ፈልግ

ፍቅር በቤተስብ ውስጥ፤ ፍቅር በቤተስብ ውስጥ፤ 

የቤተሰብ ተሞክሮችና ተግዳሮቶች፤ አሁን ያለው የቤተስብ እውነታ

የሲኖዶሱ አባቶች “የአካል ጉዳተኝነት ያልተጠበቀ ተግዳሮት የቤተሰብ ሚዛንን፣ ምኞትና ተስፋን ሊያናጋ ስለሚችል ልዩ እንክብካቤ የሚያሻቸው ሰዎች ስላሉባቸው ቤተሰቦች” ልዩ ትኩረት እንዲሰጥ አሳስበዋል። “ልዩ ድጋፍ የሚፈልግ ልጅ የማሳደግ አስቸጋሪ ፈተናን በጸጋ የሚቀበሉ ቤተ ሰቦች ሊደነቁ ይገባል። እነዚህ ቤተሰቦች ለቤተ ክርስቲያንም ሆነ ለኅብረተሰብ እንዲሁም ለሕይወት ስጦታ ታማኝ ስለ በመሆን የማይተካ ምስክርነት ይሰጣሉ። በእነዚህ ሁኔታዎች ውስጥ ያለ ቤተሰብ ከክርስቲያን ማኅበረሰብ ጋር በመተባበርና የሰውን ሕይወት ደካማነት ምሥጢር በደስታ ተቀብሎ በመንከባከብ፣ አዲስ የአቀራረብ ስልቶችንና የድርጊት ዘዴዎችን ሊቀይስና ከሌሎች ጋር የመቀራረብና የመመሳሰል መንገዶችን ሊያገኝ ይችላል። የአካል ጉዳተኞች ለቤተሰብ ስጦታና እርስ በርስ በመረዳዳት ለማደግ መልካም ዕድል የሚያጎናጽፉ ናቸው።

ቤተሰብ በእምነት ብርሃን ተመርቶ ልዩ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸውን ሰዎች በደስታ መቀበሉ የእያንዳንዱን ሰብአዊ ሕይወት ጥራትና ዋጋ ከነተገቢ ፍላጎቶቹ፣ መብቶቹና ዕድሎቹ ለማወቅና ለማረጋገጥ ያስችላል። ይህ የአቀራረብ ዘዴ ለእነዚህ የአካል ጉዳተኞች እንክብካቤና አገልግሎት ለመስጠት ይረዳል፣ ሰዎችም አካል ጉዳተኞችን እንዲቀርቡአቸውና በእያንዳንዱ የሕይወታቸው ደረጃ ፍቅር እንዲሰጡአቸው ያበረታታቸዋል። እዚህ ላይ ለስደተኞችና ልዩ እንክብካቤ ለሚያሻቸው ሰዎች ጭምር የሚሰጥ ፍቅርና እንክብካቤ የመንፈስ ቅዱስ ምልክት መሆኑን በአጽንኦት ለመግለጽ እወዳለሁ። ሁለቱም ሁኔታዎች መሠረታዊ ሌሎችን በምሕረት ለመቀበልና ደካሞችን በማኅበረሰባችን ውስጥ ሙሉ ለሙሉ እንዲታቀፉ ለመርዳት ያለንን ቁርጠኝነት ለማወቅ የሚረዱ መሠረታዊ ነገሮች ናቸው።

