉ ፥ ይህም በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ ቋሚ ክስተት፣ መደበኛ እና የተለመደ ወደ መሆን ያመራል።

ጥያቄ፦ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ በ 2005 ዓ.ም. ከላምፔዱዛ እስከ ሞሮኮ ፣ ከዛም በ 2011 ዓ.ም. በሮም በመጨረሻም አሁን ወደ ማርሴይ ፥ በድምሩ 17 የሜዲትራኒያንን ባህር የሚያዋስኑ አገሮችን የጎበኙበትን የሜዲትራኒያን ጉዞ እንዴት ይመለከቱታል?

መልስ፦ ይህ አኃዝ አስቀድሞ ጠቃሚ ነው ፥ ጥሩ መልእክትም ያስተላልፋል። ይህ ማለት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ የዚህን የሜዲትራኒያን ተፋሰስ አስፈላጊነት ተገንዝበዋል ማለት ነው ፥ ለዚህም ብጹእነታቸው በቁርጠኝነት እየሰሩ ነው። ወደ ባሪ በመሄድ ፣ አሁን ደግሞ እዚህ ወደ ማርሴይ በመምጣት እና ይህን አጠቃላይ የሜዲትራኒያን ስብሰባዎች ሂደት በመደገፍ ቁርጠኝነታቸውን እያሳዩ ነው። እዚህ ማርሴ ውስጥ መገኘታቸው የብዙ ሰዎችን ስሜት እንደሚያነቃቃ ተስፋ አደርጋለሁ።

ጥያቄ፡- በአንዳንድ የሜዲትራኒያን ባህር ዳርቻ ላይ ያሉ ክርስቲያኖች ከሌሎቹ የበለጠ የሚደረግላቸው ጥበቃ እና የሃይማኖት ነፃነትም የእነዚህ ስብሰባዎች አንኳር ጉዳይ ነው። ይህንን በሜዲትራኒያን ሃገራት ውስጥ እንዴት ጠብቆ ማቆየት ይቻላል?

መልስ፦ እኛ ካቶሊኮች የሜዲትራኒያንን ሰብአዊነት ትንሽ ክፍል ብቻ ነው የምንወክለው። በኋላ፣ ከሙስሊሞች እና ከኦርቶዶክስ ጋር ሆነን የተለያዩ ሃይማኖቶች የሚሳተፉበት የሜዲትራኒያን ስብሰባዎች እንዲደረጉ ጥሪ ማድረግ አለብን።
ይህም የሚሆነው ለካቶሊኮች ወይም ለክርስቲያኖች መብት መከበር ብቻ ሳይሆን የሁሉም ሰው የህሊና እና የእምነት ነፃነት መብት ነው። ካቶሊኮች በአንዳንድ አገሮች እንደሚሰቃዩ ሁሉ ፥ ሙስሊሞችም በሌሎች ሃገራት ይሰቃያሉ ፥ አይሁዶችም በአንዳንድ ቦታዎች የፀረ ሴማዊነት ሰለባዎች ናቸው። ሃይማኖቶች ለጋራ ጥቅም ካልተባበሩ በስተቀር የሃይማኖት ነፃነት በፍጹም ሊመጣ አይችልም።
 

22 September 2023, 21:58