ፈልግ

ብጹዕ ካርዲናል ብርሃነየሱስ ሊቀጳጳሳት ዘካቶሊካዊያን፡ የኢትዮጵያ ካቶሊክ ጳጳሳት ጉባኤ ፕረዚዳንት- ፎቶ ፋይል ብጹዕ ካርዲናል ብርሃነየሱስ ሊቀጳጳሳት ዘካቶሊካዊያን፡ የኢትዮጵያ ካቶሊክ ጳጳሳት ጉባኤ ፕረዚዳንት- ፎቶ ፋይል 

ብጹዕ ካርዲናል አቡነ ብርሃነየሱስ የኢትዮጵያን አዲስ ዓመት በማስመልከት መልዕክት አስተላለፉ

የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሊቀጳጳሳት ብፁዕ ካርዲናል አቡነ ብርሃነኢየሱስ የኢትዮጵያን 2016 ዓ.ም የዘመን መለወጫ በዓልን በማስመልከት ለመላው ምዕመናን ያስተላለፉት መልዕክት እንደሚከተለው እናቀርባለን፤

    አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

በስመ አብ ወወልድ ፤ ወመንፈስ ቅዱሰ አሐዱ አምላክ አሜን፡፡
“እንግዲህ ዘወትር ለእግዚአብሔር የምስጋናን መሥዋዕት አድርገን በእርሱ በኩል እናቅርብለት” ዕብ 13፡15
በክርስቶስ የተወደዳችሁ ብፁዓን ጳጳሳት
ክቡራን ካህናት፤
ገዳማውያንና/ ውያት
ከአገራችሁ ውጭ በተለያዩ ክፍለ ዓለማት የምትኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን፤መላው ምዕመናንና የአገራችን ሕዝቦች በሙሉ፡-
እንኳን ለ2016 ዓ.ም የዘመን መለወጫ በዓል ሁላችሁንም አደረሳችሁ በማለት በኢትዮጲያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያንና በእራሴም ስም መልካም ምኞቴን አቀርብላችኋለሁ፡፡
አዲሱን ዓመት ሁላችንም በጸጋና በምስጋና፤በትህትናና በተስፋ ብንቀበለው ወደ ማመስገን ከፍ ያደርገናል፡፡ ከእኛ በላይ ያለውንም ኃይል እንድንመለከት ይረዳናል፡፡ የእግዚአብሔር ሕዝብ የምስጋና መሥዋዕት እንደሚያቀርብ ከእግዚአብሔር ቃል እንማራለን፡፡ እንዴት ማመስገን እንደምንችል ማስተዋል ከፈለግን ወደ እግዚአብሔር ቃል ጆሮአችንን ማዘንበል እንችላለን፡፡ እንዲሁም ከእግዚአብሔር ሕዝብ ብዙ መማር ይቻላል፡፡ ሕዝቡ ባህርን ተሻግሮ ከፈርዖን ሠራዊት ባመለጠ ጊዜ የምስጋና መዝሙርን አቀረበ (ዘጸ 15):: እኛም በጥምቀት ከኃጢያትና ከሞት ላሻገረን ጌታ የምስጋና መስዋዕት እንድናቀርብ ተጠርተናል፡፡ አዲሱም ዓመት ይህንን ምስጢር ይበልጥ የምናስተውልበትና አስተውለንም ፍሬ የምናፈራበት እንዲሆንልን እመኛለሁ፡፡ ማመስገን ለኛ ለራሳችን ይጠቅመናል፡፡ ሁሉንም ነገር መቆጣጠር እንደማንችል ያስገነዝበናል፡፡ ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ “ስናመሰግን እኛ እናድጋለን” ብሎ ያስተምረናል፡፡ እግዚአብሔር ቀድሞውንም ልዑል ነው፡፡ እኛ የምንጨምርለት ነገር የለም፡፡
