ፈልግ

የኡልማ ቤተሰብ አባላት - የፋይል ፎቶ የኡልማ ቤተሰብ አባላት - የፋይል ፎቶ 

ሊቀ ጳጳስ ጌዴኪ የኡልማ ቤተሰብ 'አይሁዶችን ያዳኑ የፖላንድ ህዝቦች ምልክት' ናቸው አሉ።

የፖላንድ ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዝዳንት የሆኑት ሊቀ ጳጳስ ስታኒስላው ጋዴኪ እንደተናገሩት መጪው እሁድ የቅድስና ክብር የሚሰጣቸው የኡልማ ቤተሰብ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት አይሁዶችን የታደጉትን የፖላንድ ሰዎች ጀግንነት አጉልቶ ያሳያል አሉ።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

የኡልማ ቤተሰብ ጳጉሜ 5 2015 ዓ.ም. የቅድስና ማእረግ ሊሰጣቸው የታቀደ ሲሆን ፥ እንደ ሊቀ ጳጳስ ስታኒስላው ገዴኪ አባባል "በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት አይሁዶችን ያዳኑ የፖላንድ ህዝቦች ምልክት" ናቸው ብለዋል።
የፖላንድ ጳጳሳት ጉባኤ ሊቀ መንበር ከቫቲካን ዜን ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ መጭው እሁድ የሚካሄደው ሥርዓተ ቅድስና የካቶሊክ ቤተክርስቲያን እና የአይሁድን ግንኙነት እንዴት እንደሚያጠናክር ሀሳባቸውን ሰጥተዋል።
ሊቀ ጳጳስ ጌዴኪ እንደተናገሩት የኡልማ ቤተሰብ አይሁዶችን ከናዚዎች ጥቃት በማስጠለላቸው ምክንያት በናዚ ጀርመኖች እ.አ.አ. መጋቢት 24, 1944 የሞት ቅጣት እንደተፈፀመባቸው ገልፀው ፥ በዚህም ቅጣት በአንድ ጊዜ ሁለት ወላጆች እና ሰባት ልጆች ተገድለዋል" ብለዋል። ጳጳሱ በማከል "ይህ ድርጊት አሳዛኝ ክስተት ቢሆንም ፥ አሁን ለቤተሰቡ የሚሰጠው የቅድስና ማዕረግ በቤተክርስቲያኗ ታሪክ ታይቶ የማይታወቅ ነው ፥ ምክንያቱም መላው ቤተሰብ በአንድ ላይ ይህ ክብር ሲሰጠው የመጀመሪያው ስለሆነ” ብለዋል።

ያልተገደበ አብሮነት

ከሁለት ቀን በኋላ ለኡልማዎች የሚሰጠው ማዕረግ አስፈላጊነት ያብራሩት ሊቀ ጳጳስ ጌዴኪ ፥ የራሳችንን ህይወት ለአደጋ በሚያጋልጥበት ተግባር ውስጥ እየተሳተፍን መሆኑን እያወቅን ቢሆንም እንኳን ሌሎችን ለመርዳት ያለንን ፍላጎት በማጉላት የሰው ልጆችን የአንድነት እና የአብሮነት መንፈስን እንደሚያስታውሰን አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።
የፖላንድ ጳጳሳት ፕሬዝደንቱ ኡልማዎች አይሁዶችን በመደበቃቸው ሊደርስባቸው የሚችለውን አደጋ ያውቁ እንደነበር ጠቁመዋል።
ሊቀ ጳጳስ ጌዴኪ እንዳሉት "ይህ ቤተሰብ ከመንደሩ የተወሰነ ርቀት ላይ ቢኖሩም ብዙ ሰዎችን በቤታቸው ሰገነት ላይ በማስጠለል እራሳቸውን ጀርመኖቹ ሊወስዱባቸው በሚችሉት ከፍተኛ አደጋ ውስጥ እንደጣሉ ተገንዝበው ሊሆን ይችላል ፥ የኡልማ ልጆች በዚያን ወቅት ስለሁኔታው ሙሉ በሙሉ ግንዛቤው ስላልነበራቸው በአጋጣሚ ስላስጠለሏቸው አይሁዶች ለሰዎች ይነግሩ ይሆናል። ወይ ደግሞ በመደብራቸው ውስጥ ብዙ ሰዎች ግብይት ያደርጉ ስለነበረም የአከባቢው ሰዎችን ትኩረት ስቦም ሊሆን ይችላል” በማለት አይሁዶቹ የተያዙበትን አጋጣሚ ያላቸውን ግምት ተናግረዋል።
በወቅቱ ሌሎች ቤተሰቦችም ድጋፍ ማድረጋቸውን ጠቁመው ፥ በመንደሩ 21 ሰዎች በሕይወት መትረፋቸው የህብረተሰቡን አጋርነት አሳይቷል ብለዋል።
ሊቀ ጳጳስ ጌዴኪ እንደተናገሩት የኡልማዎች ድርጊት በፖላንድ ባህል ውስጥ ሥር የሰደደ የካቶሊክ እምነት ክርስቲያናዊ ፍቅር እና አስተዳደግ ነው ካሉ በኋላ አክለውም "ድርጊታቸው ለእያንዳንዱ ህይወት ከፅንሰ-ሀሳብ እስከ ተፈጥሯዊ ሞት ያላቸውን ክብር ያረጋግጣል ፥ እያንዳንዱ ህይወት ጥበቃ ሊደረግለት እንደሚገባ ያውቁ ነበር ፥ ለዚህም የመጨረሻውን መስዋዕትነት ከፍለዋል” ብለዋል።

