ፈልግ

ፍቅር በቤተስብ ውስጥ፤ ፍቅር በቤተስብ ውስጥ፤  (Vatican Media)

ፍቅር በቤተስብ ውስጥ፥ አንዳንድ ተግዳሮቶች

ለሁለቱ ቅድመ ሲኖዶስ ምክክሮች የተሰጡ ምላሾች ስለ በርካታ ልዩ ልዩ ሁኔታዎችና እነርሱም ስለሚያስከትሉአቸው አዳዲስ ተግዳሮቶች ተናግረዋል። እስካሁን ከተገለጹት በተጨማሪ ብዙዎቹ መላሾች ቤተሰቦች ሕጻናትን በማሳደግ ረገድ ስለሚገጥሙአቸው ችግሮች ጠቅሰዋል። በአብዛኞቹ ሁኔታዎች ወላጆች ደክሞአቸው ከሥራ ሲመለሱ ከማንም ጋር መነጋገር አይፈልጉም፤ ብዙዎቹ ቤተሰቦች እንዲያውም በጋራ ማእድ አይሳተፉም። ቴሌቪዥን ጨምሮ ሐሳብን የሚሰርቁ ብዙ ነገሮች ሞልተዋል። ይህም ወላጆች እምነትን ለልጆቻቸው ማስተላለፍ ይበልጥ ከባድ እንዲሆንባቸው ያደርጋል። ሌሎች መላሾች ደግሞ ቤተሰቦች በሚኖሩበት ኑሮ በመደሰት ፋንታ በመጪው ጊዜ ላይ እንደሚጠመዱና ጭንቀት ውስጥ እንደሚገቡ አመልክተዋል። ይህም ስለ ቋሚ ሥራ፣ ስለ ገንዘብና ስለ ልጆች የወደፊት ዕድል በመጨነቅ እየተባባሰ የሚሄድ ሰፊ ባህላዊ ችግር ነው።

አደንዛዥ ዕጽ መጠቀምም ከዘመናችን መቅሰፍቶች መካከል አንዱና በብዙ ቤተሰቦች ላይ እስከ ቤተሰብ መፍረስ ድረስ ከባድ ሥቃይ የሚያስከትል መሆኑ ተጠቅሶአል። የአልኮል ሱሰኝነት፣ ቁማርና ሌሎች ሱሶችም እንዲሁ። ቤተሰብ እነዚህ ሁሉ የሚከለከሉበትና የሚወገዱበት ሥፍራ ቢሆንም፥ ኅብረተሰብና ፖለቲከኞች ግን ሥጋት ያለባቸው ቤተሰቦች “አባሎቻቸውን መርዳት እንደማይችሉ አይረዱትም…፤ የዚህ ክስተት አሳዛኝ ውጤት የቤተሰቦች መፍረስ፣ የልጆች መበተንና የአረጋውያን ረዳት አልባ መሆን የሕጻናት የሕያዋን ወላጆች እጓለ ማውታን መሆን፣ የወጣቶችና የጎልማሶች መደናገርና ደጋፊ ማጣት መሆኑን እናያለን።” የሜክሲኮ ብጹዓን ጳጳሳት እንዳመለከቱት፥ በቤተሰቦች ውስጥ የሚፈጠር ብጥብጥ አዲስ የጥቃት ዓይነቶችን ያራባል፤ ምክንያቱም “የቤተሰብ ግንኙነቶች ነውጠኛ ስብዕናንም ይገልጻሉና። ይህም የሚሆነው ብዙውን ጊዜ ተግባቦት በሌለባቸው፣ ራስን የመከላከል አስተሳሰብ በሚበረታባቸው፣ አባላት እርስ በርስ በማይረዳዱባቸው፣ ተሳትፎን የሚያበረታቱ የቤተሰብ ተግባራት በጠፉባቸው፣ የልጆችና የወላጆች ግንኙነት አብዛኛውን ጊዜ የግጭትና የብጥብጥ ሥፍራ በሆነባቸው፣ እንዲሁም በወላጆችና በልጆች መካከል ያሉ ግንኙነቶች በጥላቻ በተሞሉባቸው ቤተሰቦች ዘንድ ነው። በቤተሰብ ውስጥ የሚፈጠር ሁከት በአብዛኞቹ ሰብአዊ ግንኙነቶች ውስጥ የቂምና የጥላቻ መራቢያ ሥፍራ ይሆናል።”