አዲሱን ዓመት በትሕትና ልንቀበለው ይገባል፡፡ ትህትና ወደ እውነት ይመራናል፡፡ በጎውን በጎ፤ ስሕተትን ስሕተት ብለን እንድንቀበል ያደርገናል፡፡ እግዚዘብሔርም በቃሉ ትሁታንን እንደሚወድ አሳይቶናል፡፡ የእግዚአብሔር ታላላቅ ሰዎች ትሑታን ነበሩ፡፡ ለምሳሌ የእግዚአብሔር ወዳጅ ሙሴ ትልቅ ኃላፊነት ተሰጥቶት ነበር፡፡ ሕዝቡን ከባርነት ነጻ እንዲያወጣ፤በኪዳኑ ምስክር እንዲሆን እስከ ተስፋይቱ ምድር ሕዝቡን እንዲመራ ሌሎችም ብዙ ነገሮችን እንዲያከናውን ተጠርቶ ነበር፡፡ እንዲያውም ከብዙ የእግዚአብሔር ሰዎችም በተለየ መልኩ ከእግዚአብሔር ጋር ፊት ለፊት የመነጋገር ጸጋም ተቀብሎ ነበር፡፡ “እሱም በምድር ላይ ካሉት ሰዎች ሁሉ ይልቅ እጅግ ትሁት ሰው ነበር” (ዘኅ 12፡3) ተብሎ ተጽፏል፡፡ ክርስቶስም “ሸክም የከበዳችሁ ወደ እኔ ኑ ለነፍሳችሁም እረፍትን ታገኛላችሁ” ብሎናል (ማቴ 11፡25-30) እረፍቱንም የምናገኘው በትህትና ነው፡፡ “እኔ የዋሕና ትሁት ነኝ” የሚለው የጌታ ቃል በልባችን ሲሠርጽ የነፍስና የሥጋ፤ የግልና የጋራ ሰላምን እናገኛለን፡፡ ለሚቀጥለውም ዓመት መልካም መሠረት እንጥላለን፡፡ እኛም ባለፈው ዓመት ያገኘናቸውንና ያጣናቸውን ነገሮች ለማስተዋል ትህትና ያስፈልገናል፡፡ ያለ ትህትና ኅሊናን መመርመር ያስቸግረናል፡፡ የሚቻልም አይደለም፡፡ ትህትና ጥፋታችንን እንድናይ፤አይተንም አንድናዝን፤እንድንጸጸትና ተጸጽተንም ንስሐ እንድንገባ ያስችለናል፡፡
አዲሱን ዓመት በተስፋ ስንቀበል ከወንጌል ብዙ እንድንማር ክርስቶስ ይጠራናል፡፡ አንዳንድ ጊዜ ጸሎታችንን እየሰማ ይሆን ብለን እንጠይቅ ይሆናል፡፡ ለምነን የማናገኘው ለምንድ ነው ብለን እናስብ ይሆናል፡፡ መልካም ነገር መፈለጋችን በእርግጥም ተገቢ ነው፡፡ ለመጪውም ዓመት ሰላምን፤ዕርቅን፤ ፍቅርንና በረከትን እንመኛለን፡፡ ለዚህም እንዲሁ ዘወትር እንጸልያለን፡፡ እዚህ ላይ የከነዓናዊቷን ሴት ታሪክ ማስታወስ ይጠቅማል፡፡ (ማቴ 15፡22-28) በመጀመሪያ ስናስብ ክርስቶስ ጸሎቷን መቀበል ያልፈለገ ይመስላል፡፡ በኋላ ግን የሷን ታላቅ እምነት እንደወደደው ገልጿል፡፡ እኛም እንደሷ በእምነት እንድንጸልይ ይፈልጋል፡፡ ወንጌል የሚያስተምረን እኛ ስንጸልይና ስንለምን ለጋራ ጥቅም እያሰብን ነው ወይንስ ለመንደራችንና ለአካባቢያችን ብቻ ነው? ነገር ግን ሌሎቹ ሕዝቦችስ? ስለ ሌሎች ሲነሳ ማመንታት እንጀምር ይሆን? ሌሎቹም የእግዚአብሔርን በረከት እንዲያገኙ እንመኛለን? ወይንስ ቅድሚያውን ለኛ እናስቀራለን፡፡ ክርስቶስ ለከነዓናዊቱ ሲመልስ መጀመሪያ የእሥራኤል ልጆች ይጥገቡ በማለት የሁሉም ጌታ መሆኑን የሚደብቅ ነገር ተናገረ፡፡ ይህንን ያደረገው ለሁላችንም ትምህርት እንዲሆን ብሎ ነው፡፡ እኛ ኢየሱስ እንዴት ከነዓናዊቷን ሴት ሊቆጣት ቻለ ብለን እንጠይቅ ይሆናል፡፡ ኢየሱስ እንዲህ ዓይነት ጠንካራ መልስ እንዴት ሊሰጣት ቻለ እንል ይሆናል፡፡ እንግዲያውስ ክርስቶስ ምድርና ሞላዋ የእግዚአብሔር መሆናቸውን፤የሰው ልጆችም በሙሉ የእግዚአብሔር ምህረትና ጸጋ እንደሚያስፈልጋቸው ሊያስተምረን ብሎ የከናዓናዊቷን ልመና በመጨረሻ ተቀበለ፤ ልጇንም ፈወሰላት፡፡