አብዛኞቹ ቤተሰቦች ለአረጋውያን ትልቅ አክብሮት አላቸው፤ እንደ በረከትም ስለሚቆጥሩአቸው በፍቅር ይንከባከቡአቸዋል። ከዚህ ሌላ፣ አረጋውያንን በመንፈስም ሆነ በማህበራዊ ኑሮ ረገድ ለማገልገል ቄርጠኝነት ላላቸው ተቋማትና የቤተሰብ እንቅስቃሴዎች ልዩ ምሥጋና ያስፈልጋቸዋል። “… የወሊድ ምጣኔ እየቀነሰ ቢሆንም፣ የአረጋውያን ቁጥር እየጨመረ ባለባቸው በኢንዱስትሪ በገፉ ኅብረተሰቦች ዘንድ አረጋውያን እንደ ሸክም ይቆጠራሉ። በሌላ በኩል፥ አረጋውያን የሚፈልጉት እንክብካቤ ብዙውን ጊዜ በዘመድ አዘማድ ላይ ውጥረት ይፈጥራል”። በመጨረሻው የዕድሜ ደረጃ ላይ እንክብካቤና ፍቅር መስጠት፣ የዘመኑ ኅብረተሰብ የሞትንና የሞትን ዱካ ሁሉ ለማጥፋት ጥረት በሚያደርግበት በዛሬ ጊዜ አስፈላጊነቱ ይበልጥ የጎላ ነው። ደካማና ጥገኛ የሆኑ አረጋውያን አልፎ አልፎ ለኢኮኖሚአዊ ጠቀሜታ ሲባል ያለ አግባብ ይበዘበዛሉ። ብዙ ቤተሰቦች የአንድን ሰው በጌታ የፋሲካ ምስጢር የመርካትና የመሳተፍ ስሜትን አስፈላጊነት በማጉላት ወደ ሕይወት ፍጻሜ ደረጃ መድረስ እንደሚቻል እያሳዩን ነው።

እጅግ በርካታ አረጋውያንም በቁሳቁስም ሆነ በመንፈሳዊ ረገድ፥ በሰላማዊ የቤተሰብ አካባቢ መኖር እንዲችሉ በቤተ ክርስቲያን ተቋማት ውስጥ እንክብካቤ ይደረግላቸዋል። “ከሕመሙ የመዳን ዕድል የሌላቸው በሽተኞችን እንዲሞቱና ራሳቸውን እንዲያጠፉ ማገዝ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለቤተሰቦች ሥጋት ሆኖአል። በብዙ አገሮች እነዚህ ድርጊቶች ሕጋዊ ሆነዋል። ቤተ ክርስቲያን እነዚህን ልማዶች በጽኑ ከመቃወም ባሻገር አረጋውያንንና አካል ጉዳተኛ አባሎቻቸውን ለሚንከባከቡ ቤተሰቦች ዕርዳታ ማድረግ አስፈላጊ እንደ ሆነ ይሰማታል።” እዚህ ላይ በከፋ ድህነትና በትልቅ የአቅም እጥረት ውስጥ የሚኖሩ ቤተሰቦችን ሁኔታ ለመጥቀስ እፈልጋለሁ። ድሃ ቤተሰቦች ብዙውን ጊዜ የሚያጋጥሙአቸው ችግሮች እጅግ ፈታኝ ናቸው። (ፍቅር በቤተስብ ውስጥ ቁ. 36)

ለምሳሌ አንዲት እናት ብቻዋን ልጅ ማሳደግና ወደ ሥራ ስትሄድ ልጅዋን ብቻውን መተው ካለባት፥ ልጁ ለማናቸውም ዐይነት ስጋትና ለሰብአዊ ዕድገት መሰናክል የተጋለጠ ሆኖ ያድጋል። በእነዚህ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ቤተ ክርስቲያን ሰዎች የእግዚአብሔርን ምሕረት ማሳየት የሚገባት እናት ኮንናለች፣ ለብቻችን ትታናለች ብለው እንዲያስቡ የሚያደርጉአቸውን ሕጎችና ደንቦች ከማስቀመጥ ይልቅ መረዳትን፣ መጽናናትን እና ተቀባይነት ማግኘትን በመስጠት ላይ ማተኮር ይኖርባታል። የጸጋን ፈዋሽ ኃይልና የወንጌል መልዕክትን ብርሃን በመስጠት ፈንታ አንዳንዶች ያንን መልዕክት “በማስረጽ በሌሎች ላይ ወደሚወረወሩ ግዑዝ ድንጋዮች” ይለውጡታል።

ምንጭ፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ፥ ፍቅር በቤተሰብ ውስጥ በሚል ርዕሥ ለጳጳሳት፣ ለካህናትና ለዲያቆናት፣ ለመነኮሳት፣ ለክርስቲያን ባለ ትዳሮች እና ለምእመናን በሙሉ ያስተላለፉት የድኅረ ሲኖዶስ ሐዋርያዊ ምክር ከአንቀጽ 46-48 ላይ የተወሰደ።

አዘጋጅ እና አቅራቢ ባራና በርገኔ

09 September 2023, 20:46