ፈልግ

ፍቅር በቤተስብ ውስጥ፤ ፍቅር በቤተስብ ውስጥ፤   (Vatican Media)

ፍቅር በቤተስብ ውስጥ፤ ቤተሰብ በቤተ ክርስቲያን ሰነዶች

ሁለተኛው የቫቲካን ጉባኤ፥ “ጋውድዩም ኤት ስፔስ” በተሰኘው ሐዋርያዊ ሠነዱ ውስጥ፥ “የጋብቻንና የቤተሰብን ክብር የመጠበቅ አንገብጋቢነት አሳይቶአል።” (ቁ. 47-52) ሕጉ “ጋብቻ የሕይወትና የፍቅር ሱታፌ ነው ይላል። (ቁ. 48) ፍቅርንም የቤተሰብ ማእከል አድርጎ ያስቀምጣል… “በባልና ሚስት መካከል ያለ እውነተኛ ፍቅር” (ቁ. 49) እርስ በርስ መሰጣጣትን ያካትታል። በእግዚአብሔር ዕቅድ መሠረት ወሲባዊና ስሜታዊ ገጽታዎችን ይይዛል፣ ያጣምራል። (ቁ. 48-49) ከዚህ ሌላ የጉባኤው ሠነድ “ባልና ሚስት በክርስቶስ ላይ የተመሠረቱ እንደ ሆኑ” በአጽንኦት ያስገነዝባል። “ጌታ ክርስቶስ ራሱን ለክርስቲያን ባልና ሚስት በምሥጢረ ተክሊል ይሰጣል” (ቁ. 48)፣ ከእነርሱም ጋር ይኖራል፡፡ በምሥጢረ ሥጋዌ፣ የሰብአዊ ፍቅርን መልክ ያዘ፣ እርሱንም ፍጹም አድርጎ ወደ ፍጽምና ያደርሰዋል፡፡ በመንፈሱ ለባልና ሚስት በዚያ ፍቅር መሠረት የሚኖሩበትን ችሎታ ይሰጣቸዋል፣ ይህም ፍቅር የእምነት ሕይወታቸውን፣ ተስፋቸውንና ልግስናቸውን ሁሉ ይሞላል፡፡ በዚህ መንገድ፣ ባልና ሚስት ይቀደሳሉ፣ በልዩ ጸጋም አማካይነት የክርስቶስን አካል ይገነባሉ፤ የቤተሰብ ቤተክርስቲያን ይመሠርታሉ። (ሉመን ጀንትዩም ሐዋርያዊ ሠነድ ቁ. 11) ቤተ ክርስቲያንም የራስዋን ምሥጢር በሚገባ ለመረዳት፣ እርስዋን በተጨባጭ ወደሚገልጸው ወደ ቤተሰብ ትመለከታለች

የቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ጳውሎስ 6ኛ፥ በሁለተኛው የቫቲካን ጉባኤ መባቻ ላይ ስለ ጋብቻና ቤተሰብ ያለውን የቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ በይበልጥ አዳብረዋል፡፡ በተለየ መንገድ፣ ሁማኔ ቪቴ በተሰኘው ጳጳሳዊ መልእክታቸው፣ በጋብቻ ፍቅርና በተዋልዶ መካከል ያለውን የተፈጥሮ ትስስር ይፋ አድርገዋል፡፡ ‹የጋብቻ ፍቅር ባልና ሚስት የወላጅነት ኃላፊነታቸውን በተመለከተ ያለባቸውን ግዴታ በሚገባ እንዲያውቁ ይጠይቃል፣ ይህ የወላጅነት ግዴታ ባሁኑ ጊዜ፣ ተገቢ ትኩረት የተሰጠውና በትክክልም ሊረዱት የሚገባ ነው። “…ኃላፊነት የሚሰማው ወላጅነት ባልና ሚስት፣ የቅድሚያ ሥርዓትን በመከተል፣ ለእግዚአብሔር፣ ለራሳቸው፣ ለቤተሰቦቻቸውና ለህብረተሰብ ያላቸውን የራሳቸውን ግዴታ እንዲገነዘቡ ይፈልጋል” (ቁ. 10)።  ር. ሊ. ጳ. ቅዱስ ጳውሎስ 6ኛ “ኤቫንጄሊ ኑንሲያንዲ” በተሰኘው ሐዋርያዊ የማበረታቻ መልዕክታቸው ውስጥ፣ በቤተሰብና በቤተክርስቲያን መካከል ያለውን ግንኙነት አስረድተዋል። ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ስለ ሰብአዊ ፍቅር በሰጡት ትምህርት፣ “ግራቲሲማም ሳኔ” በሚል ርእስ ለቤተ ሰቦች በጻፉት መልእክትና በተለይም “ፋሚሊያሪስ ኮንሶርሲዮ” በተሰኘው ሐዋርያዊ ማበረታቻቸው ውስጥ ስለ ቤተሰብ ልዩ ትኩረት ሰጥተዋል። በእነዚህ ሠነዶች ውስጥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ቤተሰብን “የቤተክርስቲያን መንገድ” ብለውታል። እንደዚሁም፣ ወንዶችና ሴቶች ስላላቸው የፍቅር ጥሪ አጠቃላይ አስተያየት የሰጡ ሲሆን፣ ለቤተሰብ ስለሚለገስ ሐዋርያዊ እንክብካቤና ቤተሰብ በኅብረተሰብ ውስጥ ስላለው ሚና መሠረታዊ መመሪያዎችን አቅርበዋል። በተለይ የጋብቻ ፍቅርን በተመለከተ (ንጽ. ቁ. 13)፣ ባልና ሚስት በጋራ ፍቅራቸው ውስጥ የክርስቶስን የመንፈስ ስጦታ እንዴት እንደሚቀበሉና የጽድቅ ጥሪያቸውን እንዴት እንደሚኖሩ አብራርተዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት በነዲክቶስ 16ኛ “ዴውስ ካሪታስ ኤስት” በተሰኘው ሐዋርያዊ መልዕክታቸው፣ በተሰቀለው በክርስቶስ ፍቅር ብቻ ሙሉ በሙሉ ሊስተዋል ወደሚችለውና በባልና ሚስት መካከል ወዳለው የፍቅር እውነታ ርዕሠ ጉዳይ ተመልሰዋል። (ንጽ.ቁ. 2) በዚህ መልዕክታቸው ውስጥ በአጽንኦት እንደገለጹት፥ “በልዩና ወሳኝ ፍቅር ላይ የተመሠረተ ጋብቻ በእግዚአብሔርና በሕዝቡ እንዲሁም በሕዝቡና በእግዚአብሔር መካከል ላለው ግንኙነት ምሳሌ ይሆናል፡፡ እግዚአብሔር በሚወደው መንገድ ለሰብአዊ ፍቅር መለኪያ ይሆናል”። (11) ከዚህ በተጨማሪ፥ “ካሪታስ ኤን ቬሪታቴ” በሚለው ሐዋርያዊ መልዕክታቸው የጋራ ጥቅምን ተግባራዊ በምናደርግበት ኅብረተሰብ ውስጥ  ፍቅርን  የሕይወት መርህ የማድረግን አስፈላጊነት አስረድተዋል።

ምንጭ፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ፥ ፍቅር በቤተሰብ ውስጥ በሚል ርዕሥ ለጳጳሳት፣ ለካህናትና ለዲያቆናት፣ ለመነኮሳት፣ ለክርስቲያን ባለ ትዳሮች እና ለምእመናን በሙሉ ያስተላለፉት የድኅረ ሲኖዶስ ሐዋርያዊ ምክር፥ ከአንቀጽ 65-68 ላይ የተወሰደ።

አዘጋጅ እና አቅራቢ ባራና በርግኔ

30 September 2023, 17:26