አዲሱ ዓመት መልካም ታሪኮችን የምንተርክበትና የምንፈጽምበት ዓመት ሊሆን ይገባል፡፡ የጥላቻ ትርክቶችም በበጎ ትርክቶች እንዲተኩ የበኩላችንን ጥረት እንድናድርግ። በእርግጥ ጊዜያችን በማስታወቂያዎች ብዛት የተጥለቀለቀበት ዘመን ነው፡፡ መምረጥ እስከሚያዳግትበት ድረስ ማስታወቂያዎች ይቀርባሉ፡፡ እንዴት መምረጥ ይቻላል? ረጋ ብሎ ለመምረጥስ ምን ያህል ጊዜ ቢኖር ነው? እንዴት ደህናውን ከማይረባው መለየት ይቻላል? ሕይወትን በሚመለከቱ ጉዳዮች ላይ መወሰን ቀላል አይደለም፡፡ መጠራጠራችን አይቀርም፡፡ የትኛው መንገድ ይሻል ይሆን? አስተማማኝ ይሆንን? ከእነዚህ ድምጾች መሀል ክፍ ብሎ የሚሰማ አንድ ፍጹም የተለየ ድምጽ አለ፡፡ ከሚቀርቡልን ግብዣዎች ወይም ጥሪዎች መሀል ምትክ የሌለው ጥሪ አለ ፡፡ “እኔ በር ነኝ፤እኔ መልካም እረኛ ነኝ” የሚል ድምጽ እንሰማለን፡፡ እጅግ አስደናቂ መልዕክት ነው፡፡ የእኛ የልጆቹን ጥማት የሚያረካው መልካም እረኛው ኢየሱስ ነው፡፡ የእርሱ ጥሪና ግብዣ በማስታወቂያዎች ከሚቀርቡልን እጅጉን ይለያል፡፡ የማስታወቂያዎቹ ዓላማ ዕቃዎችን ወይንም አመለካከታቸውን መሸጥ ነው፡፡ አመለካከታችንንም ሊያስቀይሩን ይፈልጋሉ፡፡ እግዚአብሔር ግን በዚህ ግርግር መሃል “አዳም ሆይ የታለህ? ሔዋን ሆይ የት አለሽ” ብሎ ይፈልገናል፡፡ የማስታወቂያዎቹ ተስፋዎች አያስተማምኑም፡፡ የኢየሱስ ተስፋ ግን ተስፋ ብቻ ሆኖ አይቀርም፡፡ ምክንያቱም ነፍሱን ስለ ወዳጆቹ አሳልፎ ይሰጣልና፡፡
የተወደዳችሁ ወገኖች አገራችን ያለችበት ሁኔታ እጅግ አስቸጋሪና አሳሳቢ ሆኖ እናየዋለን፡፡ ምክንያቱም አገራችን በፈጠራት ፈጣሪዋ ምንም ሳታጣና ሳይጎድላት እኛ በእግዚአብሔር አርአያና አምሳል የተፈጠርነው ምድራውያን ሰዎች እርስ በርሳችን በመገፋፋትና በመጋጨት ያለማቋረጥ መጠፋፋትንና መገዳደልን የምናስተናግድ ሆነናል፡፡ ሁሉ ባለድርሻ ኣካላት በሁሉም መስክ በአስተዋይነትና በጥበብ ነባራዊውን የጥፋት ሁኔታ ከባለፈው የስቃይ ጊዜ በመማር የሁሉንም የአገሪቱ ሕዝቦች ድምጽ በመስማት የወንድማማቾችን ግጭት በሕዝቦች ውይይት፤ በዕርቅና በሰላም ብሎም በእውነትና በመቻቻል መንፈስ ነገሮችን በማሰከንና የአብሮነትና የሰላም ጉዞ በአዲስ ዓመት እንዲመጣልን አጥብቀን እንመኛለን። ዜጎች በሰላምና በደስታ በልማትና በሥራ እንዲተጉና እንዲሳተፉ ታዳጊዎች ልጆቻችንም በተስፋና በፍቅር የሚያድጉባት አገር እንድትኖረን መልካም መሠረት ለመጣል እንድንተጋ ሁሉንም በአጽንዖት እንጠይቃለን፡፡
