ፈልግ

ብጹዕ ካርዲናል ኦማሌይ ከአባ ጆርዲ ፑጆል ጋር ሆነው መጽሐፉን ለንባብ ሲያቀርቡት ብጹዕ ካርዲናል ኦማሌይ ከአባ ጆርዲ ፑጆል ጋር ሆነው መጽሐፉን ለንባብ ሲያቀርቡት  

“የቤተ ክርስቲያን ውስጥ ምስጢር እና ግልጽነት” በሚል ርዕሥ የታተመ መጽሐፍ ይፋ ሆነ

በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ግልፅነት መኖር በተለይም በደል ሲፈጸም ቤተ ክርስቲያን አስተዋይ መሆን እንደሚገባ የቤተ ክርስቲያን ውስጥ ምስጢር እና ግልጽነት በሚል አርዕስት መጽሐፍ ያሳተሙት ሁለት የቤተ ክርስቲያን አባቶች ገልጸው፥ ያልተገደበ ግልጽነት ቤተ ክርስቲያንን ሊጎዳ እንደሚችል ተናግረው ነገር ግን ይህ የተለመደውን የምስጢራዊነት መርህን እንደማይመለከተው አስረድተዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በተለይ ሕጻናት ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶችን ጨምሮ ሁሉንም ዓይነት በደል ለመከላከል የሚያግዝ ግልጽነት በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ቦታ አለ ወይ? በማለት የማኅበራዊ መገናኛ እና የሕገ ቀኖና  ባለሙያ የሆኑት አባ ጆርዲ ፑጆል እና አባ ሮላንዶ ሞንቴስ ደ ኦካ፥ ለቀረበው ጥያቄ መልሶችን ለመስጠት የሚፈልግ መጽሐፍ በጋራ ጽፈዋል።

"ግልጽነት እና ምስጢራዊነት በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን" በሚል ርዕስ የተጻፈው መጽሐፍ የታተመው በላቲን አሜሪካ ለአካለ መጠን ያልደረሱ ልጆች ጥበቃ እና ጥናት ምክር ቤት ሲሆን፥ ለንባብ የበቃውም በሮም ቅዳሜ መስከረም 12/2016 ዓ. ም. ብጹዕ ካርዲናል ሾን ኦማሌይ በተገኙበት ሥነ-ሥርዓት ነው።

ለአካለ መጠን ያልደረሱ ሕፃናት ጥበቃ ጳጳሳዊ ኮሚሽን ፕሬዝዳንት ብጹዕ ካርዲናል ኦማሌይ የሰሐፊዎችን ሥራ በአዎንታ ተቀብለውት፣ ለአካለ መጠን ባልደረሱ ሕፃናት ላይ የሚደርስ ጥቃት ለመከላከል ግልጽ ንግግር እና ሕጋዊነት ጎን ለጎን የመሥራት አስፈላጊነት መኖሩን ገልጸዋል። “ግልጽ የማንሆን ከሆነ በሕዝባችን ዘንድ አመኔታ አይኖረንም” ያሉት ብጹዕ ካርዲናል ኦማሌይ፥ አለበለዚያ በቤተ ክርስቲያናችን እና በማኅበረሰባችን ውስጥ ያለውን አስከፊ የወሲባዊ ጥቃት ችግር በትክክል መቋቋም አንችልም” ሲሉ አሳስበዋል።

ግልጽነትን እና ምስጢራዊነትን አላግባብ መጠቀም

ቤተ ክርስቲያን ግልፅነትን ለማሳደግ ያላትን ፍላጎት በእጅጉ ያደነቁት ደራሲዎቹ፥ ነገር ግን የግል ሕይወትን ከመጠን በላይ ካጋለጡ በተጎጂዎች ላይ ሊደርስ የሚችል ጉዳት እንዳለም አስጠንቅቀዋል። ከተከሳሹ አንፃር ያልተገደበ ግልጽነት፥ ጥቃት ከማድረስ ንፁህ የመሆን መርህን ሊጎዳ እንደሚችል አስረድተዋል።

