ፈልግ

የቅዱስ ሲኖዶስ ጠቅላላ ጉባኤ የቅዱስ ሲኖዶስ ጠቅላላ ጉባኤ  

ወንድም ማቲው፥ የክርስቲያኖች የኅብረት ጸሎት የተስፋ እና የአንድነት እንደሆነ ገለጹ

በፈረንሳይ የሚገኝ የታይዜ ማኅበረሰብ አስተባባሪ የሆኑት ወንድም ማቲው፥ ከሲኖዶስ ጠቅላላ ጉባኤ አንድ ቀን አስቀድሞ የሚካሄደው የአብያተ ክርስቲያናት የኅብረት ጸሎት የተስፋ እና የአንድነት ጸሎት እንደሆነ ገለጸው፥ የጋራ ጸሎት አስፈላጊነትን በማብራራት ባደረጉት ንግግር፥ የሲኖዶሱን ሥራ ለመንፈስ ቅዱስ መሪነት በአደራ መስጠት እንደሚያስፈልግ አደራ ብለዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የታይዜ ማኅበረሰብ መሪነትን በቅርቡ የሚረከቡት ወንድም ማቲው፥ ቅዳሜ መስከረም 19/2016 ዓ. ም. የሚፈጸመውን ታላቅ የዋዜማ ጸሎት ሥነ-ሥርዓት በማስመልከት ዓርብ ጳጉሜ 3/2015 ዓ. ም. መግለጫ ሰጥተዋል።

የጸሎት ሥነ-ሥርዓቱ ከሲኖዶሱ ጠቅላላ ጉባኤ አንድ ቀን አስቀድሞ ማለትም መስከረም 19/2016 ዓ. ም.  የሚካሄድ ሲሆን፥ በአንድነት አውድ ውስጥ የሚካሔድ ሥነ-ሥርዓቱ፥ በርካታ ወጣቶችን በሮም ለማሰባሰብ የተዘጋጀ የክርስቲያኖች አንድነት የጸሎት ዝግጅት መሆኑን አስረድተዋል።

ከቫቲካን የዜና አገልግሎት ጋር ቃለ ምልልስ ያደረጉት ወንድም ማቲው፥ በዋዜማው ዕለት ቅዳሜ መስከረም 19/2016 ዓ. ም. የሚፈጸመውን የጸሎት ሥነ-ሥርዓት ትርጉም በማስመልከት ባካፈሉት ሃሳብ፥ የአብያተ ክርስቲያናት የጸሎት ምሥክርነት የሲኖዶሱ ጠቅላላ ጉባኤ መጀመሪያ መሆኑን ገልጸው፥ ስለ ዓለም አቀፋዊ ምሥክርነት ያለውንም ፋይዳ አስረድተዋል። “የጸሎት ዝግጅቱ የሲኖዶሱ ጠቅላላ ጉባኤው መክፈቻ ሳይሆን የሲኖዶሱ ጉባኤ ጅምር መሆኑን መለየት አስፈላጊ ነው” በማለት ወንድም ማቲው ተናግረዋል።

የእግዚአብሔርን ሕዝቦች ስብሰባ

የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የጸሎት ግብዣ ለሁሉም ቤተ እምነቶች እንደሚደርስ የተናገሩት ወንድም ማቲው፥ ይህም በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚሆነውን በጸሎት ለመደገፍ መላውን የእግዚአብሔር ሕዝቦች የሚሰበስብ በመሆኑ፥ ከታይዜ ማኅበረሰብ ዓላማ ጋር የሚስማማ መሆኑን አስረድተዋል።

"በእርግጥ መላውን የእግዚአብሔር ሕዝብ በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ልናገኝ አንችልም" ያሉት ወንድም ማቲው፥ "ነገር ግን በክርስትናው ዓለም ውስጥ የተለያየ የሕይወት ጎዳናን የሚወክሉ ሰዎች ይገኛሉ" ብለው፥ ተስፋቸውም በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ከሚደረግ የዋዜማው ጸሎት ምስክርነት በላይ መሆኑን ተናግረዋል።

“በዚህ የዋዜማ ጸሎት ሥነ-ሥርዓት ውስጥ የወንጌል ልኡክነትን የሚገልጽ ምልክት አለ” ያሉት ወንድም ማቲው፥ በጸሎት ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የሚሳተፉ ሰዎች አስተዋፅዖቸውን እንዲያበረክቱ ለመጋበዝ የሚመጡባቸውን አካባቢዎች ማወቅ አስፈላጊ እንደሆነ ተናግረዋል።

ዓለም አቀፍ ተደራሽነት

የሲኖዶሱ ጠቅላላ ጉባኤ የዋዜማ ጸሎት ተደራሽነት ከሮም ውጭ ወደ ልዩ ልዩ አገራት እንደሚደርስ የተነገረ ሲሆን፥ የጸሎት ሥነ-ሥርዓቱን በዓለም ዙሪያ በበሚገኙ በርካታ አገራት ዘንድ ለመፈጸም የታቀደ፥ ዓለም አቀፋዊ ምላሹ በሲኖዶሱ አንድነት እና ጸሎት ላይ ለመሳተፍ የጋራ ቁርጠኝነትን ያሳየ መሆኑ ተገልጿል።

"አውስትራሊያ ውስጥ በሚገኙ ግዛቶች በሙሉ፥ በኬንያ፣ በኡጋንዳ፣ በጃፓን፣ በታይላንድ፣ በዩናይትድ ስቴትስ፣ በካናዳ፣ በቺሊ፣ አርጀንቲና፣ ስማቸውን መጥራት በሚያዳግቷቸው የላቲን አሜሪካ እና መካከለኛው አሜሪካ አገራት በተለያዩ ቦታዎች የጸሎት ሥነ-ሥርዓቶች መኖራቸውን ወንድም ማቲው ገልጸዋል።

ወንድም ማቲው በማጠቃለያ ንግግራቸው፥ ለዚሁ ሥነ-ሥርዓት በተዘጋጀው እና “together2023.net/it” ከተሰኘው ድረ-ገጽ ላይ መረጃ ማግኘት እንደሚቻል ገልጸው፥ የዕለቱ ዝግጅቶች በሙሉ በቫቲካን የዜና ማሰራጫዎች በኩል በቀጥታ ስርጭት የሚተላለፉ መሆኑን ተናግረው፥ በአሁኑ ወቅት በቤተ ክርስቲያን እየተካሄደ ያለውን ተግባር ለመንፈስ ቅዱስ በአደራ በመስጠት ምዕመናን በዚህ አስደናቂ ሥራ ላይ እንዲተባበሩ አሳስበዋል።

 

 

09 September 2023, 16:32