በጋብቻ ላይ የተመሠረተውና የተፈጥሮ ኅብረተሰብ የሆነው የቤተሰብ መዳከም ለመላው ኅብረተሰብ ይጠቅማል ብሎ የሚያስብ ማንም የለም። ይልቁንም እውነታው የተገላቢጦሽ ነው። የቤተሰብ ድክመት ለግለ ሰቦች ዕድገት፣ ለማኅበረሰብ እሴቶች መዳበርና ለከተሞችና ለአገሮች ግብረ ገባዊ ዕድገት ስጋት ይሆናል። በአዲስ ሕይወት ውስጥ ፍሬ የሚያፈራና በኅብረተሰብ ውስጥ ለተረጋጋ ቁርጠኝነት መስፈን ትልቁን ሚና መጫወት የሚችለው በወንድና በሴት መካከል ያለው ልዩና የማይፈርስ አንድነት ብቻ መሆኑ ገና ግንዛቤ አላገኘም። የተወሰነ መረጋጋትን የሚሰጡ እጅግ የተለያዩ የቤተሰብ ሁኔታዎች መኖራቸው፣ ነገር ግን ለምሳሌ፥ በተጨባጭ የሚታዩ ወይም በተመሳሳይ ጾታ መካከል የሚፈጠሩ ጥምረቶች ከጋብቻ ጋር ሊስተካከሉ አይችሉም። ሕይወትን የማያስተላልፍ ጊዜያዊ ወይም ዝግ የሆነ ጥምረት የኅብረተሰብን የወደፊት ዕድል ሊያረጋግጥ አይችልም። ይሁን እንጂ ዛሬ ጋብቻዎችን ለማጠናከር፣ ባለ ትዳሮች ችግሮቻቸውን እንዲያሸንፉ ለመርዳት፣ ልጆቻቸውን እንዲያሳድጉ ለመደገፍ፣ በጥቅሉ፣ የጋብቻ ትስስር የተረጋጋ እንዲሆን ለማበረታታት ጥረት የሚያደርግ ማነው?

“አንዳንድ ኅብረተሰቦች አሁንም ከአንድ በላይ ሚስት የማግባት ልምድ አላቸው። በሌላ ቦታዎች ደግሞ በወላጆች ፍላጎት የሚቀናጁ ጋብቻዎች ሥር የሰደዱ ልማዶች ናቸው።… በምዕራብ አገራት ብቻ ሳይሆን በብዙ ቦታዎች ከጋብቻ በፊት አብሮ መኖር እንዲሁም የጋብቻ ፍላጎት ጨርሶ ሳይኖር በደባልነት የመኖር ሁኔታ  በስፋት ይታያል።” (40) በተለያዩ አገራት፣ ከጋብቻ ሌላ ልዩ ልዩ አማራጮችን የሚደግፍ ደንብ ቁጥሩ እየጨመረ መጥቶአል። በመሆኑም  ልዩ፣ የማይፈርስና ለሕይወት ክፍት የሆነው ጋብቻ ኋላ ቀርና አሮጌ አማራጭ መስሎ እስከ መታየት ደርሶአል። ብዙ አገራት ሙሉ በሙሉ በግለሰብ ፈቃድና ነጻነት ላይ የተመሠረቱ አሠራሮችን በመከተል የቤተሰብን ሕጋዊነት እየሸረሸሩት ይገኛሉ። በእርግጥ በአምባገነንነትና በሁከት ጭምር የሚታወቁ አሮጌ ባህላዊ የቤተሰብ ቅርጾችን መጥላት ሕጋዊም፣ መብትም ቢሆን፥ ይህ ሁኔታ የጋብቻን እውነተኛ ትርጉምና ተሐድሶ መደገፍ እንጂ ጋብቻን ራሱን ወደ ማንኳሰስ ሊያመራ አይገባም። “የቤተሰብ ጥንካሬ የሚወሰነው መውደድንና መወደድን በማስተማር ችሎታው ላይ ነው፤ ችግሮቹ በርካታ ቢሆኑም ቤተሰብ ግን በፍቅር ምን ጊዜም ያድጋል።”