አባ ጆርዲ እና አባ ሮላንዶ፥ በግፍ የተጠቁ ሰዎች እውነት እና ፍትህ የሚያደናቅፍ የቤተ ክርስቲያን ምስጢራዊነትን ተችተው፥ ጥቃቱን ይፋ በማውጣት አኳያ ምስጢራዊነት ትክክለኛ ተግባር ሊሆን እንደማይችል ያረጋገጡት የመጽሐፉ ደራሲዎች፥ ምስጢራዊነትን በትክክል መጠቀም መልካም ስም እና ግላዊነትን የማግኘት መብትን የሚጠብቅ መሆኑን ገልጸው፥ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚፈጸሙ በደሎችን በተመለከተ ግልጽነትን ወይም ምስጢራዊነትን የመጠበቅ ሚዛን ምን ያህል ስስ እንደሆነ መገንዘብ እንደሚገባ አሳስበዋል። “በሁለቱም በኩል ግፍ አለ” ያሉት አባ ጆርዲ በበኩላቸው፥ ምስጢራዊነትን እና ግልጽነትን ያለአግባብ በመጠቀም ሁለቱንም በሚያስቀይም መንገድ ለማሳየት በሚፈልጉት ሰዎች ዘንድ ስሕተት እንደሚፈጸም አስረድተዋል።

ለጥቃት ተጋላጭ የሆኑ ሰዎችን በተለይም ለአካለ መጠን ያልደረሱ ሕጻናትን ከጉዳት ለመጠበቅ የሚያግዙ መረጃን በተመለከተ ጥንቃቄ የተሞላበት ፍርድ መስጠት እንደሚገባ ያሳሰቡት አባ ጆርዲ፥ መረጃው የሚደርሰው ክፍል ጥቃት የሚፈጸምበትን ግለሰብ ማዕከል እንዲያደርግ አሳስበው፥ የመነሻ ነጥቡ የመረጃ ግልጽነት መሆን እንዳለበት ተናግረዋል። ይህን በማድረግ በሌሎች የተለያዩ ጉዳዮች ላይ ልዩ ጥበቃን በማድረግ የሰለባዎችን ምስጢር መጠበቅ እንደሚቻል አባ ጆርዲ አስረድተዋል።

እንደ መሠረታዊ መሣሪያነት የሚያገለግል መጽሐፍ ነው

“የቤተ ክርስቲያን ውስጥ ምስጢር እና ግልጽነት” በሚል ርዕሥ የታተመው መጽሐፉ፥ በሰዎች ላይ በደል ሲደርስ ለማሰላሰል እና ለመነጋገር አጋዥ ሆኖ የሚያገለግሉ ተግባራዊ ገጽታዎች ያሉት ሲሆን፥ ይህም ለብጹዓን ጳጳሳት ብቻ ሳይሆን የሀገረ ስብከቱን ማኅበራዊ መገናኛ ጽሕፈት ቤት ለሚመሩት፣ ለገዳማውያን እና ገዳማውያት፣ ለትምህርት ቤቶች እና ማንኛውንም የቤተ ክርስቲያን መገናኛዎችን ለሚመሩት በሙሉ እንደ መሣሪያነት የሚያገለግል እንደሆነ ታውቋል።

በአባ ጆርዲ ፑጆል እና በአባ ሮላንዶ ሞንቴስ ደ ኦካ ተባባሪነት የተጻፈው ይህ መጽሐፍ፥ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚደርስ በደልን ሁለንተናዊ በሆነ መንገድ የሚዳስስ፣ ስነ ልቦናዊ፣ ቀኖናዊ፣ ህጋዊ፣ ሐዋርያዊ፣ ስልጠናዊ ገጽታዎችን እና ሌሎች ምንጮችን ጨምሮ በላቲን አሜሪካ ለአካለ መጠን ያልደረሱ ልጆች ጥበቃ እና ጥናት ምክር ቤት የሚያወጣቸውን ጽሑፎች የካተተ እንደሆነ ታውቋል።

 

 

 

 

28 September 2023, 18:17