ለአደጋ የተጋረጠ ጀግንነት

የኡልማ ቤተሰብ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት አይሁዶችን ያዳኑትን የፖላንድ ህዝቦችን ተምሳሌነት ያመለክታሉ ፥ ምንም እንኳን ወደ 1,000 የሚጠጉ ፖላንዶች ይህን በማድረጋቸው የተገደሉ ቢሆንም ሕይወታቸውን አደጋ ላይ ጥለው ሌሎችን ለመርዳት ያላቸውን ጀግንነትም አስምረውበታል።
ሊቀ ጳጳስ ጌዴኪ “በፖላንድ ያለው ሁኔታ ከሌሎች አገሮች ጋር ሊወዳደር የማይችል ነበር” ካሉ በኋላ “ፖላንዳውያን አይሁዶችን በመርዳታቸው የሞት ፍርድ ተፈርዶባቸዋል። በግልጽ የታወቁ አስተሳሰቦች እና አስከፊ ድርጊቶችም ነበሩ ፥ ይሁን እንጂ እነዚህ ድርጊቶች ሌሎችን ለመርዳት ሕይወታቸውን ለአደጋ ያጋለጡትን ጀግንነት ሊጋርዱ አይችሉም። ዞሮ ዞሮ የህብረተሰቡ መለኪያ አንዳንድ ወንጀለኞች የሚያደርጉት ድርጊት ሳይሆን የተከበሩ ሰዎች ተግባር ነው” በማለት አብራርተዋል።
ሊቀ ጳጳስ ጌዴኪ የኡልማ ቤተሰብ ጳጉሜ 5 የሚደረግለት የቅድስና ሥነ ስርዓት የካቶሊክ እና የአይሁድ ግንኙነትን ለማጠናከር እንዲሁም በፖላንድ እና በአይሁድ ህዝቦች መካከል ያለውን ትስስር ለማጠናከር አስተዋፅኦ እንዳለው አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።
"እነዚህ ነገሮች ለቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ወሳኝ ጉዳዮች ነበሩ። ቅዱስነታቸው ያደጉት እና የተማሩት አይሁዳውያን ልጆች በሚማሩበት ትምህርት ቤት ውስጥ ነው። በተጨማሪም በኋለኞቹ ዓመታት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ከሆኑም በኋላ ከብዙዎቹ ጋር ተገናኝተው ነበር ፥ ብዙ አይሁዳውያን ወዳጆችም ነበሯቸው ፥ በዚህም የካቶሊክ እና የአይሁድ የጋራ ውይይት ፍሬዎችንም አይተናል” በማለት ሃሳባቸውን አጠቃለዋል።
 

08 September 2023, 13:27