ይህንን አዲስ አመት ስንጀምር የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን በሲኖዶሳዊ መንፈስ ያዘጋጀችው ከመስከረም 2016 ዓ.ም. እስከ ነሃሴ 2025 ዓ.ም. ለቀጣይ አስርት አመታት የሚቆየው ሐዋርያዊ ዕቅድ ዝግጅት ተጠናቋል። ይህ አዲስ ሐዋርያዊ አቅጣጫ የመተለም ዕቅድ ፍፅምና አግኝቶ ከብዙ ምክክር እና ውይይት በኋላ ተዘጋጅቶ ቀርቦልናል።የሐዋርያዊ እቅዱ ካቶሊካዊ መንፈሳዊነትን የሚያነቃቃ፣ የቤተክርስቲያን አባላትን የሚጠናክር፣ ምዕመናንን እና ካህናትን በእውነተኛ የሀይማኖት ትምህርት ታንጸው አዳዲስ ምዕመናንን ማፍራት የሚያስችል፣ የቤተክርስቲያን አቅምን የሚገነባ በአጠቃላይ ሁላችንንም በመንፈሳዊ ዕድገት ወደ እግዚአብሔር የሚያቀርበን እንደሆነ እናምናለን። ስለሆነም ለዚህ እቅድ ተግባራዊነት እና መሳካት ሁላችንም በፀሎት እንድንበረታ እንዲሁም ብጹዓን ጳጳሳት፣ ካህናት፣ ደናግል እና ምዕመናን ሁሉ በአብሮነት በተሳትፎ በባለቤትነት ሥሜት የየራሳችንን ጥረት እንድናደርግ ቤትክርስቲያን ጥሪዋን ታቀርባለች።
እንደሚታወቀው ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን በአለም አቀፍ ደረጃ አብሮ የመጓዝ ሲኖድ በህብረት በተሳትፎ እና ተልዕኮ መንፈስ በማድረግ ላይ ትገኛለች። ይህም ሲኖድ መርሃግብር አካል የፊታችን ጥቅምት ወር በጣልያን ሮም የምክክር መድረክ ይካሄዳል። በዚህም ጉባኤ ከኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን እኔ እና ብጹዕ አቡነ ማርቆስ እንገኛለን። ስለሆነም ምዕመናን ለዚህ ጉባኤ መሳካት በጸሎት እንድትተጉ ለማሳሰብ እወዳለው።
በመጨረሻም ይህንን የዘመን መለወጫ በዓልን ስናከብር ሁላችንም ክርስቲያኖችና ምዕመናን በችግርና በመከራ እንደዚሁም በጦርነትና በተለያዩ ምክንያቶች ተፈናቅለው ለሚገኙ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን በአጠቃላይ እገዛ ለሚያስፈልጋቸው ሁሉ አቅማችን በሚፈቅድልን መጠን በመርዳትና በመለገስ አዲሱን ዓመት በጸጋ እንቀበለው፡፡ አዲሱ ዓመት የታመሙት የሚድኑበት፤የታሠሩ የሚፈቱበት፤ ጦርነት የሚጠፋበት፤ በችግር ላይ ያሉ ከችግር የሚወጡበት፤ሕዝቦች የሚታረቁበትና አብረው የሚሠሩበት ይሁንልን፡፡
አዲሱ ዓመት የሰላምና የፍቅር ዘመን ለሁላችንም እንዲሆንልን እመኛለሁ፡፡
እግዚአብሔር ሕዝባችንና አገራችንን ይባርክልን፡ አሜን፡፡


                +ብጹዕ ካርዲናል አቡነ ብርሃነኢየሱስ
                   ሊቀ ጳጳሳት ዘካቶሊካውያን
                   የኢትዮጲያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያ ጳጳሳት ጉባኤ ፕረዜዳንት

 

11 September 2023, 10:08