በዚህ አጭር ግምገማ ውስጥ የሴቶችን መብቶችና እነርሱም በሕዝባዊ ኑሮ ውስጥ ያላቸውን ተሳትፎ በመገንዘብ ረገድ ትልቅ እርምጃ ቢኬድም፥ በአንዳንድ አገሮች እነዚህን መብቶች ለመንከባከብ ገና ብዙ እንደሚቀር ላሰምርበት እወዳለሁ። ተቀባይነት የሌላቸው ወጎችና ልማዶች መወገድ ይኖርባቸዋል። በተለይ የወንድ ጉልበት ማሳያ ከመሆን ባሻገር የፈሪዎች ድርጊት የሆነውን አንዳንድ ጊዜ በሴቶች ላይ የሚፈጸመውን አስጸያፊ እንግልት፣ የቤት ውስጥ ሁከትና የተለያዩ የባሪያ አሳዳሪነት ቅርጾችን ለማውሳት እወዳለሁ። በአንዳንድ ትዳሮች ውስጥ ሴቶች የሚደርስባቸው ቃላዊ፣ አካላዊና ጾታዊ ጥቃት መሠረታዊ የጋብቻ ትስስርን ባህርይ ይጻረራል። እዚህ ላይ በአንዳንድ ባህሎች ውስጥ የሚካሄደውን አስወቃሽ የሴቶች ግርዛት ብቻ ሳይሆን፥ ለሰብዓዊ ክብር ለተገባ ሥራና ለውሳኔ ሰጭነት ሚና እኩል ተደራሽ አለመሆናቸውን ለማውሳት እሻለሁ። ታሪክ ሴቶችን የበታች አድርገው በሚቆጥሩ ገደብ የለሽ አባታዊ ባህሎች የተሞላ ነው፤ ሆኖም በዘመናችን እናቶችን የመጠቀም እንዲሁም “በዘመኑ የመገናኛ ብዙሃን ባህል የሴት ገላን የመበዝበዝና ሸቀጥ የማድረግ” ሁኔታን ችላ ማለት አንችልም። ከዛሬ ዘመን ችግሮች አብዛኞቹ የተነሡት በሴቶች ነጻነት ምክንያት ነው ብለው የሚያምኑ ወገኖች አሉ። ይሁን እንጂ ይህ ክርክር ተቀባይነት የለውም። “የተሳሳተ፣ እውነት ያልሆነ የወንድ ትምክህተኝነት ማሳያ ዘዴ ነው።” የወንዶችና የሴቶች እኩልነት መኖር፣ አሮጌ የአድልዎ ቅርጾች ሲወገዱና በቤተሰቦች መካከል የበለጠ መደጋገፍ ሲዳብር እያየን እንድንደሰት ያደርገናል። በቂ አይደሉም ብለን የምናስባቸው አንዳንድ የሴቶች እንቅስቃሴዎች ካሉ፥ በእነዚህ  እንቅስቃሴዎች ውስጥ የሴቶች ክብርና መብቶች በግልጽ እንዲታወቅ የሚያደርግ የመንፈስ ቅዱስ ሥራ እንዳለ መረዳት ይኖርብናል።

ወንዶች “በቤተሰብ ሕይወት ውስጥ፥ በተለይም ሚስቶቻቸውንና ልጆቻቸውን በመጠበቅና በመርዳት ረገድ ተመሳሳይ የሆነ ወሳኝ ሚና ይጫወታሉ።… ብዙ ወንዶች በቤተሰብ ውስጥ ያላቸውን ሚና ጠቀሜታ ተገንዝበው የወንድነት ግዴታቸውን በሚገባ ይወጣሉ። በቤተሰብ ውስጥ የአባት አለመኖር የቤተሰብ ኑሮን፣ የልጆችን አስተዳደግና የእነርሱንም ከኅብረተሰቡ ጋር የመዋሐድ ሁኔታን ክፉኛ ይጎዳል። አካላዊ፣ ስሜታዊ፣ ሥነ አእምሮአዊና መንፈሳዊ ግድፈት ልጆችን ጥሩ አባታዊ ምሳሌ ያሳጣቸዋል።”

ሌላው ተግዳሮት ከተለያዩ የሥርዓተ ጾታ አመለካከቶች የሚመነጭ ሲሆን፥ እርሱም “በተፈጥሮ የወንድንና የሴትን ልዩነትና ተደጋጋፊነት የሚክድና የጾታ ልዩነት የሌለበትን ኅብረተሰብ የሚናፍቅ፣ ከዚህም የተነሣ የቤተሰብን ሥነ-ሰብዓዊ (አንትሮፖሎጂካዊ) መሠረት የሚንድ ነው፡፡ ይህ የአመለካከት ዘይቤ በወንድና በሴት መካከል ካለው ሥነ-ሕይወታዊ ልዩነት ፈጽሞ ወደ ራቁና ግላዊ ማንነትንና ስሜታዊ ቅርበትን ወደሚደግፉ የትምህርት ፕሮግራሞችና ሕግጋት ይወስዳል። የሰው ማንነት በጊዜ ሂደት ግለሰቡ ራሱ የሚለወጥበት የግለ ሰብ ምርጫ ይሆናል።” አንዳንድ ጊዜ ትክክለኛ ተስፋ ናቸው ተብለው የሚገመቱ እነዚህን የመሰሉ አመለካከቶች ራሳቸውን ፍጹምና ምሉዕ አስመስለው ማቅረባቸውና እንዲያውም ልጆች እንዴት ማደግ እንዳለባቸው ማስገደዳቸው አሳሳቢ ነገር ነው። “ሥነ-ሕይወታዊ ጾታና የጾታ ማኅበራዊና ባህላዊ ሚና ተለይተው ቢታወቁም፥ ሊነጠሉ ግን እንደማይችሉ” አጽንኦት ሊሰጠው ይገባል። በሌላ በኩል፥ “በሰው ልጅ ሥነ-ተዋልዶ መስክ ያለው የቴክኖሎጂ አብዮት በወንድና በሴት መካከል ከሚኖረው ወሲባዊ ግንኙነት ነጻ የሆነ የሥነ-ተዋልዶ ሥራን የመለወጥ ችሎታን አስገኝቶአል። በመሆኑም የሰው ሕይወትና ወላጅነት ምሳሌአዊና ተነጣይ እውነታዎች፥ በዋናነትም ለግለሰቦች ወይም ለጥንዶች ፍላጎት ተገዥ ሆነዋል።” የሰውን ደካማነትና የሕይወትን ውስብስብነት መረዳት አንድ ነገር ሆኖ፥ የእውነታን የማይነጣጠሉ ገጽታዎች ለማቅረብ የሚጥሩ ርእዮተ ዓለሞችን መቀበል ሌላ ነገር ነው። ፈጣሪን ለመተካት በመሞከር ወደ ኃጢአት አንግባ! እኛ ፍጡራን እንጂ ሁሉን ቻይ አይደለንም። ፍጥረት ከእኛ ይቀድማልና እንደ ስጦታ መቀበል ያስፈልጋል። ከዚህ ሌላ ስብዕናችንን መጠበቅ ይኖርብናል፤ ይህም ማለት ከሁሉ አስቀድሞ ስብዕናችንን በተፈጠረበት መልኩ መቀበልና ማክበር ያስፈልገናል።

ራሳቸውን ፍጹም አድርገው የማይመለከቱ ብዙ ቤተሰቦች በፍቅር ሲኖሩ፥ ጥሪያቸውን ሲፈጽሙና በመንገድ ላይ ብዙ ጊዜ ቢወድቁም እንኳ ጉዞአቸውን ወደ ፊት ሲቀጥሉ ሳይ እግዚአብሔርን አመሰግናለሁ። ዓይነተኛ የሆነ ቤተሰብ ተምሳሌት እንደሌለ፥ ያለው የራሳቸው ደስታ፣ ተስፋና ችግሮች ካሉአቸው ከብዙ ልዩ ልዩ እውነታዎች የተዋቀረ ውስብስብ ገጽታ መሆኑን የሲኖዶሱ ሐሳቦች ያሳዩናል። ስለዚህ እኛን የሚመለከቱ ሁኔታዎች ተግዳሮቶች ናቸው። ጉልበታችንን በአሳዛኝ ለቅሶ ከማሳለፍ ይልቅ አዳዲስ የተልዕኮ የፈጠራ ዓይነቶችን መሻት ይኖርብናል። በሚፈጠር በማናቸውም ሁኔታ ውስጥ “ቤተክርስቲያን የእውነትና የተስፋ ቃል የመስጠትን አስፈላጊነት በሚገባ ትገነዘባለች።… የጋብቻና የክርስቲያናዊ ቤተሰብ ታላቅ እሴቶች የሰው ልጅ ሕልውና አካል ከሆነው ምኞት ጋር የሚመሳሰሉ ናቸው።” ምንም ያህል በርካታ ችግሮችን ብናይ፥ የኮሎምቢያ ጳጳሳት እንደተናገሩት፥ እነዚህን ችግሮች “የተስፋችን ማደሻና የነቢያዊ ራዕይ፣ የለውጥ ተግባራትና የአዲስ ልግስና ጥሪ ምንጭ” አድርገን እንቁጠራቸው።

ምንጭ፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ፥ ፍቅር በቤተሰብ ውስጥ በሚል ርዕሥ ለጳጳሳት፣ ለካህናትና ለዲያቆናት፣ ለመነኮሳት፣ ለክርስቲያን ባለ ትዳሮች እና ለምእመናን በሙሉ ያስተላለፉት የድኅረ ሲኖዶስ ሐዋርያዊ ምክር፥ ከአንቀጽ 48-56 ላይ የተወሰደ።

አዘጋጅ እና አቅራቢ ባራና በርግኔ

16 September 2023, 08:21